Sunday, 07 May 2017 00:00

4ኛው የ”ጉማ ፊልም ሽልማት” - በቅርብ ርቀት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  · በ11 ዘርፎች የታጨው “የነገን አልወልድም”፤ 6 ሽልማቶች ሰብስቧል
          · በ14 ዘርፎች የታጨው “መባ”፤ 4 ሽልማቶች ተሸልሟል
          · የ”ለዛ” አዘጋጅ ብርሃኑ ድጋፌ፤ በሁለት ዘርፎች አሸንፏል
            
     በኢትዮ ፊልም በየዓመቱ የሚዘጋጀው “ጉማ ፊልም ሽልማት” ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ባለፈው ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ቴአትር ተከናውኗል፡፡ በጥሪ ካርዱ ላይ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ የብሔራዊ ቴአትር በሮች እንደሚከፈቱና 11፡00 ሰዓት ላይ ፕሮግራሙ እንደሚጀመር ቢገለፅም እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ የዘንድሮውም ከታቀደለት 1 ሰዓት ተኩል ዘግይቶ 12፡30 ላይ ነው የተጀመረው፡፡
ኢትዮ ፊልም፤ ስለ ሽልማት ሥነ ስርዓቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ አለባበስን በተመለከተ ጂንስ ሱሪ፣ እጀ ጉርድ ሸሚዝ፣ ሸራ ጫማ፣ ስኒከር፣ ካኪ ሱሪ --- ለብሶና ተጫምቶ መምጣት እንደማይፈቀድ፤ በዚህ አለባበስ የሚመጣ ቢኖር እንኳን በር ላይ ከሚገኙ የፀጥታ ሰራተኞች ጋር እንደሚጋጭ አስጠንቅቆ ነበር፡፡ ሆኖም በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ታዳሚዎች በተተለተለ ጂንስ፣ በሸራና በስኒከር  መገኘታቸውን ታዝበናል፡፡ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ ”አዘጋጆቹ ያልተፈቀደ አለባበስ ለብሰው የመጡትን በመመለስ፣ የሽልማት ስርዓቱን ደረጃ መጠበቅ ነበረባቸው” ብለዋል፡፡
በሽልማት አሰጣጥ ሥነሥርዓቱ ወቅት በአንዳንድ ተጋባዥ ሸላሚዎች ላይ የታየው ግራ መጋባትና መደናገር እንዲሁም የመድረክ አጋፋሪዎቹ በእንግዶቹ ላይ መሳለቅ የሥነስርዓቱን አዘጋጆች ክፉኛ አስተችቷል፡፡ “እነዚህ ሰዎች ለሸላሚነት ሲመረጡ በቅድሚያ ማድረግ ያለባቸውን መንገርና ማስረዳት የአዘጋጆቹ ስራ ነበር፤ ይህን ባላደረጉበት ሁኔታ ግርታ ውስጥ የገቡ የተከበሩ እንግዶች ላይ መሳለቅ ተገቢ አይደለም” ብለዋል - የዝግጅቱ ታዳሚዎች፡፡ “ሽልማቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እነዚህም ትንንሽ የሚመስሉ ግን ትዝብት ላይ የሚጥሉ ጉድለቶች መታረም አለባቸው” ሲሉም አክለዋል፡፡
  ወደ አንድ ሰዓት ገደማ፣ በፊልም ስራ የጉማ የህይወት ዘመን ተሸላሚ ከሚለው ዘርፍ ሽልማቱ ተጀመረ፡፡ የዘንድሮው የህይወት ዘመን የፊልም ጥበብ ተሸላሚ፤ “የዘጋቢ ፊልም አባት” እየተባሉ የሚጠሩት ክቡር አቶ ካሣ ምህረቱ ሲሆኑ ከፊልም ባለሙያው ብርሃኑ ሽብሩ እጅ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ አቶ ካሣ ምህረቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በተለያዩ ቴአትር ቤቶችና ሌሎች ቦታዎች በፎቶግራፍ ባለሙያነት ለበርካታ አመታት እንደሰሩ ተገልጿል፡፡ ተሸላሚው በከፍተኛ በደስታ ተሞልተው አዘጋጆቹን ያመሰገኑ ሲሆን የአሁኑ ትውልድ በየሙያው በርትቶ በመስራት ለቀጣዩ ትውልድ ቅርስ ማስቀመጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡  
