Sunday, 07 May 2017 00:00

“የአዋሽ” ስንኞች ርቀትና ልቀት”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 የሎሬት ፀጋዬ “እሳት ወይስ አበባ” ውስጥ “አዋሽ” የተሰኘውን ግጥም በተመለከተ እንድናገር የኢቢሲዋ ጋዜጠኛ ጋብዛኝ ገፆቹን ሳገላብጥ፣ የታመመ ልቤ እስካሁን አላገገመም፡፡ ኪኒን - አልቃምኩም፣ ፀሎትም አላረኩ! … የሚጣፍጥ ህመሜን ይዤ - ከልቤ ጋር አብሬው ተኝቻለሁ፡፡ አሁን አዋሽ ከመሬት ተነቅሎ በኔ ልብ ጓዳ ውስጥ፣ በደሜ ክሮች ይፈስሳል፤ ይዘንባል! … የፀጋዬ ዝናብ!
1200 ኪሎ ሜትር ያህል የሚረዝመው አዋሽ፤ - ግቡ አሸዋ ነው፡፡ ዕድሉ መስጠም ነው፡፡ … ሳቁና ፉጨቱ፣ ሮሮውና ዋይታው የመንገድ ስንቁ ነው። አዋሽ በመስከረም አበቦችን እንደኮረዳ ከንፈር ይስማል፤ … በምሽት ከጨረቃ ጋር እየተጣቀሰ፣ እያፏጨ ይፈስሳል፡፡ … አንዳንዴ ባይተዋር ነው፣ ሌላ ጊዜ፣ ቁጠኛ፣ አንዳንዴም - ሽፍታ! … ግና ትዝታ የለውም፤ … መንገድ ላይ ሁሌ ትኩስ ነው … እንደተጣደ ድስት! … ቤቱ ግን አይታይም፣ እንደ ሙሴ መቃብር! ለዚያም መሰለኝ ባለቅኔው እንዲህ ያለው፡-
… ላትዘልቀው ላያዛልቅህ
አሸዋ ላሸዋ ድኸህ
ውስጥ ለውስጥ ምሰህ ጠልቀህ
የምድርን ማህፀን ቦርቡረህ
ዋልታዋን ቁልቁል ሰንጥረህ
እናትህ ውቅያኖስ ማኅፀን፣ ላትገባ ትባክናለህ፣ …
ሳስቶለታል ለአዋሽ፡፡ አፈፃፀሙ ያሳዝናል፣ ብኩን ህይወቱ ያባባል፡፡ ስሱን የገጣሚ ስሜት ይሸነቁራል። ላይዘልቅ መሮጡ፣ ግብ ላይደርስ መጠለዙ፣ የባከነ ኳስ መሆኑ!
አዋሽ ሀገር ነው፡፡ አዋሽ ለቱለማ ደም ለጉራጌ አድባር ለከረዩ ማርና ቅቤ ነው፡፡ ለአሸዋው ዋሻ ነው። ታዲያ በደጉ ቀን ነው፡፡ በሰላም ጊዜ፣ … በተረጋጋ ወቅት! በክረምት ግን እንዲያ አይደለም። ቀንድ ያወጣል፤ ያስደነግጣል፤ ቀማኛ ነው ይናጠቃል፡፡
አዋሽ የመጫ ስር ፍሳሽ
የዳዳ የቱለማ ደም
የሰባት ቤት ጉራጌ አድባር
የከረዩ ቅቤና ማር
ፈስሰህ ለአሸዋ የምትዳር?
