Saturday, 06 May 2017 09:18

አሰፋ ጫቦ ከ25 ዓመት ስደት በኋላ አስክሬኑ አገሩ ገባ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የቀብር ሥነ ስርአቱ ትናንት ተፈፅሟል
የአንጋፋው የህግ ባለሙያና የፖለቲካ ሊቅ አሰፋ ጫቦ የቀብር ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት በአሜሪካ በስደት ኑሮውን ሲመራ የቆየው አሰፋ ጫቦ፤ ድንገት ባደረበት ህመም በዚያው ሀገር በሚገኝ ሆስፒታል ሲረዳ ቆይቶ ሚያዚያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን አስክሬኑም ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ  ታውቋል፡፡ አስክሬኑ ከቀኑ 9 ሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሰ ሲሆን ቤተሰቦቹ እና በርካታ አድናቂዎቹ እንዲሁም ወዳጆቹ አቀባበል አድርገውለታል፡፡
ለአገሩ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት የነበረው አሰፋ፤ በህይወት ሳለ የዘወትር ምኞቱና ጉጉቱ አገሩ መግባት እንደነበር ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገችው ብቸኛ ሴት ልጁ ተናግራ ነበር፡፡
በብዙዎች ዘንድ በተባ ብዕሩ የሚታወቀው አሰፋ ጫቦ፤ አዲስ አድማስን ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በሳልና ተወዳጅ የፖለቲካ መጣጥፎችን ይፅፍ የነበረ ሲሆን በቅርቡም “የትዝታ ፈለግ” የተሰኘ መፅሐፍ ማሳተሙ ይታወሳል፡፤
አቶ አሰፋ ጫቦ የአንዲት ሴት እና የሦስት ወንዶች አባት ሲሆን በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡


Read 3294 times