Sunday, 07 May 2017 00:00

የተመድ የሠብአዊ መብት ኮሚሽነር በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የታሰሩ የፓርቲ አመራሮችን አነጋግረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የኦሮሚያና አማራ ክልሎችን መጎብኘት አልቻለም
     በኢትዮጵያ ጉብኝነት ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራኢድ፤  በሃገሪቱ የሠብአዊ መብት ይዞታ ላይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን በቂሊንጦ  ማረሚያ ቤት የታሰሩ የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮችንም ማነጋገራቸው ተጠቁሟል፡፡
ኤዴፓ፣ ሠማያዊና መኢአድን ጨምሮ የኢህአዴግ ተወካይ ባሉበት ከ11 ፓርቲዎች ጋር የተወያዩት ኮሚሽነሩ፤ በሃገሪቱ የሠብአዊ መብት አጠባበቅ፣ በሙስና እና በሚዲያ ነፃነት ጉዳይ ላይ የቀረበላቸውን አቤቱታ ካዳመጡ በኋላ ችግሮቹን ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር እንደሚያዩባቸው አስታውቀዋል፡፡ ሠማያዊ ፓርቲን ወክለው የተሳተፉት አቶ አበበ አከሉ ለአዲስ አድማስ ስለ ውይይቱ በሰጡት መረጃ በተለይ በቅርቡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የቀረበውን ሪፖርት ተቀዋሚዎች እንደማይቀበሉት፣ በአመፅና ተቃውሞው መነሻ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በጅምላ መታሰራቸውንና ለ4 ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሃገሪቱን እየጎዳ መሆኑን ማስረዳታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በሃገሪቱ ሙስና የከፋ ደረጃ ላይ መድረሡንና ሃገሪቱን ወደማትወጣው አዘቅት እየከተታት መሆኑን መግለፃቸውን ጠቁመው በውይይቱ የተገኙት የኢህአዴግ ተወካይም ችግሩ ቢኖርም መንግስታቸው ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ማሰረዳታቸውን አቶ አበበ ጠቁመዋል፡፡
በሃገሪቱ ነፃ ፕሬስና የጋዜጠኝነት ሙያ አደጋ ላይ መውደቁን፣ ጋዜጠኞች እንደሚታሠሩና የፕሬስ ነፃነት እንደማይከበር ለኮሚሽነሩ እንደተብራራላቸው ተጠቁሟል፡፡ የተቀዋሚዎችን ሃሳብ ያዳመጡት ኮሚሽነሩ፤ ‹‹እኛ እናንተን እንረዳችኋለን እንጂ በሃገራችሁ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም፤ የሃገራችሁ መፍትሄ በእናንተው እጅ ነው፡፡›› የሚል ሃሳብ ማቅረባቸውንና በተነሡት ችግሮች ላይም ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚመክሩበት ቃል መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ከኮሚሽነሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ‹‹መድረክ›› ጥሪው በአግባቡ ስላልደረሰኝ አልተገኘሁም ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽነሩ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን የጎበኙ ሲሆን አንድ ከፍተኛ የተቀዋሚ ፓርቲ አመራር ማነጋገራቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ ያነጋገሩት የፓርቲ አመራር የኢፌኮ ም/ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞች ስለ ጉብኝታቸው  በሠጡት መግለጫ፤ በቅርቡ በተቃውሞና ግጭት ውስጥ የነበሩትን በአማራና በኦሮሚያ የሚገኙ አካባቢዎችን ለመጎብኘት እድል አለማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

Read 2227 times