Sunday, 30 April 2017 00:00

የታጂኪስታኑን መሪ ባለ 19 ቃል ማዕረግ ያልጠራ ጋዜጠኛ ይቀጣል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የታጂኪስታን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ኢሞማሊ ራህሞንን የተመለከቱ ዘገባዎችን በሚሰሩበት ወቅት፣ ከስማቸው በፊት በእንግሊዝኛ 19 ቃላት ያሉትን ረጅም ማዕረጋቸውን አሟልተው እንዲጠሩ የሚያስገድድና ቅጣትን የሚያስከትል አዲስ ህግ መውጣቱ ተዘግቧል፡፡
የሰላምና የብሄራዊ አንድነት መስራች፣ የሃገሪቷ መሪ፣ የታጂኪስታን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፣ የተከበሩ ኢሞማሊ ራህሞን የሚል አማርኛ አቻ ያለውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሉ ማዕረግ ሳይጠራ ዘገባ የሚሰራ ጋዜጠኛ ህገወጥ ድርጊት እንደፈጸመ ተቆጥሮ ቅጣት እንዲጣልበት የሚደነግገው ህግ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዋናው የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜናዎችን በሚሰራበት ወቅት ይህንን ህግ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የጠቆመው ዘገባው፣ የፕሬዚዳንቱ ስም ከእነ ሙሉ ማዕረጋቸው በቴሌቪዥኑ ግርጌ በተንቀሳቃሽ ጽሁፍ መልክ ታይቶ ለማለቅ 15 ሰከንድ ያህል እንደወሰደም አመልክቷል፡፡
አስቂኙ ህግ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በማህበራዊ ድረገጾች መሳለቂያ ሆኖ መዝለቁን የጠቆመው ዘገባው፣ አንዳንድ አስተያየት ሰጪ የአገሪቱ ወጣቶችም፣ የፕሬዚዳንቱ ማዕረግ በጣም አጥሯልና ሊጨመርበት ይገባል ሲሉ መሳለቃቸው ተነግሯል፡፡
በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ በፕሬስ አፈና እና በመናገር ነጻነት አልቦነት ስሟ የሚጠራውን ታጂኪስታንን እ.ኤ.አ ከ1992 አንስቶ በማስተዳደር ላይ በሚገኙት የፕሬዚዳንቱ ዘልዛላ ማዕረግ ላይ ሊጨመሩ ይገባል በሚል በፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከተሰነዘሩት አዳዲስ ማዕረጎች መካከልም፣ “የጨረቃው ሰው” እና “የአለሙ ሁሉ ፈጣሪ” የሚሉት ይገኙበታል፡፡

Read 1287 times