Wednesday, 04 April 2012 09:19

የላሊበላው የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነብይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

አንድ ፀሐፊ ስለጉዞው ማስታወሻ የፃፈውን ያዩ ሰዎች “ይሄ ጉዞህ መቼ ነው የሚያልቀው?” ቢሉት፤ “እግሬ ሲያልቅ” ብሎ መሰስ ይላሉ፡፡ እግራችን እስኪያልቅ እንጓዝ፡፡ቀጥለን የምናገኘው ቤተ-መስቀልን ነው - ከቤተ ማርያም በሰሜናዊው አቅጣጫ፡፡ በሩ በደቡብ አቅጣጫ ብቻ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጠኛ ክፍል ወደ ዕቃ ቤት የሚወስድ በር አለው፡፡ እንደሌሎቹ ቤተ-ክርስቲያናት ይህም የጥበብ መናኸሪያ ነው፡፡ ከውጪ በኩል ሲታይ በግማሽ ክብ ቅርፅ መልክ የተቀረፁ አሥር ቅርፆችን እናገኛለን፡፡ የአሥርነታቸውን ተምሳሌት ፀሀፍት በሦስት ይመስሉታል፡፡ አንደኛው፤ ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የተሰጠውን አሥሩን ቃላት ኦሪት፡፡ ሁለተኛው በደብረ ኖህ የተሰሩትን አሥሩን አብያተ ክርስቲያናት፡፡ ሦስተኛው፤ እሌኒ ንግሥት የክርስቶስን መስቀል ፈልጋ ያገኘችው ከመጋቢት ወር በ10ኛው ቀን መሆኑን፡፡

ይህ ቤተ መቅደስ ከሌሎቹ ጠበብ ያለ መስሎ ይታይ እንጂ ታሪካዊ ሥዕሎች ግርማ ሞገሱን ያገዝፉታል፡፡ ካህናት የሚለብሱት የወርቅ ዘርፍ ያለው የቅዳሴ ልብስ፣ የሚይዟቸው የሚያብለጨልጩ ዣንጥላዎች፣ ፀናፅሎችና ከበሮዎች አስደናቂ ውበትን ያላብሱታል፡፡

ከቤተ ማርያም ደቡባዊ አቅጣጫ ወጣ ሲባል የሚታየው የቤተ-ደናግል አነስተኛው ቤተ መቅደስም ሌላው እይታ ነው፡፡ መታሰቢያነቱ በ4ኛው ክፍለ ዘመን በሮም ነግሦ የነበረው በጁሌይን ዘመን ለክርስትና እምነታቸው ሲሉ በአደባባይ ለተሰየፉት ደናግላን ነው፡፡

ፀሀፍት እንደሚጠቁሙት፤ “ንጉሥ ጁሊያን በኤዲሳ አቅራቢያ ሲያልፍ የደናግሉን መኖሪያ ይመለከትና በውስጡ ያሉ ማናቸውም ሰዎች እንዲገደሉ አንጋቾቹን ያዛል፡፡ ታዛዦቹ አንጋቾችም ደናግሉን በሰይፍ ቀጠፏቸው፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ለነዚህ ሰማዕታት ይህን ቤተ መቅደስ አነፀ!” ኢትዮጵያ ከጥንታዊው የክርስትና ዓለም ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚያጐላ ምሳሌ ነው፡፡ በቤተ ደናግል የመጨረሻ በር ተወጥቶ ከዚሁ ቤተ መቅደስ ጋር የተያያዘው የማርያም ቤተመቅደስ ንዋየ-ቅድሳት ማስቀመጫ ዕቃ ቤት እና የህሙማን ማጥመቂያ ስፍራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ሲታለፍ ሦስት መንገዶችን እናገኛለን፡፡

