Sunday, 07 May 2017 00:00

የጊልጋሜሽ የጀግንነት ገድል

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(0 votes)

ጊልጋሜሽ በደቡብ ምዕራብ እስያ፤ በሜሶፖታሚያ ውስጥ ትገኝ በነበረቺው  የዑር (የዑሩክ) እውነተኛ ንጉሥ የነበረ መሆኑን ከተለያዩ ሰነዶች ለመረዳት ይቻላል፡፡ የጊልጋሜሽ የጀግንነት ገድል ከክርስቶስ ልደት በፊት  በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን  በአሶራውያን ከመጻፉና ከመጠበቁ  በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ዘንድ ለብዙ ዘመናት ይታወቅ ነበር፡፡ በመጨረሻ በ19ኛው ምእት ላይ በተደረገው አሰሳና ጥናት  አማካይነት  የግጥሙ ግማሽ  አካል በሸክላ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ተገኝቷል፡፡ በግጥሙ ውስጥ ጊልጋሜሽ  የሴት አምላክ የሆነቺው የኒንሰን ልጅ ሲሆን አባቱ የዑር ከፍኛ  ቄስ ናቸው፡፡
እናም ጊልጋሜሽ መልኩ ያማረ፤ ቁመቱ የሠመረ፤ ጠንካራና በራሱ የሚተማመን፤ በአስተዳደጉም ኩራትና ትእቢት የተሞላበት ነበር፡፡ ስለሆነም የሚገዛውን ሕዝብ  መጨቆንና በጭካኔ መምራት የዘወትር ልማዱ ነበር፡፡ ሕዝቦቹም ከጭቆናውና ከግፉ የተነሣ ስለጠሉት  ከዚህ ሥቃይ የሚድኑበትን ዘዴ ፈለጉና ለአማልክቶቻቸው ጸሎት አደረጉ፡፡ አማልክቱም የሕዝቡን ጩኸት ስለሰሙ  በጊልጋሜሽ ላይ ጨካኝና አረመኔ የሆነውን የጫካ ሰው ኢንክዱን አሥነሱበትና ጊልጋሜሽ ከኢንክዱ ጋር ለመዋጋት ተገደደ፡፡ በጊልጋሜሽ የጀግንነት ገድል የዋናው ባለታሪክና የጓደኞቹ እጣ ፋንታ የሚወሰነው በሴትና በወንድ አማልክት ነው፡፡
እጅግ ጥንታዊ በሆነው  በጊልጋሜሽ የጀግንነት ገድል ውስጥ ሦስት ሥራዎችን እናገኛለን፡- እነርሱም “ወይን ጠማቂዋ ሲዱሪ”፣ “ወጣት የሚያደርገው አበባ” እና “የሑምባባ አገዳደል” የሚባሉት ትረካዊ ድርሰቶች ናቸው፡፡ ወይን ጠማቂዋ ሲዱሪ በሚለው ድርሰት ዋና የታሪኩ አጠንጣኝ መለኮታዊቱ ሲዱሪ ናት፡፡ ወጣት የሚያደርገው አበባ በተሰኘው  ትረካዊ ድርሰት ዋናው ገጸ ባሕርይ ኡትናፒሽቲም ነው። ኡትናፒሽቲም ዘለዓለማዊ ሕይወት ያለውና  የማይሞት ብልህ ሰው ነው፡፡ የሑምባባ አገዳደል  በሚባለው ትረካዊ ገድል ደግሞ ዋናው ተዋናይ የሴዳርን ጫካ የሚጠብቀው ጨካኙ ፍጡር  ሑምባባ  ነው፡፡
የአሶራውያን ጥንታዊ የጀግንነት ገድል የሆነው ጊልጋሜሽ የተጻፈው በዐሥራ ሁለት የሸክላ ሰሌዳ ላይ ነው፡፡ ትረካዊ ግጥሙ መሬት ውስጥ ተቀብሮ ሲኖር የሥነ የሸክላ ሰሌዳው ከፊል ገጽታ ምድር ተመራማሪዎች (አርኪዎሎጂስቶች) በአካሔዱት ቁፋሮና ምርምር ከዛሬ አንድ መቶ አሥራ ዐራት  ዓመት በፊት የተወሰነውን  ጽሑፍ ከነሸክላ ሰሌዳው  አግኝተውታል፡፡
