Print this page
Saturday, 06 May 2017 09:58

የሜሪ ጆይ ፕሮጀክት - የአረጋውያን ማዕከላት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   · “ይሄ ማዕከል ተሰርቶ በነጋታው በሞትኩ” (አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ)
                      · “በሁሉም ከተሞች የአረጋውያን ማዕከላት ይገነባሉ”

          ሜሪ ጆይ የልማት ማህበር የዛሬ 8 ዓመት የአረጋዊያን ሁለገብ አገልግሎት ማዕከል ለመገንባት በሀዋሳ ከተማ 6 ሺህ ካ.ሜ ቦታ የተረከበ ሲሆን በ2003 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ዘንድሮ ተጠናቅቋል፡፡ የምረቃ ስነ-ስርዓቱ በመጪው ግንቦት 12 ይካሄዳል ተብሏል፡፡ የዛሬ ሁለት ሳምንት ቅዳሜ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ የድርጅቱ መስራችና ዋና ዳይሬክተር ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ፣ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል፡፡
   በስፍራው የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ስለ ማዕከሉ ግንባታ አጠቃላይ ሂደት፣ ለአረጋውያን ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ በድሬደዋና በአርባ ምንጭ ሊገነቡ ስለታቀዱት የአረጋዊያን ማዕከላትና ተያያዥ ጉዳዮች
አንስታ ሲስተር ዘቢደርን አነጋግራቸዋለች፡፡

    ማዕከሉን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜና ገንዘብ ወሰደ?
በጎ ፈቃደኞች በሙያቸው የለገሱትን ገንዘብ ሳይጨምር 12.5 ሚ. ብር ወስዷል፡፡ የህንፃ ዲዛይኑን አርክቴክት አሰፋ ገበየሁ በነፃ ነው የሰሩልን። በወቅቱ በነበረው ገበያ ዲዛይኑ 350 ሺህ ብር የሚያወጣ ነበር፡፡ ህንፃው ተጀምሮ እስኪያልቅ የክትትልና የማማከር ስራውን ለ6 ዓመት የሰሩልን ወጣቶች፣ MDC የተባለ የህንፃ ስራ አማካሪዎች ናቸው፡፡ ስራ አስኪያጁ ዳዊት ይባላል፡፡ እነዚህ ልጆች ከማማከር ባለፈ የግንባታ እቃ ሲያልቀብን ከራሳቸው እያቀረቡ በነፃ ሲረዱን ቆይተዋል፡፡ የእነዚህ ልጆች እገዛ በገንዘብ ሲሰላ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል። የሀዋሳ ከተማ የግንባታ እቃ ባለ ሱቆች፣ከሴራሚክ ጀምሮ የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገውልናል፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን፣ አርቲስቶች፣ ባለሀብቶችና ባለሙያዎች እገዛ ባይጨመርበት ኖሮ፣ አጠቃላይ ህንፃው ከ20 ሚ. ብር በላይ ይፈጅብን ነበር፡፡ ማእከሉ ከሚለይባቸው ዋናውና አንዱ በኢትዮጵያዊያን መገንባቱ ነው። በዚህ የብዙ ኢትዮጵያዊያን አሻራ ባረፈበት ህንፃ መጠናቀቅ የብዙ ሰዎች ደስታ ተገልጿል፡፡ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያትን አሳልፈን ነው ያጠናቀቅነው፡፡
ማዕከሉ ለአረጋዊያን መጠነ ሰፊ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡ እስቲ ዋና ዋናዎቹን ይንገሩን …
ከመጀመሪያው ጀምሮ ማዕከሉን ለመገንባት ስንነሳ፣ አንድ አረጋዊ ምን ያስፈልገዋል የሚለውን አጥንተን ነው፡፡ ስለዚህ የተሟላ ክሊኒክ አለው፡፡ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፤ ለዚህም ካፍቴሪያ አላቸው። ቤተ መፅሀፍት፣ ኮምፒዩተር ላብ፣ ዶክሜንቴሽን ማዕከል፣ ጌም ሴንተር፣ ቴሌቪዥን መመልከቻ ክፍል አለው፡፡ ሲደክማቸው የሚያርፉበት የወንድና የሴት ክፍሎችም አሉት፡፡ ብቻ አንድ አረጋዊ ያስፈልገዋል ተብሎ የሚታሰበው ነገር ሁሉ ተሟልቶለታል፡፡
የማዕከሉ ክፍሎች በተለያዩ ባለሀብት ድርጅቶች ስም የተሰየሙበት ምክንያት ምንድን ነው?
