Sunday, 07 May 2017 00:00

“ባይደርስህ ይሻል ነበር…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው… የዝሆን ስባሪ የሚያካክሉት አገሮች ፉከራ በዛሳ! የእውነት አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ደርስናል እንዴ! እነሱ በሚፎካከሩት የእኛ ልብ ቀጥ ልትል ነው እኮ!
ደጉን ያሰማን፡፡
ስሙኛማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እሱዬው ከአንድ ወዳጄ ከሚለው ሰው ጋር በሆነ ነገር ሳይስማሙ ቀርተው ከተራራቁ የተወሰነ ጊዜ ሆኗል፡፡ በዛ ሰሞን ያኛው ይደውልና ላገኝህ  እፈልጋለሁ ይላል፡ ይሄን ጊዜ ይህኛው ደስ አላለውም፡፡ “አግኘውና የሚለውን ስማው…” ሲባል ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ስንት ወር ቆይቶ የደወለልኝ ተንኮል ቢያስብ ነው፣” አለላችሁ፡፡
ምን ይደረግ ዘመኑ እንደዛ አድርጎናል፡፡ ምንም አይነት ነገር ይሁን..
“እንደዛ የሚለው ተንኮል ቢያስብ ነው…”  
“አጅሪት ግብዣ ግብዣ የምትልኝ የሆነ ነገር አስባ ነው…” የምንባባልበት ዘመን ሆኗል፡፡
የሆነ ሰው ደስ አለው እንበል፡፡ “ስማ… አሪፍ ወሬ አለኝ፣ መጀመሪያ እንኳን ደስ አለህ በለኝ…”
“ምን አገኘህና…ዲቪ ደረሰሀ እንዴ”
“ሎተሪ ደረሰኝ…”
ሎተሪ! ጓደኝየውም የሚሰማውን ደስታ አስቡትማ፡፡ አሀ…ምናልባት “እንዴት ነው ከፍዬ የምጨርሰው?” እያለ ሲያስጨንቅው ለነበረው የኮንዶሚኒየም ቀሪ ክፍያ ድጋፍ ሊገኝ ይችላላ! ሲያምረው የኖረውን አርባ ሁለት ኢንች ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን በስጦታ ሊያገኝ ይችላላ!
“ሎተሪ!” ያዝናል፡፡ “ኸረ ባይደርስህ ይሻል ነበር፣” ይለዋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ! ዘሎ አንገት ላይ ይጠመጠማል ሲባል…
እልል በይ ሀገሬ
የእኩል ሆንሽ ዛሬ
እያለ ሆታውን ያስነካዋል ሲባል ጭራሽ “ባይደርስህ ይሻል ነበር…” ብሎ ነገር ምን የሚሉት አማርኛ ነው!
“ያምሀል እንዴ፣ ሎተሪ ደረሰኝ እያልኩህ ነው እኮ! ባይደርስህ ይሻል ነበር ትለኛለህ!”
“ምቀኛው! ጌታው ምቀኛው አያስቀምጥህም! ምን አለ በለኝ፣ ዘመድ በለው፣ ባዳ በለው ተንኮል ሲጎነጉንልህ ነው የሚያድረው፡፡ ያው ድህነትህ ይሻልህ ነበር፡፡”
እኔ የምለው…. የእነ እንትናን ‘አርአያ’ ተከትለን ቪ ኤይት ምናምን ስንመኝ ‘ድህነት’ እንዴት ነው የሚሻለን!  ስሙኝማ…ይቺ “ሀብት ኖሮህ ምቀኛ ከሚከብህ የድሀ ቆሎህን እየቆረጠምክ ያለ ሀሳብ መተኛት ይሻላል…” የሚሏት ነገር እጅና እግርን አስራ ቁጭ ነው የምትለው፡፡
እግረ መንገዴን… ድህነት ላይ ያሉ አንዳንድ አባባሎቻችን ግርም አይሏችሁም!