በደጉ ቀን አዋሽ ሙሽራ ነው፡፡ አዋሽ ደም ነው ወዘተ .. በሌላ ቀን ግን …
አባ ጭራቅ - አክናፍ ቀንዶ
አዋሽ ዘጠኝ ራስ ዘንዶ
ቁልቁል እንደምሽት ጥላ፣ ከሰማየ ሰማይ ወርዶ
ሞልቶ ተንደላቆ ኮርቶ፣ የስንት ዓለም ምድር ጎርዶ
ቀይ ደመና ተከናንቦ፣ ጋራ እንዳሻንጉሊት አብሎ
ስንቱን በረት ጉድፍ፣ አውተፍትፎ አንጠልጥሎ
አውድማውን አንገዋሎ
ወርካውን ግቻ አሳክሎ
አመንምኖ አሰልሎ
* * *
አዋሽ ቁጣ አባ ዱታ
የሰማይ ጥጉ ቱማታ፣
አዋሽ አባሻኛው ጋራ
ኩሩ እንደነማታ ሃራ፣
የግርማ ሞገሥ ዘርፉ
እስከነምድረ አቀፍ ዘርፉ
አባ ገርስስ ሞልቶ ደራሽ፣ አባ አደፍርስ አባ ኩርፋድ
ከተፍ እንደመብረቅ ግማድ
በምድር ቁና ድንገት ሲጣድ፣
አዋሽ ንፉግ አባ መዓት
የገጠሬ አታምጣ ምጣት፣
አዋሽ ደርሶ ቀማው መብረቅ
አባ መዝረፍ መውሰድ መንጠቅ
ግሣንግሱን አግበስብሶ በምድረ በዳ ለማመቅ
በነዚህ ስንኞች ለዋጭ ሰውኛና እንቶኔ፣ ጠቃሽ ዘይቤዎች በእጅጉ ይወዘወዛሉ፡፡ አዋሽ እዚህ ጋ ያስፈራል፡፡ አያሳዝንም፣ ያበሳጫል። … ቁጣ ነው ድንገት ይወድቃል፡፡ ገርሣሽ ነው፣ እንደ ፈጣሪ ሀብታሙን ደሃ ማድረግ ይችላል። ከብቶቹን ከበረት፣ ሰብሉን ከእርሻው መደምሰስ ማንም አይከለክለውም፡፡ ነጥቆ ለኪሱ አይደለም፣ ነጥቆ ለትዳሩ አይደለም፣ ቤት የለውም፣ ማደሪያ አላገኘም። መሸሸጊያ ሽርጥ እንኳ አላገለደመም፤ እርቃኑን ሮጦ መቃብር ይገባል፡፡ እሰይ! … ዘርፎ መና አይዬ!
ደ‘ሞ አዋሽ ያሳዝናል፡፡ አዋሽ ገራገር ነው፡፡ ደግ ነው፣ ባይተዋር ነው፡፡ ባከና ነው፣ የትም ለማንም ይሞታል - ያለ አመስጋኝ፡፡
የሸዋ የእምብርትሽ ላቦት፣ የምንጮችሽ ፍላጭ፣
እስከመቼ ይሆን አዋሽ፣ ወዝክን አሸዋ እሚውጥህ?
ደምክን በረሃ እሚመጥህ
አጥንትህን ምድረ በዳ ሀሩር እሚመዘምዝህ?
መጫ ቋጥሮ ሸዋ ፀንሶ፣ ሰባት ቤት ጉራጌ አርግዞ
ከዳዳ ምንጭ አርሲ እምብርት፣ ከነቅሪቱ ተጉዞ
ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን፣ አዳል ሞቲ ሽሉን ይዞ
ከከረዩ ማታ ሐራ፣ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ
እንደወላድ ሳይታረዝ፣ ከነፅንሱ አረህ ሰምጦ …
በምድረበዳ ጉሮሮ፣ በረሃ ላንቃ ተውጦ
አሸዋ ነክሶ ቀረ አዋሽ፣ ላይገላገል ሸምጥጦ፡፡  
አዋሽ ብቸኛ ነው፡፡ አይዞህ ባይ የለውም፡፡ የጨረቃ ግዞተኛ ነው፤ የምድረበዳ የበረሀ ተጓዥ ነው፤እያፏጨ ይገሠግሣል - እንደ ጎረምሳ፡፡ ቡቡ ነው - ያለቃቅሳል፡፡ ዋናተኛ ነው፤ ይዋኛል፡፡
የአለት ጉልጥምጥሚት ፍራሽ ውስጡን አደፍርሶት፤ ከብዶት ነው የሚጓዘው፤ ግራና ቀኙን የመልካውን ገላ እየቆረሰ፣ እየዳበሰ ይሄዳል፡፡ እንደ ኮረዳ ዳሌውን እያማታ፤ በፍስሀ አይደለም ዳንሱ፤ በሠቀቀን ነው ሩጫው፡፡ ወዴት እንደሚሄድ ያውቃላ!... የጠቢቡ ሰለሞን መጽሐፈ መክብብን ሳያንጎራጉር አይቀርም፡፡
“የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፤ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሀይ በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ማንም ‘እነሆ፤ ይህ ነገር አዲስ ነው’ ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ሰዎች ተደርጓል፡፡ ለፊተኞቹ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ለኋለኞቹም ነገሮች ከእነርሱ በኋላ በሚነሱት ሰዎች ዘንድ መታሰቢያ አይገኝላቸውም፡፡
አዋሽ ቡቡ በረኸኛ
የአረህ ሸለቆ በረኛ
የአዋሽ ዋሻ መተኛ
የበረሀ ዋናተኛ
የምድረበዳ ብቸኛ
የዘለዓለም መንገደኛ….