የተማሪ አጭር ፊልም በሚለው ዘርፍ “ፊዲስቱ” የተሰኘው የሚካኤል ሽመልስ ፊልም አሸናፊ ሲሆን ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ከአንጋፋው ተዋናይና የህግ ባለሙያ አበበ ባልቻ ሽልማቱን ከወሰደ በኋላ መታሰቢያነቱን ለአንጋፋው የፊልም ልሂቅ ለፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እንዲሆንለት ጠይቋል፡፡
ምርጥ የፊልም ድምፅ በሚለው ዘርፍ “አትውደድ አትውለድ”፣ “ከደመና በላይ” “መባ” እና “የነገን አልወልድም” የተሰኙት ፊልሞች እጩ የነበሩ ሲሆን የ”አትውደድ አትውለድ” የድምፅ ባለሙያ ብሩክ አየለ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከአንጋፋው የዋሊያስ ባንድ አባልና የድምጽ ሊቅ አቶ መሀመድ አማን እጅም ሽልማቱን ወስዷል፡፡
በመቀጠል ምርጥ የጉማ የሙዚቃ ሽልማት አሸናፊ የሚለይበት የእጩዎች ዝርዝር የተገለፀ ሲሆን በሙዚቃ የላቀ ስራ ሰርተዋል ተብለው ምርጥ አምስት ውስጥ የገቡት፡- “ሄሮል”፣ “ስስት ሁለት” (አብነት አጎናፍር)፣ “መባ” (ብሩክ አሰፋ)፣ “ሄዋን ስታፈቅር” (አዳነች ሀይሉና ተገኘ ብሩ) እና “ዩቶጵያ” (ማክዳ አፈወርቅና ኤልሳቤት መንግሥቱ) ነበሩ።  ድምፃዊ አብነት አጎናፍር በ”ስስት ሁለት” አሸናፊ ሆኗል፤ድምጻዊው በሥፍራው ባይገኝም በተወካዩ በኩል ከክብር ዶ/ር ዳዊት ይፍሩ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡
ምርጥ የፊልም ስኮር በሚለው ዘርፍ “ከደመና በላይ” (ቴዎድሮስ ሞገስ)፣ “የነገን አልወልድም” (ታደለ ፈለቀ)፣ “ሄሮል” (ስምአገኘሁ ሳሙኤል)፣ “አትውደድ አትውለድ” (ብሩክ አየለ) በእጩነት የቀረቡ ሲሆኑ “የነገን አልወልድም” በሚለው ፊልም ወጣት ሙዚቀኛ ታደለ ፈለቀ አሸንፎ፣ ከታዋቂው ሙዚቃ አቀናባሪ ሱልጣን ሶፊ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ ከመድረክ ከመውረዱ በፊት ባደረገው አጭር ንግግርም፤ “ታዴ እንኳን ደስ አለህ፤ በርታ አመሰግናለሁ” በማለት ራሱን ሲያበረታታ፣ አዳራሹ በሳቅ ተሞልቷል፡፡  
ምርጥ የገፅ ቅብ (ሜካፕ) ዘርፍ - “መባ”፣ “የነገን አልወልድም”፣ “ያቤፅ” እና “ስስት ሁለት” እጩ የነበሩ ሲሆን የ”መባ” ፊልም ሜካፕ አርቲስት ደረጀ ፍቅሬ አሸናፊ ሆኖ ከገፅ ቅብ ባለሙያውና አምና “የመሀን ምጥ” በሚል ፊልም የዘርፉ አሸናፊ ከነበረው ታደሰ ንጉሱ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡
ምርጥ ወጥ የፊልም ፅሁፍ በሚለው የሽልማት ዘርፍ በ”ስስት ሁለት” ፍፁም ካሳሁን፣ በ”ባማካሽ” ጌታቸው ታደለ፣ በ”ዩቶጵያ” በኃይሉ ዋሴ፣ በ”መባ” ቅድስት ይልማ፣ በ”አትውደድ አትውለድ” ፊልም ናኦድ ጋሻው ታጭተው፣ ናኦድ ጋሻው አሸናፊ ሆኗል።
