Sunday, 07 May 2017 00:00

እኔና አሰፋ ጫቦ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 (ካለፈው የቀጠለ)
                   ‹‹ወዳጄ›› ይለኝ የነበረ ሰው አለፈ!!
                  

     (ካለፈው የቀጠለ)
‹‹ወዳጄ›› ይለኝ የነበረ ሰው አለፈ!!
ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ፤ አሰፋ እና እኔ ማዕከላዊ እሥር ቤት ውስጥ እንኖር እንደነበረ፤ ተርኬላችኋለሁ፡፡ ከዚያው ልቀጥል፡፡-
አሰፋ ትዝታው አያልቅም፡፡ አሰፋ ካለው ባህሪ አንዱ፣ አጠገቡ ካለ ሰው ጋር ጨዋታ መፍጠር ነው። በዚህም ምክንያት የእኛ ቤት አባል ከሆነ ሰው ጋር ከእኛ ቀድሞ ይተዋወቃል፤ ያወራል፣ ይጫወታል፡፡ የልባቸውን ይነግሩታል፡፡ ሲፈልግ ይተርባቸዋል፡፡ ሲፈልግ የሒስ መዓት ያወርድባቸዋል፡፡
እኛ ክፍል አባ ደመረ የሚባሉ እሥረኛ አሉ። አጭር፣ ሽበታም፣ ጨዋታ አዋቂ ናቸው። የታሠሩት በሚገርም ሁኔታ ነው፡፡ እንዲህ ነው፡- ወንድማቸው ጡረታ ሚኒስቴር የሚሠሩ ሰው ናቸው፡፡ እሳቸውን  ለመጠየቅ አባ ደመረ ወደ ጡረታ ሚኒስቴር የወንድማቸው ቢሮ ይሄዳሉ፡፡ ለካ ወንድማቸው (በደርግ ጊዜ ነው) በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት (ኢዲዩ) ፓርቲ አባልነት ይጠረጠሩ ኖሮ ሊታሠሩ ይፈለጋሉ፡፡ ስለዚህም ቢሮአቸው ተከበበ፡፡ አባ ደመረ ከወንድማቸው ጋር ውስጥ ሆነው ቡና እየጠጡ ይጨዋወታሉ፡፡
የአባ ደመረ ወንድም ያለ አንዳች ጥያቄ ታሠሩ፡፡ ቀድሞውኑ ተጠርጥረው ስለነበር፡፡ አባ ደመረ ግን እንደ አዲስ ተጠርጣሪ ታስበው ተፈተሹ፡፡ ፍተሻው ጦሰኛ ሆነ፡፡ አባ ደመረ በኪሳቸው የዕለት ፀሎት የሚያደርሱበት ከደረት ኪሳቸው በውስጥ በኩል የሚይዙት ዳዊት ኣላቸው፡፡
ፈታሾቹ፤
‹‹ዳዊቱንም በርብረው›› አሉ፡፡ ዳዊቱ ተበረበረ።
ዳዊቱ ውስጥ አንድ ብጣሽ ወረቀት ተገኘች፡፡ ‹‹ይሄ ምንድነው?›› አለ ፈታሹ፡፡
‹‹ግጥም ናት፤ ከሬዲዮ ሰምቼ የፃፍኳት ናት!
‹‹እስቲ አምጣው፡፡ ብሎ አነበበው፡፡
‹‹ጀበናው ተጥዶ ሲኒው ሲኩነሰነስ
ባሪያው ሰው ጨረሰ አሰፋ ወሰን ድረስ!››
እረረረ! ይሄማ ዋናው ፀረ-አብዮተኛ ነው አስገባው›› ብለው ወደ መኪናው አስገብተው፤ ይዘዋቸው ማዕከላዊ መጡ፡፡  እንዳጋጣሚ እኛ ክፍል ገቡ፡፡ በነጋታ ለምርመራ ተጠሩ፡፡ እኔና አሰፋ ጫቦ ቁጭ ብለን ስናወራ ተመልሰው መጡ፡፡
‹‹ምን አሉዎት?›› አላቸው አሰፋ
‹‹ኢዲዩ ነህ ዕመን አለኝ››
‹‹ምን አሉት እርሶ?››
‹‹አይደለሁም! አልኩ፡፡ ‹ቆይ አሳይሃለሁ› ብሎ ወደ አንድ መግረፊያ ክፍል አስገብቶ፣ እነዚህን የታሠሩ ሰዎች ተመልከት አለኝ…፡፡ ውነትም ምን የሚያካክሉትን ግዙፍ ግዙፍ ሰዎች፣ ልጅ አሳክለው አሥረው ይደበድቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጠየቀኝ፡-
‹‹አሁንስ፤ አታምንም? ኢዲዩ ነህ?› አለ
‹‹በመንፈስ… አዎ!› አልኩት››
ይሄኔ አሰፋ ሳቀና፤
‹‹አባ ደመረ ታድለዋል፤ ሁለት ዓይነት ዕምነት ይዘዋል፤ የመንፈስና የሥጋ፡፡ እኛ አንዱን ብቻ ይዘን እኮ ነው መከራችንን የምናየው›› አለኝ፡፡
አሰፋ ጫቦ አንድን ነገር መናገር ሲሻ በጣም ባጭሩ ነው የሚገልፀው፡፡ ነገርን ጥቅልል አድርጎ መግለፅ ይችላል (Summarize ወይም paraphrase እንደሚሉት ፈረንጆቹ) ያውም በአማረ-ወግ /ውስጡ- ወይራ (Wit) ጋር፡፡ አንዲህ ያለው ችሎታ፤ ጥበብና ጭንቅላት ይጠይቃል። ፍጥነት ይጠይቃል (an athlet in the mind የሚሉት አይነት) አሰፋ ይሄ ሁሉ የተሰጠው ሰው ነው!