አዋሽ እንደ ዘላለም ነው፣ መቆሚያ የለውም። መታሰቢያ የለውም፡፡ ጠቢቡ እንዳለ አዲስ ነገር የለውም፡፡ ዝም ብሎ ይፈሥሣል፡፡ አዲስ ነገር የለም!.... አምናም-ሀቻምና ዘላለምም!...
አዋሽ አይቆጭም፤ አዋሽ አይፀፀትም፡፡ ሲከፋው ያኮርፋል፣ ይቆጣል፤ ይሮጣል፤ ሲናደድ ደሙ ሲደፈርስ ይዘርፋል፡፡ ፀፀት ቢኖረው ኖሮ የአረጋሽ ሰይፉን ግጥም ያሠላሥል፤ ወይም ያነበንብ ነበር፡፡
ጣሉብኝ እርጥባን፣ ምንተ…ስለ…ስለት!
በዋዛ ፈዛዛ፤ ያሳለፍኩትን ቀን መልሼ ልግዛበት፤
አይበርድም ነዲዱ፤ ፍሙ እንኳ ቢከስል፤
እዩት እንደራቀ የባከነ ጊዜ፤ ምን አለ ሚያቃጥል!
ሎሬቱ የአዋሽ ጊዜ አንገብግቦታል፤ የአዋሽ ሕይወት ውስጡን ነዝንዞታል፤ ልቡን አንጥፎታል። አዋሽ በፀጋዬ ልብ ላይ ፈሥሶዋል፡፡ በእምባው ውስጥ ተሽከርክሯል፡፡
አዋሽ ሎሬት ፀጋዬን፣ ከቶ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ፀጋዬ ዘንዶ አይደለም፤… ፀጋዬ አባ መዝረፍ አይደለም፡፡ አባ ጭራቅ፣ አባ መዐት ሊሆን አይችልም!...
አዎ ፀጋዬ ቡቡ፤ ፀጋዬ ዋናተኛ፣ ፀጋዬ የጨረቃና የውበት ግዞተኛ ሊሆን ይችላል፡፡
በሁለተኛ መደብ ትረካ፤ በዘይቤዎች ጌጥ የተንቆጠቆጠው አሸዋ፤ ዛሬ ወደ አዋሽ እየሮጠ ነው፤… ዛሬም ወደ መቃብሩ እየፈሰሰ ነው፡፡ ሃያል መታሰቢያ የለውም፤ ይልቅስ ይሮጣል፡፡ በቀንና ሌት ይሄዳል፡፡ … መድረሻው የምድር ከርሥ ነው፡፡ … ግቡ አይታወቅም፡፡ ብቻ ይሞታል፡፡ ድምፁ ይሰወራል። ህይወቱ ይጠፋል፡፡ ጉልበቱ ይቀራል፡፡ መዝሙሩ ይከሽፋል፡፡
ምናልባት አዋሽ ህይወት ይሆን! … ደም ይዞ የሚጓዝ፣ … በተቆጣ ቀን በረት የሚገለብጥ፣ ኑሮን የሚያመሳቅል! ሲለው የሚሞሽር አሊያም ገድሎ የሚገንዝ! … የአዋሽ ጉዞ የህይወት ጉዞ ቢሆንስ? ፀጋዬን አንጠይቅም! .. የጥበብ ድንኳኖቻችንን እንንጣለን፣ … ነፍሳችንን እናርገበግባለን፡፡ … የበገናውን ክሮች .. እንጠዘጥዛለን … ያኔ ምስጢሩ ይገለጣል፡፡     

Read 444 times