ምርጥ የፊልም ቅንብር (ኤዲቲንግ) ዘርፍም እንዲሁ በ”መባ” ፊልም ብስራት ጌታቸው፣ በ”ሄሮል” ዳንኤል አንማው፣ በ”ስስት ሁለት” ዘርዓይ ያዕቆብ፣ በ”አትውደድ አትውለድ” ናኦድ ጋሻው እና በ”የነገን አልወልድም” ፊልም ናሆን ግርማ ታጭተው፣ የ”ሄሮል” ፊልሙ ዳንኤል አንማው አሸናፊ ሆኖ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በሚድሮክና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ኤዲተርና የኦዲዮ ቪዥዋል ባለሙያ የሆነችው አስናቀች ፀጋዬ እጅ ሽልማቱን ወስዷል። ሸላሚዋ የሙያ አቧቷ የሆኑት አቶ ካሣ ምህረቱ፣ የህይወት ዘመን ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማትን ደስታ ገልፃለች፡፡
ከዚህ በኋላ በህይወት ያጣናቸው አንጋፋ አርቲስቶች የሚታወሱበት የቪዲዮ ምስል ለታዳሚው የታየ ሲሆን በዚህ ቪዲዮ ላይ ተዋናይ ጌታሁን መርዳሳ፣ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ አባተ መኩሪያ፣ ታምራት ምህረተአብ፣ ሰብለ ተፈራና ሌሎችም ታውሰዋል፡፡ ቀጣዩ የሽልማት ዘርፍ ምርጥ ሲኒማቶግራፊ የሚል ሲሆን “ሄሮል”፣ “ባማካሽ”፣ “መንሱት”፣ “መባ” እና “የነገን አልወልድም” እጩ ነበሩ፡፡ የዘርፉን ሽልማት “መባ” በተሰኘው ፊልም ብስራት ጌታቸው አሸናፊ በመሆን የረጅም ዓመት የፎቶግራፍ ባለሙያ ከሆኑትና አሁንም በሙያው ላይ ከሚገኙት አንጋፋ የፎቶግራፍ ባለሙያ አቶ ክንፈ ኃ/ማሪያም እጅ ተቀብሏል፡፡ አቶ ክንፈ ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት አጭር መልዕክት፤ አገራቸውን ያገለገሉ በርካታና በጡረታና በእድሜ የተገለሉ ባለሙያዎች እንዲታወሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምርጥ ተስፋ የተጣለባት ተዋናይት በተሰኘው ዘርፍ፤ ከ”መባ” ፊልም አለም ካሳሁን ከ”ማካሽ” ሜላት አዲስ፣ ከ”እውነት ሀሰት” ብሩክታዊት ሽመልስ ታጭተው የነበረ ሲሆን የ”መባ”ዋ አለም ካሳሁን አሸንፊ ሆና ከሞዴልና ተዋናይት እፀህይወት አበበ እጅ ሽልማቷን ወስዳለች፡፡ አምና በዚህ ዘርፍ የ”ላምባዋ” ሊዲያ ሞገስ አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል፡፡ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት የወንድ ተዋናይ ዘርፍ፤ በ”መንሱት” ማህደር ታሪኩ፣ በ”መባ” ሳምሶን በቀለ እና በ”የነገን አልወልድም” በሸገር ኤፍኤም የ”ለዛ” ፕሮግራም አዘጋጁ ብርሀኑ ድጋፌ ታጭተው የነበረ ሲሆን ብርሀኑ ድጋፌ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው ንግግር፤ ”አንድ ዳይሬክተር ተዋናዩን ይፈጥረዋል አይፈጥረውም በሚል ከፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ጋር ስንከራከር፣ ሀይሌ ገሪማ ዳይሬክተሩ ተሰጥኦውን ያወጣዋል እንጂ አይፈጥረውም ብሎኝ ነበር፤ እኔን ግን ዳይሬክተሩ አብርሃም ገዛኸኝ ፈጥሮኛል” ሲል የፊልም ዳይሬክተሩን አወድሷል፡፡  
በምርጥ ረዳት ተዋናይት ዘርፍ፤ በ”መ”ባ ፊልም ዘሪቱ ከበደ፣ በ”የነገን አልወለድም” ህይወት ግርማ፣ በ”ወፌ ቆመች” ድርብወርቅ ሰይፉ፣ “በቁም ካፈቀርሽኝ” ማህሌት ፍቃዱ፣ በ”ስስት ሁለት” ማርታ ጎይቶም ታጭተው፤ ማርታ ጎይቶም አሸናፊ ሆናለች፡፡ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ዘርፍ፤ “የነገን አልወለድም” በተሰኘው ፊልም ተስፋዬ ይማም ተሸላሚ ሆኗል፡፡  