አንድ ጊዜ በግቢው (በማዕከላዊ ምርመራ ድርጅት እሥር ቤት) ያለ የሌለው ስለት ያለው ነገር ሁሉ…. (እንደ ምሥማር፣ ሽቦ…. ያለ ነገር ማለት ነው) ይውጣ ተባለ፡፡ የልብስ መስቀያ ምሥማሮቻችን ሁሉ ተወሰዱ፡፡ አሰፋ ከዘበኞቹ፤ ከጠባቂዎቻችን ጋር ይስማማል፡፡ በተለይ ከጋሞ ልጆች ጋር፡፡ በጋሙኛ ያናግራቸዋል፡፡
ስለዚህ ይመስለኛል አንድ ትንሽ፤ እጀታ የሌለው ቢላ ነበረው፡፡ ብርቱካን በዚያ እየቆረጠ ነበር የሚበላው፡፡ ግቢው ውስጥ ባለሥልጣን ነን የሚሉ ካድሬዎች፤ ‹‹አሰፋ ቢላ አለው፣ ስለት አለው›› ብለው ጠቆሙበት፡፡ የአስተዳደር ሰዎች መጥተው፤
‹‹ቢላ አለዎት ተብሏል አስረክቡ›› አሉት፡፡
‹‹አልሰጥም›› አለ አሰፋ፡፡
‹‹ለምን?››
‹‹ሻምበሉ ጋ አቅርቡኝና ላስረዳ›› ይዘውት ሄዱ።
አሰፋ ደፋር ነው፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ አዛዥ ኮሎኔል አረጋው እሸቴ ነበሩ፡፡ አሰፋ አገር ግዛት (አስተዳደር) በምሠራ ጊዜ አርጋውን አውቀው ነበር ይለኛል፡፡ ስለዚህ አሁን አልፎ አልፎ ኮሎኔል አርጋው ቢሮ ድረስ ሄዶ አቤቱታ ያቀርብ ነበር፡፡
ይህ ሁኔታ የእሥሩ ቤቱ አስተዳደር ሻምበል አሰፋን እንዲፈራው ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም አሰፋ ንግግር አዋቂ ስለሆነ ሁኔታውን ተጠቅሞ ማስፈራራቱን ችሎበት ይሆናል፡፡ እንግዲህ ‹‹ቢላ አለህ አስረክብ›› ተብሎ አሰፋ የቀረበው እዚህ ሻምበል ዘንድ ነው፡፡
‹‹ አቶ አሰፋ፤ ለምንድን ነው ሌላው እሥረኛ ሁሉ ስለት ያለው ነገር ሲያስረክብ፣ አንተ እምቢ ያልከው?››
አሉ ሻምበሉ፡፡
አሰፋም፤ ‹‹ለምን ስለት አምጡ እንደምትሉ ማወቅ እፈልጋለሁ›› አለ ፍርጥም ብሎ፡፡
ሻምበሉ ማስረዳት ጀመረ፣
‹‹ምን መሰለህ አቶ አሰፋ፤… እሥረኛ ብስጩ ነው፡፡ የእስር ጊዜው ሲረዝም፣ ወይም ምርመራው ሲበረታበት፣ ወይም ማስፈራራትና መገረፍ ሲያጋጥመው ይጨነቃል፡፡ ስለዚህ አጠገቡ ስለት መሳይ ነገር ካገኘ፣ በዚያ ራሱን ሊያጠፋ ይችላል…።›› እያለ ሊቀጥል ሲል አሰፋ ያቋርጠውና፣
‹‹እንዴ ሻምበል! እኛ ኮ እናንተ ትገድሉናላችሁ ብለን ነው የምንሰጋው፡፡ ጭራሽ እራሳቸውን ይገድላሉ ብላችሁ እኛኑ ነው እንዴ የምትጠረጥሩን?!›› ይላል፡፡
ሻምበሉ፤ ‹ዎዎ! ይሄ ሰው ዕብድ ነው ወንድሜ፤ ወደ እሥር ቤቱ መልሱት›› አለ፡፡
