Wednesday, 04 April 2012 09:19

የ“ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ምንቸት…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

ከስንት ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኳስ ግጥሚያ ናፈቀኝማ! ስሙኝማ…ነገ ምናልባት የብሔራዊ ቡድናችንን ሜሲ እናገኝ ይሆናል…! (ልክ ኮለምበስ አሜሪካን አገኘ እንደተባለው ቂ…ቂ…ቂ…) እኔ የምለው…እስቲ ከጀመርነው አይቀር እነእንትና ደግሞ ቢሮ ቁጭ ብለው ‘ውሳኔ የሚያስተላልፉበት ጨዋታ’ ይዘጋጅልንማ! ልክ ነዋ…የቸገረንን የምናውቀው እኛ! ብዙ ነገሮች ‘ጨዋታ’ ይመስሉን ከጀመሩ ከርመዋላ! ያውም ቀሺም ጨዋታዎች!)

ስሙኝማ… ጨዋታም አይደል… የቀበቶ ቀዳዳ እያጠበቡ መሄዱ ስለሰለቸን ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ወዳለውና ወጪ ቆጣቢ ወደሆነ ወደ መቀነት ልንዞር ነው፡፡ ልክ ነዋ… ዕድሜ ለአሮጌ ነጠላ…ጥለቱን እየተረተሩ መቋጠር ነው!

እኔ የምለው…እግረ መንገዴን፣ ማሳጅ ቤቶች…ከዋናው መታሻ በተጨማሪ በህዝብ ጥያቄ ‘ሌላም አገልግሎት’ ትሰጣላችሁ የሚባለው እውነት ነው እንዴ! አይ ጦቢያና ‘ስልጣኔ’!  ልክ እኮ ከምግብ በኋላ “ብርቱካን ምናምን ትፈልጋለህ?” ሲባል “እንክት ነዋ!” እንደምንለው፣ ከማሳጅ በኋላ “እንትን ከፈለግህ ሦስቷን ሳይንቲስት ቁጭ አድርግ!” ምናምን ይባላል አሉ፡፡ እና ከማሳጅ አገልግሎት ጋር ‘በተጠቃሚ ጥያቄ’ ነገርዬውም መኖሩ ፈራንካዋን ለመሰብሰብ ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ አለዋ!

ምን መሰላችሁ… ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ እንደሌለን ወይም ኖሮ ከነበረን እንዳበቃልን የምንጠረጥርባቸው ምልክቶች መኖራቸው እሰየው ነው፡፡ አለ አይደል…“ያ የተነጋገርነውን ነገር ምን አደረስከው…” ስትሉ “ምን መሰለህ፣ አብረን ብንሠራ ደስ ይለኝ ነበር…ግን…”   ከተባላችሁ… በቃ ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታው’ ያለው ሰው ተገኝቷል ማለት ነው፡፡ “ግን…” ያለችባት ነገር ብዙ ጊዜ “ቀሪ ገንዘብ የለዎትም…” እንደሚባለው ነው፡፡

ሌላ ደግሞ አለላችሁ… “ጉዳዩ ያልቅልህ ነበር…ግን የሚፈርም የለም፣” ይባላል፡፡ (በነገራችን ላይ… “ፈራሚ የለም” ማለት…አለ አይደል… “ለማስፈረም የሚያስፈልጉ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮች እንዴት እስከዛሬ አልገቡህም! ያውም እዚቹ ያሁኗ ጦቢያችን ውስጥ ሆነህ!” ማለትም ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ይግባልንማ!) እኔ የምለው… ለጨዋታ ያህል… ብዙ መሥሪያ ቤት ፈራሚ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ልጄ ነገርዬው “ማን ፈርሞ ጥርስ ውስጥ ይገባል!” አይነት ሆኗል፡፡ ነገራችን ሁሉ ቆቅ ለቆቅ አይነት ነገር ይመስላል፡፡ (እኔ የምለው… “ውሳኔዬ ይገለበጣል እንጂ እኔ አልገለበጥ” የሚለው አባባል እስከዛሬ እንዴት እንዳልተለወጠ ይነገረንማ! ይኸው ስንቱ ወንበር ይገለበጥ የለ እንዴ! (እኔ የምለው… ብዙም ሳይቆይ ብዙ ወንበሮች አዳዲስ ‘ተቀማጮች’ ያገኛሉ የሚባለው… ያው የማያልቅው የአዲስ አበባ ‘ጎሲፕ’ ነው እንዴ!)