በምርጥ መሪ ተዋናይት የሽልማት ዘርፍ፤ ከ”መንሱት” ፊልም አዚዛ መሀመድ፣ ከ”ያቤፅ” መዓዛ ታከለ፣ “ከደመና በላይ” ቃልኪዳን ጥበቡ፣ ከ”ሰላም ነው” ፀጋሽ ሀይሉ፣ ከ”መባ” እድለወርቅ ጣሰው በእጩነት ቀርበው፣ የ”መባ”ዋ እድለወርቅ ጣሰው ስታሸንፍ ከአንጋፋዋ አርቲስት ፍቅርተ ጌታሁን እጅ ሽልማት ተቀብላለች፡፡ ገና ስሟ በስክሪን ላይ ሲታይ ጭብጨባና ፉጨት የተስተጋባላት አርቲስት እድለወርቅ ጣሰው፤ ሽልማቷን ከተቀበለች በኋላ፡- “ቀድማችሁ ሸልማችሁኛል፤አመሰግናለሁ” ብላለች - ታዳሚውን፡፡  
በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ ዘርፍ፤ ከ”ያቤፅ” ሰለሞን ጥላሁን፣ ከ”የነገን አልወልድም” ብርሀኑ ድጋፌ፣ ከ”ዩቶጵያ” ደሞዜ ጎሽም፣ ከ”መባ” አማኑኤል ሀብታሙና ከ”ደመና በላይ” እንግዳሰው ሀብቴ ታጭተው፣ ብርሃኑ ድጋፌ “የነገን አልወልድም” በሚለው ፊልም አሸንፎ ሁለተኛ ሽልማቱን ለመውሰድ መድረክ ላይ የወጣ ሲሆን ከተባባሪ ፕሮፌሰር አቦነህ አሻግሬ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡ ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ አጠር ያለ ንግግር ያደረጉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ”እንዲህ አይነት ዝግጅቶች የአገራችንን የሲኒማ ደረጃ የሚያመላክት በመሆኑ በርቱ” በማለት አዘጋጆቹን አበረታተዋል፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት ብቸኛው የ”ጉማ ሽልማት” የክብር ስፖንሰር ሆኖ የዘለቀው የበደሌ ስፔሻል ምርጥ የህዝብ ምርጫ ፊልም በተሰኘው ዘርፍ፤ “እውነት ሀሰት”፣ “ይመችሽ”፣ “ሀእና ለ”፣ “ወፌ ቆመች” እና “ስስት ሁለት” በእጩነት ቀርበው፤ ‹‹ወፌ ቆመች›› ያሸነፈ ሲሆን የፊልሙ ዳይሬክተሩ ከበደሌ ስፔሻል ማርኬቲንግ ማናጀር ከአቶ ፍቃዱ በሻህና ከባልደረባቸው  ሽልማቱን ወስዷል። በምርጥ የፊልም ዳይሬክተር ዘርፍም፤ ‹‹የነገን አልወልድም›› የፊልም ዳይሬክተር አብረሀም ገዛኸኝ ያሸነፈ ሲሆን ‹‹የፍቅር ዋጋው›› በተሰኘ ፊልሟ 11 ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ካገኘችው ሄርሞን ሀይሌ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል። በምርጥ ፊልም ዘርፍም ይሄው ፊልም ያሸነፈ ሲሆን ከኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዱዩሰሮች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም አለማየሁ እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡ ዓምና በዚህ ዘርፍ ያሸነፈው “ላምባ” ፊልም እንደነበር ይታወሳል። በ11 ዘርፎች የታጨው “የነገን አልወልድም”፤ በ6 ዘርፎች ሽልማት በመሰብሰብ ቀዳሚ ሲሆን በ14 ዘርፎች የታጨው “መባ”፤ በ4 ዘርፎች በመሸለም ተከታይ ሆኗል፡፡
በመጨረሻም አዘጋጆቹ፤ በቀጣዩ ዓመት የሰዓቱን ጉዳይ ለማስተካከልና እንደተለመደው የካቲት ላይ ለማዘጋጀት ቃል ገብተው የሽልማት ሥነሥርዓቱ ተጠናቅቋል፡፡

Read 1714 times