አሰፋ የብዙ ጊዜ ንባብ፣ የተጠራቀመ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ይሄ በንግግሩ ውስጥ፣ በነገር-አዋቂነቱ ውስጥ፣ ይንፀባረቃል፡፡ ጨዋታ ይችላል። ከሚግባባው ሰው ጋር በኮስታራ ጉዳይ ላይም መቀለድ ይችላል፡፡ ዛሬ ህይወቱ አልፏል። ከእነዕውቀቱ ከእነነገር አዋቂነቱ፣ ከእነቀልዱ የአገሩን አፈር ቀምሷል፡፡ አሰፋን ካለ አገር ጉዳይ ማስታወስ አይቻልም፡፡ የአገር ጉዳዮቹ ደግሞ ሰው ሰው የሚሸሸቱ አሉባቸው፡፡ እነሱን የማነሳው አንባቢ ሙሉውን አሰፋ ያገኝ ዘንድ ነው፡፡ አሰፋም በህይወት ቢኖር የሚያነሳቸው ይመስሉኛል፡፡
አንድ ጊዜ አስተዳዳሪው ሻምበል ያስጠሩኝና፤ ‹‹ስለዲያሌክቲካዊ ቁስ አካልነት እንድናጠና ታዘናል፡፡ (በዚያን ጊዜ እያንዳንዱ ሻምበል በሥሩ ሃያ ሃያ ሰዎችን ስለ ማርክሲዝም እንዲያስተምር/ እንዲያነቃ ታዞ ነበር፡፡ ሻምበልም በኃላፊነቱ ለማንቃት መንቃት ነበረበትና የተሰጠውን ወረቀት ለማንበብ ሞክሮ ዳገት ሆኖበታል፡፡) ስለዚህ ነው እኔን አስጠርቶ የሚያናግረኝ፡፡
‹‹ስማ ነቢዩ፤ እናንተ እሥር ቤት ስለሆናችሁ ብዙ ጊዜ አላችሁ!! ስለዚህ ታነባላችሁ፡፡ ለመሆኑ ይሄን ቁስ አካል የሚባል ነገር ያመጣብን ማነው?›› አለ ምርር ብሎ፡፡ ወረቀቱ ላይ አንድ አሥራ ስምንት ቦታ ቁስ አካል የሚለው ላይ በቀይ ተሰምሮበታል፡፡ በሆዴ እየሳቅሁ፤ ላስብበት ብዬ ወጣሁ፡፡ ከቢሮ እንደወጣሁ አሰፋ ግቢው ውስጥ ሲንጎራደድ አገኘሁት፡፡ የሚጥል በሽታ (Epleptic) ነበረበትና  በ‹‹በሀኪም›› ትዕዛዝ ንፋስ እንዲያገኝ ተፈቅዶለታል፡፡ ብዙ ጊዜ ዘወር ዘወር ይላል ብቻውን፡፡ በኋላ አንደኛውን የግቢያችን ካቦ ሆኖ ደጅ የመቆም ዕድል እስኪያገኝ ድረስ ማለት ነው፡፡
‹‹እህ ነቢይ ሻምበል ቁጩ ምን አለህ?›› (እኛ ለሻምበሉ የሰጠነው ቅፅል ስም ነው (ሻምበል ቁጩ›)
‹‹ይሄን ቁስ አካል የሚባል ነገር ማነው ወደ አገራችን ያመጣው? ይለኛል››
አልኩት፡፡
አሰፋም ፈጠን ብሎ፤
‹‹አሃ ደሞ ይሄ ጠፋህ እንዴ?!ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ናቸው አትለውም እንዴ?!›› አለኝ፡፡ ተሳሳቅን፡፡
አሰፋ ውግ- ያለው ቀልድ አያልቅበትም ነበር። ከነውግ-ያለው ቀልዱ አልፏል- ዛሬ፡፡ አፈር ይቅለለው፡፡
አሰፋ ‹‹ወዳጄ ነቢይ›› ይለኝ የነበረ ወዳጄ ነበር። ዛሬ የለም፡፡ የአንድ ጥሩ ድርሰት ያህል ይጥመኝ የነበረው ደብዳቤው ዛሬ የለም፡፡ እንደ ሙዚቃም፤ እንደ ቃለ-ተውኔትም አዳምጠው የነበረው ድምፁ ዛሬ የለም፡፡ ክላሲክ ልብ-ወለዶች ይተነትንልኝ፣ ያወያየኝ የነበረው ሰው ዛሬ አፈር ቀምሷል፡፡ ዕውቀት ሲርቅ ለአገር ደግ አይደለም፡፡ ስደት ሰውን ያደበዝዛል፡፡
እድሜ ለብዕሩ! አሰፋ ግን አልደበዘዘም፡፡ እንዲያውም ገና በቀለሙ እየወዛ ይሄዳል፡፡ ከዱሮ ጀምሮ ‹‹ትምህርትህን ይግለጥልህ!›› እየተባባልን እንመራረቅ ነበር፡፡
የወዳጄን የአሰፋን ለዛ ነገም እነቁጣለሁ፡፡ መታወሱ ለአገር ተገቢ ነውና! የብዕር ጀግና ነውና!