አንድ ወደ ቤተ መድኃኒዓለም፤ አንዱ ወደ ዋናው የመኪና መንገድ የሚወስድ ሲሆን በስተቀኝ ያለው ወደ ቤተ ደብረ ሲና ይወስዳል፡፡ ቤተ ደብረሲና 9.5 በ8.5 ሜትር ስፋትና 3 ሜትር ከፍታ ያለው ቤተ-መቅደስ ነው! በሦስት አቅጣጫ ከአለት ተፈልፍሎ የተዋቀረ ነው፡፡ በቤተ-ደብረሲና እንደ ሌሎቹ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ለዐይን የሚከብዱ ነገሮችን አናይበትም፡፡ በተለያየ አይነት ቅርፅ የተሳሉ መስቀሎች ያሉባቸው ምሰሶዎች አሉት፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ቋሚዎች ከግድግዳው ጋር በቅስት መልክ የተሰሩ ናቸው፡፡ የምዕመናኑ ፀሎት ማድረጊያ ቦታዎች ቅኔ ማኅሌቱን ጨምሮ አምስት ስፍራዎች በአምስት መስመሮች ተለይተዋል፡፡

በውስጡ ከሚገኙ ቅርሶች መካከል ካህናቱ ለዘመናት ሲያሳዩት የኖሩት በተለያየ ቀለማት ያሸበረቀ መሀረብ አለ፡፡ የቀለማቱ ውህደት አስገራሚ ናቸው!

የደብረ ሲና መንትያ ቤተ-ጐለጐታ ነው - በሰሜን አቅጣጫ የሚገኝ ነው፡፡ ቤተ-ጐለጐታ ሦስት ታቦታት ያሉበት ሲሆን ቃሉ የአረማይክ ነው፡፡ ትርጉሙም የራስ-ቅል ማለት ነው፡፡ የእየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ስፍራ ነው፡፡ ካህናቱ፤ “የአዳምና ሄዋን የዕዳ ደብዳቤ የተቀደደው፤ በአምላክና በሰው መካከል የነበረው የጥል ግድግዳም የተወገደው በጐልጐታ ላይ ነው” ይላሉ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ በእሥራኤል ያለውን ጐልጐታ እናስብ ዘንድ በምድረ ኢትዮጵያም ጐልጐታን ቀርፆታል፤ ይላሉ፡፡ በድንቅ አቀራረፅ የታነፁት ሁለት መስኮቶች አንዱ በቤተ ጐልጐታ ለሚገኘው “ለእየሱስ ቤት” (መቅደስ) ብርሃን የሚያስገባ ሲሆን ሌላው “ለሥላሴ - ቤት” (መቅደስ) ብርሃን ያስገባል፡፡ በሦስት ምሶሶዎች የተደገፉ ሁለት ቅኔ ማህሌቶች አሉት፡፡ በውስጠኛው ክፍል ስንዘልቅ “የእየሱስ ቤት” የሚባለውንና “የእየሱስ ክርስቶስ መቃብር”ን እናገኛለን፡፡

የጐልጐታን ቤተ መቅደስ አልፈን የሥላሴን ቤተ መቅደስ እናገኛለን፡፡ ይህ ቤተ መቅደስ በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ከሚገኙት ቤተ-መቅደሶች መካከል ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚታይበት ነው፡፡ ለእይታ ብዙ አይፈቀድም፡፡ የቤተ መቅደሱ ግድግዳ ሁለት ሦስተኛው በመጋረጃ የተሸፈነ ነው፡፡ ከቅድስናው የተነሳ ለካህናቱ እንኳን ግልፅ አይደለም፡፡ የመሳለሚያው ስፍራ ከአለት የተሰራ ነው፡፡ የታችኛው ምስሶ ጣሪያውን ደግፎ በመያዝ ያገለግላል፡፡ በዘመኑ የነበሩ ሰዓሊያን በማፅሀፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ታሪኮችን በስዕል ለማስቀመጥ መሞከራቸውን ከስዕሎቹ ለመረዳት ይቻላል፡፡ የሥላሴን ዙፋን ተሸክመው የሚኖሩት የአርባእቱ እንስሳ ምስልም እዚህ ይታያል፡፡

