Sunday, 07 May 2017 00:00

ኡጋንዳ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን፣ 6 ጋዜጠኞችን አስራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የኡጋንዳ ፖሊስ ባለፈው ረቡዕ የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ለማክበር በመዲናዋ ካምፓላ ወደሚገኙ ጎዳናዎች ከወጡ የአገሪቱ ጋዜጠኞች መካከል ስድስቱን ማሰሩን ኒውስዊክ ዘግቧል፡፡
የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን የት ይከበር በሚለው ጉዳይ ላይ በኡጋንዳ የጋዜጠኞች ማህበር አመራሮች መካከል ልዩነት መፈጠሩን ተከትሎ፣ የተወሰኑ የማህበሩ አባላት ዕለቱን ለማክበር ወደ አደባባይ ወጥተው በአመራሮቻቸው ላይ ተቃውሟቸውን ባሰሙበት ወቅት የከተማዋ ፖሊስ “ሰልፉን ለማካሄድ ህጋዊ ፈቃድ አላገኛችሁም” በሚል ስድስት ያህል ጋዜጠኞችን ማሰሩን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የከተማዋ ፖሊስ በፕሬስ ነጻነት ቀን በጋዜጠኞች ላይ የወሰደው እርምጃ የመንግስት ባለስልጣናትን ማስቆጣቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለስልጣናቱ ባስተላለፉት ፈጣን ትዕዛዝ ጋዜጠኞቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው በሰዓታት ልዩነት ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፈው ሳምንት ባወጣው የ2017 የአለማችን አገራት የፕሬስ ነጻነት ደረጃ  መሰረት፤ ኡጋንዳ በፕሬስ ነጻነት ከአለማችን 180 አገራት 112ኛ ደረጃን መያዟንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1288 times