እኔና አሰፋ እሥር ቤት ሆነን ደጋግመን በቃል ስናነበንበው የነበረውን የመንግሥቱ ለማን ግጥም- ‹‹የአንበርብር ጎሹ ሞት›› የተሰኘውን፤ እዚህ ጋ ለአሰፋ መሸኛ መጥቀስ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም፡፡ እዚያው በተኛበት ያድምጠኝ፡- ይቀሰቅሰዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
የአንበርብር ጎሹ ሞት
እስቲ ላነሳሳው፤ አንበርብር ጎሹን
በደራ አደባባይ፣ የወደቀውን፡፡
እሱስ ሆኖ አይደለም፤ ታሪከ-ቅዱስ
መፅደቋንም እንጃ፣ ያች የአንበርብር ነብስ!
የሚያዘወትራት፣ የአንበርብር ወዳጅ
ነበረችው አንዲት፣ ጠይም ቆንጆ ልጅ
ሴትኛ አዳሪ ናት፣ እሱም አላገባ
ቀሳሚው ቢበዛም ይህቺኑ አበባ
አያ ማር ወለላ፣ አያ ማር እሸት
እሱ ብቻ ነበር፣ የእሳቲቱ እራት!
ቢወጣም በጠዋት፣ ቢገባም በሌት
በር ይመታል ሲያውቀው፣ እንዲከፍቱለት፡፡
አንድ ቀን አምሽቶ፣ ደጃፉን ቢመታ
ወይ የሚለው አጣ፣ ገጠመው ዝምታ
ሂድልኝ አለችው፣ ሰጠችው መልሱን
ሌላ ሰው ወርሶታል፣ የሱን ቦታውን
እሱም ተበሳጭቶ፣ ነዶት መረቃት
ለንጉሡ ተመኛት፤ ለዚያን ቀን ሌሊት
ይሄውም ሆነና፣ ዋንኛ ጥፋት
ከዳኛ ፊት ቢቀርብ ፣ ወዲያው በማግሥቱ
አርባ ጅራፍ ሆነ፣ ህገኛ ቅጣቱ!
ሞራ ሲጠጣ ነው፣ የዋለው ጅራፉ
ግን አላርፍም አለ፣ የገራፊው አፉ!
‹‹ዐይንህን ተጠንቀቅ፣ ወንድም አደራህን
እንዳላጎልብህ፤ በከንቱ አካልህን!››
ምፀቱ ገደለው፣ እዚያው ግጥም አለ
ጅራፉም ዕድሜውም፣ ሰላሣን ሳይሞላ!
ከተሰበሰቡት፣ ከተመልካቾቹ
የልብ ድካም ነው፤ አሉ አብዛኛዎቹ
ፈላስፎቹም፤
ለሰው መጥፊያው ሴት ነች አሉ
አቤልን አነሱት፣ ተዝካሩን ሲበሉ!
ኧረ ስንቱ … ስንቱ፣ ናቸው የሞቱቱ
ለንጉሣቸው ክብር፣ ለባንድራይቱ!
(ይሄን እየፃፍኩ የአሰፋ ጫቦ አስከሬን (ሐሙስ ለታ ኤርፖርት እየመጣ ነው- ተብሎ እየጠበቅን ነው፡፡ ህያው ሸኝቶ አስከሬን መቀበል ይከብዳል! ሆኖም የኢትዮጵያ ዕጣ-ፈንታ ከሆነ ቆይቷል፡፡) የናፈቀውን አገር ሳያይ ያለፈውን ወዳጄን ነብሱን ይማረው!
(ይቀጥላል)

Read 1904 times