ቤተ-አማኑኤል ሌላው ፍልፍል ቤተ-ክርስቲያን ሲሆን የምድር ቤቱና ፎቅ ቤቱ መስኮቶች የአክሱምን የመሰለ ነው ቅርፃቸው፡፡ ታላቅ የተመራማሪዎች መስህብ የሆነው ይህ ቤተ-መቅደስ ውስጡ አራት አምዶች ያሉበት አዳራሽ ነው፡፡ ወደ ሰገነቱ የሚያወጣው ደረጃም ከዚያው ከአለቱ ተጠርቦ የታነፀ ነው፡፡

ተፈልፍሎ የተሰራው ከቀይ ሸክላ አለታማ ድንጋይ ነው፡፡ የቤተክርስቲያኑ ግድግዳዎች የተሰሩት ወደ ጐን እና ወደ ላይ በተመሳጠሩ ሥራዎች ነው፡፡ በሦስት የቅስት ቅርፅ የተዋቀሩ መስኮቶች አሉት፡፡ ከመስኮቶቹ ሥር የተቀረፁት መስቀሎች የግሪኮች አይነት ናቸው፡፡ የበሮቹም ሳንቃዎች በወፍራሙ ተጠርበው በዓለቱ በር መድረክና ጉበን ተሹለው የገቡ ናቸው፡፡ ስምንት መቶ ዓመታት ያህል ያለ ችግር የቆዩ ናቸው፤ ይባላል፡፡ በውስጠኛው የቤተክርስቲያኑ ክፍል አራት የተስተካከሉ፣ አራት ደግሞ በሦስት ማዕዘን የተሰሩ ምሰሶዎች አሉ፡፡ ከመቅደሱ ደቡብ ወገን ወደ ጐረቤቱ ወደ ቤተ-መርቆርዮስ የሚወስድ ዋሻ አለ!

ቀጣዩ ቤተ-መርቆርዮስ ነው፡፡ እንደ አንዳንድ መረጃዎች ከሆነ፣ ቤተመቅደሱ በሰማዕቱ ስም ከመሰየሙ በፊት ለፍትህ አገልግሎት ይውል የነበረ ነው ይላሉ፡፡ በታችኛው የህንፃው ክፍል የተገኙት የእግር ብረቶች እንደ ማስረጃ ይጠቀሳሉ፡፡ ዛሬ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እየዋለ ያለው ቤተ መቅደስ በመፍረሱ ለረጅም ጊዜ በቤተ-አማኑኤል ተዳብሎ የኖረ ነው፡፡ በመቅደሱና በማኅሌቱ 15 አምዶች አሉ፡፡ አጣጣላቸው ተወዳጅ የሆኑ የቀለም ሥራ ስዕሎች ይታዩበታል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች ጥበባቱ የ17ኛውና 18ኛው ክ/ዘመን አሻራ ይታይባቸዋል፡፡ መርቆርዮስ በሰማዕትነቱ ከፍ ያለ ክብር ከሚሰጣቸው ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡

ቤተ-አባ ሊባኖስ፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ቁጥሩ ከላሊበላ ሥራዎች ይሁን እንጂ ያነፀችው የቅዱስ ላሊበላ ባለቤተ ቅድስት መስቀል ክብራ ናት፡፡ ቅድስቲቱ በህልሟ ሲታነፅ አይታ በገዳም የምንኩስና ህይወታቸው ታዋቂ ለሆኑት ለአባ ሊባኖስ መታሰቢያ አደረገችው፡፡

