Sunday, 07 May 2017 00:00

ልዩ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  አራቱ የ1980ዎቹ ኮከብ ድምፃውያን ከሮሃ ባንድ ጋር ዘፈኖቻቸውን ያቀርባሉ

    ግንቦት 12ቀን 2009 ዓ.ም በግዮን ሆቴል ይካሄዳል በተባለው በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በወቅቱ ‹‹ሁሉም ቢተባበር›› በሚለው የጋራ ዜማቸው ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፉትና የ1980ዎቹ አራት ምርጥ ድምፃውያን፡- አረጋኸኝ ወራሽ፣ ፀሐዬ ዩሐንስ፣ ፀጋዬ እሸቱና ንዋይ ደበበ እንደሚሳተፉበት የኮንሰርቱ አዘጋጅ ከትናንት በስቲያ በአዚማን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ገልፀዋል፡፡
የኮንሰርቱ አዘጋጅ ታምር ማስታወቂያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን መለሰ እንደገለፀው፤ የሙዚቃ ኮንሰርቱ በአገራችን ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው ድምፃውያን ከሮሃ ባንድ ጋር በመሆን ያን ዘመን የሚያስታውሱ ሥራዎችን በሺዎች ለሚቆጠሩ አድናቂዎቻቸው ያቀርባሉ፡፡
የሙዚቃ ኮንሰርቱ ከተለመደው የሙዚቃ ኮንሰርት የተለየ መሆኑን የገለፀው አቶ ሰለሞን፤ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ‹‹ወርቃማው ዘመን›› እየተባለ በሚጠራው የ1980ዎቹ ዓመታት ያለፉ በዘመኑ ምርጥ የተባሉ የሙዚቃ ሥራዎችን ሲያጣጥሙ የነበሩ አድናቂዎች ከሚወዷቸው ድምፃውያን ጋር የሚገናኙበትን እድል የሚፈጥር መሆኑ ዋንኛው ነው ብሏል፡፡ ድምፃውያኑ ከሮሃ ባንድ ጋር በጋራ በሚያቀርቡት በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ከ10ሺ በላይ ታዳሚዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከኮንሰርቱ ገቢ 10 በመቶ አገር በቀል ለሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ለመስጠት መታሰቡንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
ከኮንሰርቱ መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ የሚያስታውስና በተለይም በ1970ዎቹና 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚዘጋጅ የአንድ ሰዓት ትኩል ዘጋቢ ፊልም እንደሚዘጋጅና ሲዲውም ከኮንሰርቱ መጠናቀቂያ በኋላ በሚዘጋጅ የምስጋና ፕሮግራም ላይ እንደሚመረቅ የኮንሰርቱ አዘጋጆች በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚዘጋጀው ኮንሰርት ከተጠናቀቅ በኋላ በ3 ዋና ዋና የክልል ከተሞች ተመሳሳይ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

Read 1177 times