Saturday, 29 April 2017 15:41

ሰሜን ኮርያ በየ2 ወሩ 1 የኒውክሌር መሳሪያ የማምረት አቅም ፈጥራለች ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የአሜሪካና የሰሜን ኮርያ ፍጥጫ ተባብሷል

      አለማቀፍ ውግዘት፣ ተደራራቢ ማዕቀብ፣ የማያባራ ዛቻና ማስጠንቀቂያ የኒውክሌርና የሚሳኤል ፕሮግራሟን ከማስፋፋትና ከማሳደግ በፍጹም እንደማይገታት በይፋ ስታውጅ የዘለቀቺው ሰሜን ኮርያ፣ በየሁለት ወሩ አንድ የኒውክሌር መሳሪያ ማምረት የምትችልበት አቅም ላይ መድረሷ ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት የሰሜን ኮርያን የኒውክሌር ፕሮግራም አቅምና የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ በስውር ያስጠናውን ጥናት ጠቅሶ ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፣ ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር አቅሟን በተፋጠነ ሁኔታ በማሳደግ በየስድስት ሳምንቱ አንድ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ማምረት የምትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡
የሰሜን ኮርያ እና የአሜሪካ ፍጥጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ አሜሪካ በደቡብ ኮርያ ጦር ማስፈሯንና በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ስራ የሚጀምርና ታድ የሚል ስያሜ የተሰጠው የተራቀቀ ጸረ-ባላስቲክ ሚሳኤል መከላከያ ሲስተም ባለፈው ረቡዕ መትከል መጀመሯንም ገልጧል፡፡
ሰሜን ኮርያ በ11 አመታት ውስጥ ስድስተኛውን የኒውክሌር ሙከራ እንደምታደርግ ከሰሞኑ መዛቷን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህን ተከትሎም ቻይና ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር ሙከራውን እንዳታደርግ ያስጠነቀቀች ሲሆን፣ አሜሪካ በደቡብ ኮርያ በመትከል ላይ የምትገኘውን የሚሳኤል መከላከያም የአካባቢውን ውጥረተ ክፉኛ የሚያባብስ ስለሆነ በአፋጣኝ እንዲቆም ጠይቃለች፡፡

Read 2822 times