Sunday, 07 May 2017 00:00

ሳፋሪ አዲስ ሆቴል በቅርቡ ሥራ ይጀምራል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹ለሠራተኞቻችን በምንሰጠው ልዩ ትኩረት እንለያለን››
                      
     በእንግዶች፣ በሠራተኞችና አብረውት በሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ተመራጭ እንዲሆን በትጋት እንደሚሰራ የጠቆመው ሳፋሪ አዲስ ሆቴል፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተገልጿል።
የሳፋሪ አዲስ ሆቴል ልዩ አማካሪ አቶ ዜናዊ መስፍንና የሆቴሉ ማኔጅመንት አባላት ባለፈው ማክሰኞ በቦሌ መንገድ ከቴሌ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የሆቴሉ አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የሆቴሉ ዓላማ ልዩ አገልግሎት በመስጠት በሆቴል ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግና የአገሪቱን ቱሪዝም ገጽታ መቀየር ነው ብለዋል፡፡
በ1,3000 ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈው የዚህ ሆቴል ግንባታ 6 ዓመት እንደፈጀ የጠቀሱት የሆቴሉ ልዩ አማካሪ አቶ ዜናዊ፣ አሁን ዝግጅቱን አጠናቅቆ ግንቦት 5 በይፋ ስራ ይጀምራል ብለዋል፡፡
ሳፋሪ ማለት እንደ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ፐርልና መሰል ማዕድናት የከበረ ድንጋይ ስያሜ ነው ያሉት ልዩ አማካሪው፤ ላለፉት 30 ዓመታት በወርቅና የከበሩ ድንጋዮች ንግድ ላይ ተሰማርተው የቆዩት የሆቴሉ ባለቤት አቶ ፍስሐ አባይ፣ ለሥራቸው ክብርና ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሆቴሉን ‹‹ሳፋሪ›› ብለው መሰየማቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆቴሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 64 ደሉክስ፣ 8 ባለ ሁለት አልጋ (ትዊንስ)፣ 26 ሱትና 24 ስታንዳርድ የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፣ ረዥም ጊዜ የሚቆዩ እንግዶች፣ ምግባቸውን የሚያዘጋጁባቸው 8 አፓርትመንት ክፍሎች ከተሟላ የወጥ ቤት ዕቃዎች ጋር ተደራጅተው ይጠብቋቸዋል፡፡
2 ሬስቶራንቶችና 3 ባሮች ያሉት ይኼው ሆቴል፤ ከ20-50 ሰዎች ማስተናገድ የሚችሉ አራት አዳራሾች ያሉት ሲሆን በሆቴሉ ላረፉ እንግዶችና ለውጭ ተጠቃሚዎች የጂምናዚየምና የስፓ  (ስቲም፣ ሳውና፣ ጃኩዚ ማሳጅ) አገልግሎት በባለሙያ ይሰጣል፡፡  ለወንዶችና ለሴቶች የፀጉር ውበት፣ የእጅና የእግር ጥፍር ማስዋቢያ አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡
ሆቴሉ፣ 60 መኪኖችን ማቆም የሚችል ስፍራ ሲኖረው፤  ቦታው በሆቴሉ ለሚያርፉና ለውጭ እንግዶች ይበቃል ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ዘናዊ ሲመልሱ፤ ‹‹ሆቴሉ ቢዝነስ ስታይል ነው። በርካታ መኪና ማቆሚያ የሌላቸው የዚህ ዓይነት ሆቴሎች በአሜሪካም ሆነ በሌሎች አገራት በብዛት አሉ›› ብለዋል፡፡
በግንባታ ወቅት ለ700 ሰራተኞች የሥራ ዕድል እንደፈጠረ የጠቀሱት ልዩ አማካሪው፤ ‹‹ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ200-230 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ሳፋሪ አዲስ፤ ለሠራተኞቹ የላቀ ልዩ ትኩረት ይሠጣል›› ብለዋል፡፡
እኛን ልዩ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ፣ ከእንግዳውም በላይ ለሰራተኞቻችን የምንሰጠው የቅድሚያ ትኩረት ነው፡፡ ምክንያቱም በማኔጅመንቱ አስተዳደር ደስተኛ ያልሆነ ሰራተኛ፤ እንግዶችን በጥሩ ሁኔታ አያስተናግድም፡፡ ስለዚህ ሠራተኞቹ፣ የባለቤትነት ስሜት ተሰምቷቸው፤ ‹‹ሆቴሉ የኛ ነው›› ብለው እንዲቀበሉ፣ ከደሞዝና ከደረጃ ዕድገት በተጨማሪ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ የስራ ላይና ከውጭ አገር ባለሙያ አስመጥተን ሥልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ በዚህ ዓይነት የሠራተኞችን ፍልሰት እንቀንሳለን ብለን እናምናለን›› ብለዋል- አቶ ዜናዊ፡፡
‹‹ከሠራተኞች 40 በመቶ ያህሉ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የሆቴል ሥራ ልምድ የሌላቸውና እኛው እዚሁ ያሰለጠንናቸው ናቸው፡፡ የቀጠርናቸው ሰራተኞች ከትምህርና ከሥራ ልምድ ባሻገር ከ7 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አቀላጥፈው የሚናገሩ ናቸው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ምናልባትም በአዲስ አበባ የመጀመሪያው እንደሆነ የሚነገርለት ግዙፍና እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተገጠሙለት የላውንደሪ ክፍሉ፤ ለሠራተኞች ዩኒፎርም፤ ለእንግዶችና ለውጭ ተጠቃሚዎች አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል፡፡

Read 2806 times