እንግዲህ “50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ነው፤ ለ50 ሰው ጌጡ ነው” ይባላል፡፡ እኛም ህንፃው ተገንብቶ ራዕያችን እንዲሳካ፣አንድ ሰው ወይም አንድ ድርጅት ገንዘብ እንዲሰጠን ከማስጨነቅ፣  የተለያዩ ባለሀብቶችና የሀዋሳ ከተማ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስም በመሰየም ክፍሎቹን በገንዘብ እንዲደግፉ ነው ያደርገነው፡፡ ለምሳሌ ጂምናዚየሙን  - ይርጋለም ኮንስትራክሽን፣ ሻወር ቤቱን - ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኙ የማሪያም ማህበርተኞች (በአምስት ሺህ ዶላር)፣ ሴራሚኩን - የሀዋሳ ከተማ ሴራሚክ ሱቆች፣ ሰርቶ ማሳያውን አንዱን ክፍል - ንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ፣ ሌላኛውን አንበሳ ጫማ፣---- ስፖንሰር አደረጉ፡፡
በሌላ በኩል ሁለቱንም የማረፊያ ክፍሎች፣ ናርዶስ ወ/ሰንበት የተባለች ዱባይ የምትገኝ ባለሀብት፣ ሱቁን - የጂት መቻል የተባለ የሀዋሳ ነዋሪ፣ በሱቁ አንዳንድ ነገር ለሚሰሩበት ሶስት ሲንጀርና 32 ሺህ ብር - አበባ የተባለች ግለሰብ ለግሳለች፡፡
ክሊኒኩን ሃዋሳ የሚገኘው ያኔት ሆስፒታል ስፖንሰር አድርጓል፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን በሆስፒታሉ ያሉ ስፔሻሊስቶች፤ አረጋዊያንኑን እዛው ወስደው ሊያክሙልን ቃል ገብተዋል፡፡ አለነታላንድ የተባለው የንግድ ድርጅት - መታሻ ክፍሉን፣ ጁፒተር ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ - አንዱን መታሻ ክፍል፣ ታካሚዎች ቁጭ ብለው ህክምና የሚጠብቁበትን ክፍል - ዋሪት ሙሉ ጥላ (አቶ ለገሰ ዘሪሁን) ስፖንሰር ሲያደርጉ፣ ሎቢውን በ360 ሺህ ብር ዮድ አቢሲኒያ አድርገውታል፡፡ ኢታብ ሳሙና በ260 ሺህ ብር - ካፍሬቴሪያውን ስፖንሰር አድርገዋል፤ የማናጀሩ ቢሮ፣ የፀሀፊው፣ የበጎ ፍቃደኞቹ ቢሮና ሌሎችም በስፖንሰሮች ተሰርተው በስማቸው ተሰይሟል፡፡ አጥሩን እንኳን የከተማው ከንቲባ ፅ/ቤት ነው፣በ900 ሺህ ብር ያጠረው፡፡ ግቢውን እያስዋበ ያለውም የከተማው ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ ጋትስ አግሮ ኢንዱስትሪ፤ቤተ መፅሀፍቱን ስፖንሰር ሲያደርጉ ሌዊ ሪዞርት በበኩሉ፤ ኮምፒዩተር ላቡንና ዶክሜንቴሽን ክፍሉን ስፖንሰር አድርጓል፡፡ ብቻ በአጠቃላይ ለዚህ ማዕከል እውን መሆን፣ ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት ከፍተኛ ትግል አድርገዋል፡፡ ይሄ እንግዲህ የሚዲያውም አስተዋፅኦ ታክሎበት ነው ለዚህ የበቃው፡፡ ሁሉንም እናመሰግናለን፡፡
ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ምን ያህል አረጋዊያንን ያስተናግዳል?