እናም የወይን ጠጅ ጠማቂዋ የሲዱሪ ታሪክ በዐሥረኛው ቁጥር የሸክላ ሰሌዳ ላይ እንደተገኘ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል፡፡ ይኽንን የጀግንነት ታሪክ ማለት ስለ ወይን ጠማቂዋ ሲዱሪ የሚተርከውን ግጥም ከአሶራውያን ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመው  ዊልያም ሊዎናርድ  ሲሆን እኔም ወደ አማርኛ መልሸዋለሁ፡፡                        
እጅግ ቆንጆና ሸንቃጣ የሆነቺው የወይን ጠጅ ጠማቂዋ ሲዱሪ  ራቅ ከአለ ባሕር ውስጥ የምትኖር የሴት አምላክ ስትሆን ወይን እየጠመቀችና በጽዋ እየሞላች ለአማልክቱ የምታድለው እርሷ ናት። ሁለት አናብስትን አንቆ የገደለው፤ አስፈሪውን የሴዳር ጫካ የመነጠረውና ግዙፉን የጫካ ጠባቂ ሑምባባን የገደለው፤ አፍቃሪና ጦረኛ የሆነው ጊልጋሜሽ አንድ ቀን የጦር ልብሱን እንደለበሰ ሲዱሪ በምትኖርበት ሰፈር በኩል እየተጀነነ ሲያልፍ ያየቺው ሲዱሪ፤ ትልቁን  የምትኖርበትን የቤቷን በር ዘግታ፤ መኝታ ቤቷንም በኃይል ቆልፋ ትቀመጣለች፡፡ ጊልጋሜሽም በድርጊቷ ተገርሞ፤-
“ የወይን ጠጅ ዋንጫውን የያዝሽው ሲዱሪ፤
ኧረ ለምን ይሆን በሩን የዘጋሽው ስትንደረደሪ፤
በዓይኔ አይቼሻለሁ የክፍልሽን መዝጊያ ስትቀረቅሪ፡፡
የተቆለፈውን መዝጊያውን ሰብሬ፡
እኔ እከፍተዋለሁ በትኘ ዘርዝሬ፡፡” ይላታል፡፡
እርስዋም በበኩሏ፤
“ምን ያደርጋል በእውነት  አንጃና ግራንጃ፤
በአውላላ ሜዳ ላይ ጥድፊያና ችኮላ የፈጠነ ርምጃ ---፡፡”
በዚህ ዓይነት ሲዱሪና ጊልጋሜሽ በግጥም እየተመላለሱ ለየራሳቸው ብዙ ታሪክ ይተርካሉ፡፡ በተለይ ጊልጋሜሽ በሴዳር ጫካ ውስጥ ሑምባባን በገደለበት ወቅት በጫካ ውስጥ ያደገውና ተዋጊ የነበረው የልብ ጓደኛው ኢንክዱ ስለፈጸመው ጀብዱ በስፋት ከመተረኩም ባሻገር እንደዚህ ዓይነት ጀግና መሞት እንዳልነበረበት ለሲዱሪ ይነግራታል። ሲዱሪም ከኀዘኑ እንዲጽናናና እንዲረጋጋም ትመክረዋለች፡፡
ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠው ኡትናፒሽቲምም ጊልጋሜሽ የጀግንነት ሥራ ለመሥራት ብሎ አገር ለአገር ከመዞርና ከመንከራተት እንዲቆጠብና በጓደኛው በኢንክዱ ሞት ምክንያትም  እንዳያዝን ይልቁንም ዝም እንዲል ቢመክረውም ፈቃደኛ አልሆን ይላል፡፡ ይልቁንም ጊልጋሜሽ፤  “--- ውዱ ጓደኛየ እኔ የማፈቅረው ሳላስበው ሞቶ፤ ምን ዝም ያሰኘኛል ወደ ዐፈር ሲለወጥ ወደ መሬት ገብቶ ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን በሞት ተረትቼ፤
የማልገባ ነኝ ወይ ከመቃብር ቦታ በሞት ተረትቼ።---”
አለ ለሞተው ጓደኛው ከልቡ  በመቆርቆር፡፡