ጨለምለም ባለ ዋሻ የተከበበ ግድግዳ፡፡ የአክሱማውያን ዘመን አይነት የሥዕል ጥበብ፡፡ ከአለት የተቀረፀ እንደ ዋሻ የተፈለፈለ ዙሪያ ያለው መቅደስ! የዋሻ ውስጥ ቤተ-ክርስቲያን ምሳሌ! ሦስት በዋሻ የተለዩ ክፍሎች፡፡ የቤተ መቅደሱን ህንፃ አይነት ከሌሎች የሚለየው አናቱ፤ ተፈልፍሎ ከተሰራበት አለት ጋር መያያዙ ነው፡፡ የግድግዳዎቹ አፈላፈል ከአክሱማውያን አሰራር ለየት ቢልም ባለ ሦስት ቅስት መስኮቶቹ ግን እንደ አክሱም ስልጣኔ ሥራ ነው፡፡ አንድ አስደናቂ ነገር አለ:- የመንበሩ ግድግዳ ላይ ቀን ከሌሊት ብርሃኗን የማታቋርጥና በራሷ ሃይል የምትበራ ትንሽ መብራት መኖሯ!

ከቤተ ሊባኖስ 50 ሜትር ያህል ርቃ ቤተልሄም አለች፡፡ ቤተልሄም በአሰራሯ የዋሻ ቅርፅ ያላት ወደ ውስጥ ሲገባ ከስፋት ወደ ጥበት የምትሄድ ዋሻ ናት፡፡ አጀማመሯ ጥምዝምዝ ኮረብታማ አጨራረሷ ክብ ናት፡፡ አንድ ምሰሶ ብቻ ነው ያላት፡፡ ስዕልም ሆነ ቅርፅ የላትም! የታሪክ አስረጂዎች የተለያየ ሀሳብ አላቸው - ስለ አገልግሎቷ፡፡ አንዱ ወገን ቅዱስ ላሊበላ ለሱባኤና ለፀሎት ይጠቀምባታል ይላል፡፡ ሁለተኛው ወገን ለቅዱስ ቁርባን የሚሆነው ህብስት የሚዘጋጅባት ናት ይላታል፡፡ ሦስተኛው ወገን ደግሞ ይህ ቦታ የቅዱስ ላሊበላ የፈረስ ግርግም ነበር - ምሰሶው ማሰሪያው ነው፡፡ በየትኛውም ንድፈ-ሃሳብ ይሁን ቤተልሄም ቅዱስ ስፍራ ናት፡፡

ቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል የበሩ አሰራር አምሳያ በአክሱማውያን እጅ-ጥበብ አይነት ነው፡፡ መግቢያው በቤተ አማኑኤል በሚገኘው ድልድይ ነው፡፡ የባህር ዛፍ ርብራብ ድልድይ ነው፡፡ ከዚያ ዋሻ አለ፡፡ ከዋሻው ቀጥሎ ቤተ-አማኑኤል አለ፡፡ ከአለት የተሰራው መንገዱ “የመንግሥተ ሰማያት መንገድ” ይባላል፡፡ ወደ ጣሪያው ያደርሳልና ነው፡፡ ከሰገነቱ ስንወርድ የውሃ ጉደጓድና ውስጡን የሚፈላ ውሃ እናገኛለን፡፡ ከዚያ ምሰሶዎች ያሉበት አዳራሽ አለ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ፎቅና ምድር ነው፡፡ የታችኛው ሳይፈለፈል ድፍኑን ቀርቷል፡፡ በግድግዳዎቹ መስኮቶች ያሉት ጌጦች እንዳሉ ናቸው - እስከዛሬ፡፡ ከቤተስኪያኑ ውስጣዊ ገፅታ እንደማዳመቂያ የሚታዩት ግድግዳው ላይ የተለጠፉት ሦስት የላቲን መስቀሎች ብቻ ናቸው፡፡ (የቤተ ገብርኤል ወሩፋኤል) ቤተክርስቲያን ከበዓላት ቀን ውጪ የአምልኮ ስፍራነቱ ተረስቷል ለማለት ይቻላል፡፡ ከበሮና መቋሚያዎችም ተጐሳቁለው ይገኛሉ፡፡

እግራችን እስኪያልቅ ገና እንጓዛለን!

(ይቀጥላል)

 

 

Read 2150 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 09:24