ስሙኝማ… ድሮ እኮ “ሲኒማ ኢትዮጵያ ብንገባ ምን ይመስልሻል?”  ሲባል  “ደስ ይለኝ ነበር፣ ግን ሰው አለኝ…” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ “ሰው አለኝ”  የሚል ቀርቷል አሉ፡፡ ምን ይደረግ…ሰው አለኝ ማለት መአት በሮች እየዘጋ ‘ስትራቴጂያዊ ጉዳቱ’ ብሷላ!

ስሙኝማ…ጨዋታ ከሆነ አይቀር ይቺን አንድ ጊዜ ያወራናትን ነገር በራሴ ጥያቄ ልድገማትማ፡፡ ምድር ላይ ያለውን ጨርሶ ሰማይ ቤት ሲደርሱ ለትዳር ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ እየታየ መጓጓዣ ይሰጣል አሉ፡፡ እናላችሁ…ሦስት ጓደኛሞች እዛ ይገናኛሉ፡፡

አንደኛው አንዲትም ጊዜ ሌባና ፖሊስ ምናምን ነገር ሚስቱ ላይ ስላልተጫወተ ጄት አውሮፕላን ይሰጠዋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ትንሽ ወዲያ ወዲህ ይል ስለነበር ብዙም ያልተጎዳች መኪና ትሰጠዋለች፡፡ ሦስተኛው ሆዬ ለካላችሁ ዋናውን ቤቱ አስቀምጦ በትርፉ ‘ከተማዋን ያቀልጥ’ ስለነበር ምን ይሰጠዋል መሰላችሁ… ከርካሳ መኪና፡፡

ታዲያላችሁ… አንድ ቀን ባለከርካሳ መኪናው ከሄደበት ሲመለስ ክፍት ብሎት ነበር፡፡ ጓደኞቹ ምን እንደሆነ ይጠይቁታል፡፡ “ሚስቴን ሰማይ ቤት መጥታ አየኋት” ይላቸዋል፡፡ እነሱም “ታዲያ ደስ ይልሀል እንጂ ይሄ ምን ያስከፋል?” ይሉታል፡፡ ምን አለ መሰላችሁ… “አሮጌ ቢስክሌት ስትነዳ አየኋት!” የባሰ አታምጣ ማለት እንዲህ ነው! ዘንድሮ ብዙዎቻችን አይደለም አሮጌ ብስከሌት አሮጌ ጫማም ማግኘታችንን እንጃ!

የስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ጊዜ ሆኗላ! አብዛኛው የ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ የሚገለጸው ተቀምጦ ሳይሆን ጋደም ብሎ ሆኗላችኋል፡፡ እኔ እኮ ይሄ “ወተር ቤድ” ምናምን የሚሉት የ‘ፈርኒቸር ቢዙ’ ለምንድነው እንዲህ የጦፈው! ስፖንጁ ሰለቸና ነው እንዴ ነገርዬው ‘ወተር’ ላይ የተጀመረው! እንትና ዋጋው መቶ ስንት ሺህ ብር ነው አልከኝ!)

እናላችሁ… በፊት እኮ ጎረቤት እየተጠራራ ቡና ይጣጣ ነበር፡ዘንድሮ ልጄ ቡና መጠጣቱም ከስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ጋር ተያይዞላችኋል፡፡ ደግሞላችሁ… ቡና የምንጠጣ መስለን ሰው ቤት ገብተን የቤት ውስጥ ወንበርና ምናምን የምንቆጥር በዝተናላ! ልጄ…ተከራይ ሁሉ ቤቱ ከገባ በኋላ በሩ ላይ “ታሽጓል!” ምናምን ለመጻፍ ምንም የማይቀረው… “ቤት ለእንግዳ” ማለት ስትራቴጂያዊ ጉዳቱ እየበዛ ነዋ!