እያንዳንዱ አገልግሎት ቢያንስ መቶ ሰው ያስተናግዳል፡፡ ጠቅላላው አገልግሎቱ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት፤ ይህን ማዕከል ልዩ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንደኛው በኢትዮጵያዊያን ብቻ መሰራቱ ሲሆን ሁለተኛው በተለያዩ ስፖንሰር አድራጊ ባለሀብቶችና ግለሰቦች እያንዳንዱ ክፍል መሰየሙ ነው፡፡ ሶስተኛው በሃዋሳ ከተማ የሚገኙ የአልጋ ቁራኛ አረጋዊያንን እያሰሰ፣ ምግብ ለሌላቸው ምግብ ያቀርባል፤ ይህን የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞን አሰልጥነናል፡፡ በሌላ በኩል በቀደመውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ክፍተት እንዳይኖር አረጋዊያን ለወጣቱ ልምዳቸውንና፣ እውቀታቸውን የሚያካፍሉበት አዳራሽ ከማዕሉ ጀርባ ይገነባል። በኪነ ጥበብ፣ በታሪክና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ወጣቶች አገራቸውን እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን አስተባብረን  ነው አዳራሹን የምንገነባው፡፡ አዳራሹ ከ500 ሰው በላይ የሚይዝ ትልቅና ዘመናዊ ነው የሚሆነው። ለሰርግ፣ ለጉባኤና ለስብሰባዎች እየተከራየ፣ ማዕከሉን ይደግፋል የሚል እቅድ ይዘናል። ሌላው ጥናትን መሰረት ያደረገ ዘላቂ የአረጋዊያን ድጋፍ ለመስጠት፣ ‹‹ኮሚዩኒቲ ሰርቪስ›› በሚለው ዲፓርትመንታቸው በኩል ከሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ጋር በንግግር ላይ ነን፤ ይሄም የሚሳካ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሙያና ቴክኒክ ትምህርት ቤቱ፤ ለ30 አረጋዊያን በነፃ ስልጠና ሰጥቶልናል፡፡ ሜሪ ጆይ፤ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው አረጋዊያን ማህበርን አቋቁሟል፤ ስልጠናውም ቅድሚያ የተሰጠው ለእነሱ ነው፡፡ ከስልጠናው በኋላ ስራ እየሰሩ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርገናቸዋል፡፡
ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር ዓመታዊ በጀቱ ምን ያህል ይሆናል?
አመታዊ በጀቱ 1.5 ሚ ብር ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ ከባለሀብቶች፣ ከታዋቂ አርቲስቶች፣ ከመንግስትና ከንግዱ ማህበረሰብ ነው የምናሰባስበው፡፡ አሁን ያቀድነው ለአንድ አመት የሚሆነውን በጀት ዘግተን ለመጀመር ነው፤ ማሰባሰብም ጀምረናል፡፡ ለምሳሌ ግርማዬ ፈረደ የተባሉ ባለሀብት ወይም ሲጂኤፍ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ - 130 ሺህ ብር፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ - 300 ሺህ ብር ለመነሻ የሰጡን ሲሆን የደቡብ ክልል መስተዳደር 750 ሺህ ብር ሊሰጠን ቃል ገብቶልናል፡፡
ሜሪ ጆይ በአርባ ምንጭና በድሬደዋ ተመሳሳይ ማዕከላትን ለመገንባት ከዓመታት በፊት እንቅስቃሴ መጀመሩን አውቃለሁ፡፡ ከምን ደረሰ?
በሁለቱም ቦታዎች እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አርባ ምንጭ ላይ ወደ 2 ሚ. ብር አለን፡፡ ድሬደዋ እንቅስቃሴው በጣም ሄዷል፤ እንዲያውም ፀደቀ የተባለ ወጣት ባለሀብት፣ 600 ሺህ ብር አውጥቶ አጥሩን አጥሮታል፡፡ እዛ የምንሰራው ከዳዊት አረጋዊያን ማህበርና ከከተማው ፅ/ቤት ጋር ነው፡፡ በቅርቡ ግንባታ ይጀመራል፡፡ ግንባታው የሚካሄደው በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ነው፡፡ የአርባ ምንጩን ግንባታ ለመጀመር ጠረጋ ተጀምሯል፡፡ የአርባ ምንጩ በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እነዚህም ማዕከላት እንደ ሀዋሳው እውን ይሆናሉ፡፡ ሶስቱ ማዕላት ስራ ላይ ሲሆኑ ለየከተማዎቹ አረጋዊያን እያንዳንዳቸው በወር ለ5 ሺህ ሰው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በአጠቃላይ በወር 15 ሺህ አረጋዊያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሜሪ ጆይ ዋና ፅ/ቤቱ ያለው አዲስ አበባ ነው። በሌላ በኩል ታዋቂና አንጋፋ አርቲስቶች በበጎ ፍቃደኝነት የሚደግፉት ነው፡፡ ሁላችሁም ደግሞ አረጋዊ ወደመሆኑ እየሄዳችሁ ነው፡፡ መጀመሪያ ለራሳችሁ ማረፊያ አዲስ አበባ ላይ ማዕከል ሳታቋቁሙ እንዴት ወደ ክልል ሄዳችሁ?
