Saturday, 06 May 2017 10:19

5ኛ ዓመት “የኢትዮጵያ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር ግንቦት 19 ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 “የአፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ዋና መ/ቤት አዲስ አበባ ሆነ
                   

      ከተመሰረተ 5ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የ“ኢትዮጵያ ስፔሊንግ ቢ” የማጣሪያ ውድድሩን በመጪው ግንቦት 19 እንደሚያካሂድ የገለፀ ሲሆን 184 የአዲስ አበባና የክልል ተማሪዎች በውድድሩ እንደሚሳተፉ “የኢትዮጵያና የአፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር መስራች አቶ አብይ ተክሌ ገለፁ፡፡ የዘንድሮው ውድድር በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2900 ት/ቤቶች በተውጣጡ 750 ሺህ የሚደርሱ ከ3-8ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ሲካሄድ መቆየቱንና በመጨረሻም ከአዲስ አበባ 115፣ ከድሬደዋ፣ ከሀዋሳ፣ ከደብረዘይት፣ ከባህርዳርና ከሌሎችም ከተሞች የተውጣጡ በድምሩ 184 ተማሪዎች ተወዳድረው “ምርጥ 10ቹ” የሚለዩበት እንደሆነም ታውቋል፡፡
ከዘንድሮው ውድድር መስፈርቶች አንዱ “Ethiopia through writers’ eye” የተሰኘና በ8 የውጭ አገር ዜጎች የተፃፈ መፅሐፍን ማንበብና ተማሪዎች ስለ አገራቸው ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት እንደሆነ የገለፁት አቶ አብይ የመወዳደሪያ ጥያቄዎችም ከዚሁ መፅሀፍ እንደሚወጡ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ከ1-10 ለወጡ ተማሪዎች 1ኛ ለወጣ 50 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለወጣ 40 ሺህ ብር፣ 3ኛ ለወጣ 30 ሺህ ብር፣ 4ኛ ለወጣ 20 ሺህ ብር ሽልማት የሚያስገኝ ሲሆን ከ6-10 ለሚወጡ አሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ሽልማት ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ1-3 የሚወጡ አሸናፊዎች በሐምሌ ወር በኬኒያ ሞምባሳ በሚካሄደው “የአፍሪካ ስፔሊንግ ቢ” ውድድር ላይ ለመካፈል እንደሚሄዱ የገለፁት መስራቹ፤ በኬንያው ውድድር 1ኛ ለሚወጣ 10 ሺህ ዶላር፣ 2ኛ 5 ሺህ ዶላር፣ 3ኛ የሚወጣ የ2 ሺህ 500 ዶላር ሽልማት እንደሚያገኙም ተገልጿል፡፡ 1ኛ የሚወጣው ተማሪ አጋዥ መምህር ተማሪው 10 ሺህ ዶላር ሲያገን መምህሩ አምስት ሺህ ሁለተኛ የሚወጣው ተማሪ 5 ሺህ ዶላር ሲያገን መምህሩ 2500 ዶላር 3ኛ የሚወጣው ተማሪ አጋዥ መምህር፣ የተማሪውን ሽልማት ግማሽ እንደሚያገኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል የአፍሪካ ስፔሊንግ ቢ ዋና መ/ቤት ወደ አዲስ አበባ መዛወሩን የገለፁት አቶ አቢይ፤ እሳቸውም በዳይሬክተርነት መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከመጪው ዓመት ጀምሮ የአፍሪካ ስፔሊንግ ቢ የመጨረሻ ዙር ውድድር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 1370 times