ደግሞላችሁ… እጥፍ ዘርጋ ብሎ ሰላም ይላችሁ የነበረው ሰው በሚያስደነግጥ ሁኔታ ድንገት ‘ይቀረቅራችኋል’፡፡ በቃ ከእናንተ ጋር መወዳጀቱ ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ሳይኖረውስ! “በፊት እኮ አንድ ቦምቦሊኖ ለሁለት እንበላ ነበር…” “ብር ተሀምሳ ይዘን ጣልያን ሰፈር አብረን ነበር የምንሄደው” ምናምን የሚል ‘ትዝታ በፖስታ’፣ ‘ዘ ጉድ ኦልድ ታይምስ’ ምናምን ነገር አይሠራም፡፡ ዋናው ነገር…“ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታና ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ” ብቻ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…

ለምሳሌ በፊት የፈረንጅ ቤት ሠራተኛ መያዝ ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ነበረው፡፡ አሀ…የ‘አሮስቶ ዲቢቴሎ’ ምናምን በፌስታል ተጠቅልሎ ይመጣላ! (‘አሮስቶ ዲቢቴሎ’ የሚባል ምግብ አለ አይደል! አሀ… እንኳን ጣልያንኛው አማርኛው ‘ኤስፔራንቶ’ ምናምን ነገር እየሆነብን ነው!)

ስሙኝማ…የ‘ፈረንጅ’ ነገር እንደገና ካነሳን አይቀር…በፊት እኮ “ዋሺንግተን ወንድም አለኝ” “ለንደን የአክስቴ ልጅ አለች…” “ዘመዶቻችን በሙሉ አውሮፓና አሜሪካ ናቸው…” ምናምን ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ነበረው፡፡

ዘንድሮ እነዋሺንግተን በተለያየ መንገድ እዚሁ መጡና ነገርዬው ተበላሸ መሰለኝ፡፡ አሁን እኮ ለጉብኝት የሚመጡ ‘ዳያስፖራዎች’ን ዶላርና ፓውንድ ማጫረሳችን ቀርቶ በዚቹ በ‘ጦቢያዋ ብራችን’ ጋባዥ እኛ እየሆንን ነው፡፡ አሀ… አሁን፣ አሁን የሚመጡት እዛው ‘ተጫርሰው’ ነዋ! (በነገራችን ላይ…ዳያስፖራ ምናምን ካልን… እነኚህ በኢሚግሬሽንና ካዛንቺስ አካባቢ የሚሰበሰቡትን ሺዎች ወጣት ሴቶች አይቶ ሚዲያ ላይ የሆነ ‘ብሩህ ቀለም’ ምናምን ለመቀባት ሲሞከር ስትሰሙ ትንሽ ግር አይላችሁም! ከትናንሽ ገጠር ቀበሌዎች ሁሉ መከራቸውን እያዩ የሚተሙት እኮ አገራቸው ዕድል ስላልሰጠቻቸው ነው፡፡ አለቀ—ይኸው ነው፡፡ አያስፎክርም፣ ያሳፍራል እንጂ!)

ስሙኝማ… እንግዲህ ስለ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ እያወራንም አይደል… ዘንድሮ ብዙ መሥሪያ ቤቶች ቅጥር የሚካሄደው በሙያ ሳይሆን በ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ነው የሚል ‘ጎሲፕ’ ምናምን ነገር አለ፡፡ በተለይ ‘ቦተሊካ’ና የ‘መንደር ልጅነት’ የመስፈርቱ የ“ሽፋን ገጽ” ነገር እየሆነ ነው ይላል ‘ጎሲፑ’፡፡ (ስሙኝማ…እንደው ስታስቡት በ‘ጎሲፕ’ ዓለምን የምንመራ አይመስላችሁም!)

ዘንድሮ ለምሳሌ የሆነ ሰው እንትናዬ ላይ ጆፌ ሲጥል….እንደ ድሮ “በደረቁ ሌሊት ታስለፈልፋለች…” ምናምን አይሠራም፡፡ (ደግሞ ዘንድሮ ስንት የሚያስለፈልፈን ነገር ሞልቶ!) “ላይ ያሉ ባለስልጣኖች ታውቃለች!”  “ከሀብታሞች ጋር ነው የምታመሸው…”  ነገር ሆኗል፡፡ በተረፈ ከእንትናዬ ለሚገኘው ‘መደበኛ ነገርዬ’ እንደ ድሮው ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ምናምን ቀርቷል፡፡ መለፍለፍ ማለት እንዲህ አይደል!  ቂ…ቂ…ቂ…

ደግሞላችሁ…  ሰው ተወዳጅቶ የሚራራቅበትን ፍጥነት ልብ ብላችሁልኛል! እናላችሁ… ነገሩ ሁሉ እንደ እህል በረንዳ ዋጋ ዛሬ ያደረው ነገ የማይገኝበት አይነት እየሆነ “አንተ፣ ያ ጓደኛህ ደህና ነው!” ምናምን ማለትም እያሳቀቀን ነው፡፡ ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ጓደኝነትን እያፈረሰ ነዋ!