‘ድሀ ሲቀልጥ አመድ፡ አመድ ይሸታል’
‘ድሀ ሲንቀባረር ያለቀሰ ይመስላል’
‘ድሀ ቅቤ ወዶ፣ ማን ይሸከም ነዶ’
የምር ግን… ባለሙያዎቹ አብረውን የቆዩትን አንዳንድ አባባሎቻችንን  እየመረመሩ ከጊዜው ጋር ሊያስኬዱልን ይገባል፡፡
እናላችሁ… ሎተሪ የደረሰው ሰው ወዳጅ ምክሩን ይቀጥላል፡፡ “እየው ምንም አይነት ነገር ምግብ፣ መጠጥ የደስ ደስ ብለው ቢያመጡልህ እንዲች ብለህ እንዳትቀምስ! ዘወር ሲሉልህ ጓሮ ወስደህ መድፋት ነው፡፡”
እናላችሁ… ያለመተማመናችን፣ እርስ በእርስ የመጠራጠራችን፣ “ደህና የሚባል ሰው ድሮ ቀረ” የመባባላችን ነገር የደረሰበት ደረጃ የምር የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ምንም ነገር ላይ መተማመን እያቃተን ነው፡፡  ድንገት ዘወር ብሎ ያየንን ሁሉ…
“ይሄንን ደግሞ ማን ልኮብኝ ነው?” የምንልበት ዘመን ሆኗል፡፡ ከርሞ ሊጠይቀን የመጣን ዘመድ… “የሆነ ተንኮል አስባ ነው እንጂ ዛሬ ምን ተገኘና ነው ቤቴ ድረስ የመጣችው!” የምንልበት ዘመን ሆኗል፡፡ ስጦታ ነገር የሰጠንን ሰው ሁሉ…
“ይሄኔ የሆነ ይሄኔ እነኛ ቅጠል በጣሽ ዘመዶቿ ዘንድ አስተብትባባት ነው…” የምንልበት ዘመን ሆኗል፡፡ ደግ ነገር የተናገረ ሁሉ “አጅሬ፣ ይሄኔ በሆዱ የሆነ ነገር እየደገሰልኝ ነው…” የምንልበት ዘመን ሆኗል፡፡
እናላችሁ… ያለመተማመናችን የደረሰበት ደረጃ… ነገና ተነገ ወዲያ የእግዜሐር ሰላምታችን ሁሉ “ምን ቢያስብ ነው እንዲህ ተሽቆጥቁጦ ሰላም ያለኝ…” ሳያስብለን አይቀርም፡፡
እናላችሁ…ይሄ ያለመተማመናችን ‘እርግማን’ ምንም ነገር በበጎ እንዳናይ እያደረገን ነው፡፡
እንትና አሪፍ ሠራተኛ ነው እንበል፡፡ እናላችሁ…የሆነ ጊዜ እድገት ነገር ያገኛል፡፡ ታዲያላችሁ፣ በደህናው ጊዜ ሲሆን
“እንደውም ሲያንሰው ነው…ምክትል ሥራ አስኪያጅ መሆን ነበረበት፡፡”
“በላይ በላዩ ይጨምርለት…” ምናምን ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ… ‘የጨዋታው ህጎች’ እየተለወጡ ነው፡፡
“ምን! ለእሱ ሰውዬ እድገት ሰጡት ነው የምትለኝ!”
“እድገት ቢሉህ እድገት ነው፣ ደሞዙ እንኳን እጥፍ ሊሆን ምንም አልቀረው…”
“እሱ ሰውዬ እኮ እጠረጥረው ነበር…ከአለቆች ጋር ሳይሞዳሞድ አልቀረም…”
“እንደውም እኔ ላይ ከባድ ዘመድ አለው አሉ…”
“እሱ ሰውዬ አይታችሁት እንደሁ ቀለበቱን ቀኝ እጁ ትንሿ ጣት ላይ ነው የሚያደርገው፡፡ የሆነ ድግምት ሳያስደርግበት አይቀርም…”
እናላችሁ… ሰውየው እውነት በሥራው ታታሪ ነው ወይ፣ የተሰጠው እድገት ይገባዋል ወይ… ምናምን ከማለት ይልቅ…ሃያ ምናምን አጫጭር ልብ ወለዶች ተፈጥረውለት ልፋቱን ሁሉ ገደል እንከተዋለን፡፡ ፡፡ እናማ…ሥራውን በዓይናችን እያያን ሁሉ እድገት ያገኘው በሆነ ተንኮል ነው ብለን እንጠረጥራለን፡፡
እናላችሁ… ያለመተማመናችን፣ እርስ በእርስ የመጠራጠራችን፣ “ደህና የሚባል ሰው ድሮ ቀረ የመባባላችን ነገር የደረሰበት ደረጃ የምር የሚያስደነግጥ ነው፡፡
ጠበቅ አድርጎ መሳምም እኮ ‘ጥርጣሬ ደረጃ አንድ’ ያስከትላል፡፡ “እንዲህ አጥብቃ የሳመችኝ የሆነ ነገር ብትደግስልኝ ነው!” ይባላል እንጂ…አለ አይደል… “ሰሞኑን ስላልተገናኘን ናፍቄያት ነው…” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ እግር መንገዴን…የመሳምን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…
መድረክ ላይ ‘ሮሚዮና ጁሊየት’ እየተሠራ ነው፡፡ እና ጁሊየት ሮሚዮን እየተማጸነችው ነበር፡፡
“ሮሚዮ፣ እባክህ ሳመኝና ቤቴ ልሂድ!”
“አልችልም…”
“እባክህ ሮሚዮ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ሳመኝና ቤቴ እሄዳለሁ፡፡”
“አዝናለሁ፣ ግን አልችልም፡፡”
“ሮሚዮ የእኔ ፍቅር ሌላ ጊዜ አላስቸግርህም፣ አንዴ ሳመኝና ቤቴ ልሂድ!”
ይሄኔ ከተመልካች መሀል አንዱ የተበሳጨ ምን አለ አሉ መሰላችሁ…
“አቦ… ሳማትና ሁላችንም ቤታችን እንሂድ!” አለና አረፈው፡፡
ሮሚዮ ‘የሆነ ተንኮል አስባልኝ ይሆናል’ ብሎ ጠርጥሮ ይሆናል፡፡
እናላችሁ… ያለመተማመናችን፣ እርስ በእርስ የመጠራጠራችን፣ “ደህና የሚባል ሰው ድሮ ቀረ የመባባላችን ነገር የደረሰበት ደረጃ የምር የሚያስደነግጥ ነው፡፡
እናላችሁ… “ባይደርስህ ይሻል ነበር…” የሚል አይነት የጥርጣሬና ያለመተማመንን ‘እርግማን’ የሚያረክስ ብልሀት ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3097 times