መጀመሪያ አዲስ አበባ ላይ ለመገንባት ነበር እኮ እንቅስቃሴ የጀመርነው፡፡ ቦታ አጥተን ነው፤ ለአዲስ አበባ የመደብነውን 2 ሚ. ብር ይዘን ሀዋሳ የሄድነው። ቦታ ጠይቀን በጣም ረጅም ጊዜ ሲፈጅብን ሀዋሳ ሄደን፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ስንጠይቅ፣ “ይሄ ተገኝቶ ነው” ብለው፣ በ10 ቀናት ውስጥ ነው ያየሽውን አይን የሆነ ቦታ የሰጡን፡፡ ቦታው በዛን ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከልክሎ ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረው፣ በ10 ቀናት ውስጥ ካርታ አገኘን፤ ይሄ ሞራል ሰጠን። የአዲስ አበባን ብር ይዘን፣ እዛ ጀመርን፤ ይሄው ለመጠናቀቅ በቃ፡፡
አሁንስ የአዲስ አበባውን ማዕከል ለመገንባት የቦታው ጉዳይ ተስፋ ሰጪ ነው?
አዎ መገንባቱ አይቀርም፤ ካልሆነ ሜሪ ጆይ የራሱ ቢሮ ግቢ ውስጥም ቢሆን በጣም ዘመናዊ ማዕከል ይገነባል፡፡ እንዳልሺው ያው እኛም ወደ አረጋዊነቱ እያመራን በመሆኑ ነገ ማረፊያ ያስፈልገናል፡፡ ለአዲስ አበባ አረጋዊያንና ለራሳችን ማዕከሉን ለመገንባት፣ ከአርቲስት በጎ ፈቃደኞቻችንና አጋሮቻችን ጋር በምክክር ላይ ነን፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድና ፈተና በኋላ ማዕከሉ ተጠናቅቆ ማየት ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥራል?
በጣም ደስ ብሎኛል፤ ያው አንዳንዴ ደስታን በቃላት መግለፅ ያስቸግራል፤ እንደውም አርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ ለዚህ ማዕከል ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙ ፈተና ገጥሞታል። ግማሹ እያለ የለም ሲያስብለን፣ ሌላው በሩን ሲዘጋብን እሱ፣ ብዙ ችግር ከእኔ ጋር አሳልፏል። መጨረሻ ላይ የምንሰራበት ብር ሁሉ አጥተን፤ ‹‹እንደው ይሄ ማዕከል ተሰርቶ በነጋታው በሞትኩ›› ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ትልቅ ነው። አንዳችንም በቁጥር ሳንጎድል ማዕከሉ ተጠናቀቀ። ሲጀመር የነበራችሁ ጋዜጠኞች፣ ባለፈው ቅዳሜ ቦታው ላይ ተገኝታችሁ በማዕከሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ስሰጥ፣ከምቆጣጠረው በላይ የሆነ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ በመጨረሻ ለዚህ ህልም እውን መሆን ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን አርቲስቶች፤ የሀዋሳ ከተማ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ነጋዴዎች፣ በአዲስ አበባና በውጭ የሚገኙ ባለሀብቶችና ግለሰቦች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና መገናኛ ብዙሀን ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ አብረውን የደከሙትን ሁሉ ብድራታቸውን ፈጣሪ ይክፈላቸው እላለሁ፤ አመሰግናለሁ፡፡ “ይቻላል” የሚለውን መንፈስ አዳብረናል፤ አይደለም በሶስት ከተሞች በአገራችን በሁሉም ከተሞች የአገር ባለውለታዎች የሚዝናኑበት፣ የሚታከሙበት፣ የሚጨዋወቱበት ማዕከላት ይገነባሉ፡፡

Read 3041 times
Administrator

Latest from Administrator