Sunday, 30 April 2017 00:00

ቱርክ 1 ሺህ ፖሊሶችን ስታስር፣ ከ9 ሺህ በላይ ከስራ አባርራለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የቱርክ መንግስት ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን 1 ሺህ ፖሊሶች ያሰረ ሲሆን ከ9 ሺህ 100 በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ ፖሊሶችን ደግሞ ከስራ ገበታቸው ማባረሩን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ጠይብ ኤርዶጋን ከሳምንታት በፊት በተከናወነው ህዝበ ውሳኔ ተጨማሪ ሃይል የሚሰጣቸውን ድል መቀዳጀታቸውንና መንግስትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘሙን ተከትሎ፣ በአገሪቱ ተቃውሞ እንደገና መቀስቀሱን የጠቆመው ዘገባው፤ ከስልጣን ሊያስወግዱኝ እያሴሩ ነው ካሏቸው ቡድኖች ጋር ንክኪ አላቸው ያሏቸውን ፖሊሶች ባለፈው ረቡዕ ታድነው እንዲታሰሩ ማድረጋቸውን ገልጧል፡፡ 8 ሺህ 500 ያህል የመንግስቱ ታማኝ ፖሊሶች በተሳተፉበትና መላ ቱርክን ባዳረሰው አሰሳ፣ 1 ሺህ 120 ያህል ፖሊሶች መታሰራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ለቱርክ ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ናቸው የተባሉ 9 ሺህ 103 ፖሊሶችም ከስራ ገበታቸው እንዲባረሩ ተደርጓል ብሏል፡፡
ተቀማጭነታቸው በአሜሪካ የሆነው ፈቱላህ ጉሌን ያቋቋሙት ቡድን ያቀናበረው ነው የተባለውና ባለፈው ሃምሌ ወር በኤርዶጋን ላይ የተቃጣው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ለእስር የዳረጋቸው ዜጎች ብዛት 47 ሺህ፣ ከስራ የተባረሩት ደግሞ 120 ሺህ ያህል መድረሱንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የቱርክ መንግስት ከከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ የሚያስራቸውና ከስራ ገበታቸው የሚያፈናቅላቸው ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ አለማቀፍ ትችት እንደገጠመው የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፣ አገሪቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን የጀመረቺውን ጥረት እያጓተተው እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

Read 3219 times