Sunday, 30 April 2017 00:00

19 ሚ. የመናውያን የ1.1 ቢ. ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

  በየመን በየ10 ደቂቃው አንድ ህጻን ይሞታል

      በጦርነት በፈራረሰችዋና የዓለማችን የከፋው ርሃብ ሰለባ በሆነቺው የመን የሚኖሩ 19 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች 1.1 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2017 የመናውያንን ከከፋ ጥፋት ለመታደግ የሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሆነ ያስታወሰው ተመድ፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ማሰባሰብ የተቻለው 15 በመቶውን ያህል ብቻ መሆኑን ጠቅሶ፣ ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬስም የመናውያንን ለመታደግ አለማቀፉ ማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን አመልክቷል፡፡
የዛሬይቱ የመን ሙሉ ትውልድ በአለማችን እጅግ የከፋው ርሃብ እየተጠቃ ነው ያሉት ጉቴሬስ፤3 ሚሊዮን ዜጎቿ ቤታቸውን ጥለው በተሰደዱባትና በጦርነት በፈራረሰቺው የመን የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ እየከፋ መሄዱን ገልጸዋል፡፡
በየመን በየአስር ደቂቃው ዕድሜው ከአምስት አመት በታች የሆነ አንድ ህጻን በመከላከል ሊድኑ በሚችሉ ምክንያቶች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረግ የጠቆሙት አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ አለማቀፉ ማህበረሰብና የሰብዓዊ ድጋፍ ተቋማት በተለይም ለየመናውያን ህጻናት ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

Read 1261 times