ወጣት የሚያደርገው አበባ በሚለው ትረካዊ ገድል፣ ኡትናፒሽቲምና ኡርሻናቢ (በሙታን ውኃ ላይ ሲያቋርጥ ጊልጋሜሽ የሚፈራውና ለእርሱም ጽኑ ጥላቻ ያለው መርከበኛ) እንዲሁ ጊልጋሜሽ እንደምኞቱ  ሞትን በመሸሽ አገር ለአገር የሚንከራተት ንጉሥ መሆኑን ስለተረዱ፣ ወጣት ሆኖ ለመኖር   ወደሚያደርገው አበባና ምትሐተኛ ዛፍ መሄድ እንዳለበት ያደርጉታል፡፡ በዚህ ረገድ ጊልጋሜሽና ኡርሻናቢ (መርከበኛው) በባሕር ላይ እየቀዘፉ ወደ ኡር ይጓዛሉ፡፡ ሰማኒያ ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዙ ለማረፍ ፈልገው ይቆማሉ። ምክንያቱም ጨለማው እየመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ቢሆንም መርከባቸውን እያንሳፈፉም ወደ የብሱ ዳርቻ በመድረስ ያርፋሉ። በዐረፉበት ቦታ ላይ ቀዝቃዛ ኩሬና  ንጹሕ ውኃ ነበር፡፡
ንጉሡ ጊልጋሜሽ ከዳርቻው ላይ  እንደ ወጣት የሚያደርገውን አበባ ተመለከተ፡፡ በጣም ከመደሰቱ የተነሣ  አበባውን እያየ በቀዝቃዛ ውኃ ሰውነቱን ለመታጠብና ለዘለዓለም ለመኖር ፈለገና  በኡርሻናቢ ምክር ወደ ኩሬው ወረደ፡፡ ነገር ግን በቀዝቃዛው ውኃ ሥር  እባብ ተኝቶ አበባውን እያሸተተ  ሲበላና  በዛፉም ላይ ሲጠመጠምበት አስተዋለ፡፡ ወዲያው ከእባቡ ገላ (በቆዳ) ላይ ቅርፊቱ ተቀርፍቶ  ሲወድቅ  እንደገና እባቡ (ሟችኙ)  ወጣት ሆነ።
በዚህ ጊዜ ጊልጋሜሽ ተቀመጠና ድምፁን ከፍ አድርጎ  ያለቅስ ጀመር፡፡ “ለዚህ ነው እንዴ ስደክምና  ስጥር የነበረው? የልቤ ምት  በእባብ መርዝ ተቋርጦ  እንዲቆም ነው እንዴ የደከምኩት? ይኼ ለድካሜ ሽልማቴ መሆኑ ነው? ስለዚህ ዘለዓለማዊነት የእኔ  መጨረሻ ሕይወት መሆን የለበትም፡፡ በእጄ ላይ ገና ወጣት የሚያደርገውን አበባ ይዠ ነበር ፡፡---” ብሎ ከኡርሻናቢ ጋር  ወደ ዋና ከተማው ወደ  ኡርተጓዘ። በጉዞ ላይም “መርከቡን እዚህ እንተውና  በየብስ ላይ እንጓዝ፤ የእኔን ታላቅ ከተማ አሳይሃለሁ፡፡ ቢያንስ እዚያ የእኔ ድካም ፍሬ ቢስና ከንቱ አይደለም” አለው፡፡ እንደ ወጣት ሆኖ በመኖር ሌሎች ታላላቅ ሥራዎችን  ለመሥራት አስቦ ከአገር አገር ሲንከራተት የነበረው ጊልጋሜሽ፤ በከተማው ውስጥ በጣም ከፍ አድርጎ የገነባቸውን ታላላቅ ሐውልቶችን፤ ሕንጻዎችንና ቤተ መንግሥቱን ለኡርሻናቢ አሳየው። እነዚህ ሥራዎቹም ስለ እርሱ ታላቅነት ለዘለዓለም ሲመሰክሩ ይኖራሉ፡፡
የሑምባባ አገዳደል  የተሰኘው ትረካዊ ገድል  ስለ  ሰዎች ሕይወትና ሞት ያወጣና ያወርድ ስለነበረው ጊልጋሜሽ ተዋጊነት ያትታል፡፡ ጊልጋሜሽ  እጅግ አስፈሪ ወደ ሆነው ወደ ሴዳር ጫካ ተጉዞ  በጣም ግዙፍ የሆነውን ሑምባባን የጦርነትና የፍቅር አምላክ በሆነቺውና ቤተ መቅደሷ በኡር ከተማ በሚገኘው በኢንሽታር እርዳታ በገደለበት ወቅት ታላቅ እገዛ ያደረገለት በጫካ ውስጥ ያደገውና ተዋጊ የነበረው የልብ ጓደኛው  ኢንክዱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

Read 1495 times