ደግሞላችሁ… ድሮ  ‘ማሬጅ’ ምናምን እንኳን … አለ አይደል… “አባቷ መአት ጋሻ መሬት አላቸው…” “ከብት ማድለቢያ አላቸው…” ምናምን ነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ “መሬት አላቸው…” ምናምን ነገር ቀርቷል፡፡ (መሬት! የምን መሬት! ቂ…ቂ…ቂ…)

የ‘ቦተሊካ’ ነገርማ… ምን አለፋችሁ… ወላ መሬት ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል ያለስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አትሆንም፡፡

(ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አንድ ሰው ‘ቦተሊካ ሲጀማምረው’ ከ‘ብሬይን’ የሆኑ ቡሎኖች ጠፍተው… አለ አይደል… ልክ የሆነ ከባዶ አየር ላይ ‘ዳውንሎድ’ የሚደረግ ሶፍትዌር የቡሎኖቹን ቦታ የሚይዝ ይመስለኛል፡፡ እናማ… “አንተ ያ እንትና ምንድነው ጠባዩን እንዲህ እንደ ጦቢያችን ኳስ መላ ቅጡን ያሳጣው?” ሲባል… መልሱ ምን መሰላችሁ… “እባክህ ቦተሊካ ሳይጀማምረው አይቀርም” አይነት ነው፡፡ እናማ … ‘ቦተሊካ’ ፈልገን የምናገኘው ሳይሆን እንደ ‘በርድ ፍሉ’ ምናምን ፈልጎ ‘ድንገት የሚይዝ’ ነገር እየመሰለን ተቸግረናል፡፡)

እናማ… የ‘ሊበራል’፣ ‘ኮንሰርቫቲቭ’፣ ቅብጥርስዮ ዛር ሲሰፍርብን ሰው መሆን እናቆምና የሦስተኛው ዓለም ‘ቦተሊከኛ’ እንሆናለን፡፡

የእነ ‘ሊበራል’፣ ‘ኮንሰርቫቲቭ’ ቅብጥርስዮ ምናምን ነገር የፖሊሲ ምናምን ነገር ሳይሆን የ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ጉዳይ ሆኗላ! (ጥያቄ አለን… አንድ ሰው በሦስተኛው ዓለም ‘ቦተሊከኛ’ ሲሆን አንደበት ሰጥቶት ‘ማገናዘቢያ ኩላሊቱን’ የሚወስድበት ምንድነው!)

እናላችሁ… እነኚህ በሪሞት ኮንትሮል የሚቆጣጠሩንና ልንሰማ የምንፈልጋቸውን ነገር በጆሮ በጆሯችን የሚለቁልን ‘አሳዳሪዎቻችን’ አገሮች እኮ የእኛ ፍቅር አናታቸው ላይ ወጥቶ ምናምን ሳይሆን ዋናው ዓላማቸው  ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ነው፡፡

እናላችሁ… የ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ዘመን ሆኖላችኋል፡፡ “አይ የሰው ነገር!” “አይ የዘመን መበላሸት!” “ምን አለ በሉኝ፣ ስምንተኛው ሺህ የእውነትም ጫፉ ላይ እየደረሰ ነው!” ምናምን ለምንለው ነገር ሁሉ ዋናው መነሻ ምን መሰላችሁ…‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ!’ እናላችሁ የ“ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ምንቸት…” ከእነ አሰስ ገሰሱ ገብቶላችኋል፡፡

የ‘ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ’ ዘመን…ሰው የሚያደርጉን መለያዎችን ሙሉ ለሙሉ አሟጦ እንዳይጨርስብን ይጠብቀንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

Read 1892 times Last modified on Friday, 06 April 2012 11:19