Wednesday, 04 April 2012 09:31

ድህነትን መቀነስ ለኢህአዴግ “እንጀራው” ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነው - የኢቴቪን “ልማታዊ ዜናዎች” ቁጭ ብዬ እኮመኩማለሁ፡፡ እናም ኢቴቪ ደህና ሄደ ሄደና ድንገት “ጣቢያ ቀየረ”  (ወደ አረብ ሳይሆን ወደ ኪራይ ሰብሳቢዎች ዜና ከመሬት ዝርፊያ፣ እንዲሁም ከጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ተቋማት የገንዘብ ምዝበራ ጋር የተገናኘ ነበር - ዜናው፡፡ ሙስናው የተፈፀመው  የት መሰላችሁ? ደቡብ ነው፡፡  ጊዜው ደግሞ አሁን - በኢህአዴግ ዘመን! (ድህነት ሲጨምር ሙስና ይስፋፋል ያለው ማን ነበር?) እናም … ኢህአዴግ “አምናቸዋለሁ” ብሎ ከመለመላቸው “የስልጣን ሠራዊት” አባላት አንዳንዶች ፓርቲው የጣለባቸውን እምነት አፍርሰው የሙስና ሰለባ መሆናቸውን በሃይለኛው እየሰማን ነው!  በኢቴቪ የሰማሁትን የሙስና ዜና ልንገራችኋ! የሙስና ሱሰኞች 90ሺ ካ.ሜ የሚሆን መሬት የሞጨለፉ ሲሆን በፀረሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ ጥረትና “እርብርቦሽ” 41ሺ ካ.ሜ መሬት ተመላሽ እንደሆነ ሰምቻለሁ (ብራቮ ፀረ-ሙስና!)

በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ተቋማት ውስጥ ተፈፀመ የተባለው ሙስና ግን በ1ለ5 የአደረጃጀት ስትራቴጂ የተፈፀመ ነው የሚመስለው፡፡ እንዴ በአንድ ተቋም 15 ሃላፊዎች እኮ ነው የተሳተፉበት! ይገርማችኋል … የሌሉ ማህበራትን አሉ እያሉ ነበር የገንዘብ ምዝበራውን የፈፀሙት (መረጃው የኢቴቪ ነው!) እኔማ ቢቸግረኝ “የሙስና ሰራዊት” በህቡዕ የሚያደራጅ ተቋም ተፈጠረ እንዴ አልኩ? (ለራሴ!) ምን ልበል ታዲያ?

በነገራችሁ ላይ 1ለ5 አደረጃጀትን በምርጫ ወቅት መጠቀም ምንም ችግር እንደሌለው የስትራቴጂው ብቸኛ “ፈጣሪ” የሆነው አውራው ፓርቲና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን መግለፃቸውን ሰምቼ ተደምሜአለሁ (ሌላ የምሆነው ስላጣሁ ነው!)

የሙስና ነገር ሲነሳ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ በቅርቡ በአገራችን የሙስና ችግሮች ላይ ጥናት ማካሄዱን የገለፀልን የውጭ ተቋም አለ ወይስ ሄዷል? (ሊሄድማ አይችልም!) ሄዶም ከሆነ ግን በአፋጣኝ ተጠርቶ ይምጣ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ያልጨረሰው ስራ አለው - ከሙስና ጋር የተያያዘ፡፡ ሥራው ምን መሰላችሁ? … ኢህአዴግ በ20 ዓመት የስልጣን ዘመኑ በአቅምና በችሎታቸው ሳይሆን በ”ታማኝነታቸው” (ታማኝነት ለትዳር እንጂ ለስልጣን ምን ይሰራል?) ከሾማቸው ባለስልጣናት መካከል ምን ያህሉን በሙስና ከሃላፊነታቸው እንዳስነሳቸው ጥናት አድርጐ ውጤቱን በፐርሰንት ቢነግረን፣ ወሮታውን አለም ባንክ ወይም IMF ይከፍልልን ነበር፡፡ (በዶላር!) ጥናቱ እስኪሰራ ግን እኔ ግምቴን ልነግራችሁ እችላለሁ፡፡ (ያለ ምንም ጥናት!) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን “ሙሰኛ” ባለስልጣናት ከስልጣን በማውረድ የትኛውም የአገራችን መንግስታት ከኢህአዴግ ጋር ፈጽሞ ሊወዳደሩ አይችሉም! ሌላው ቀርቶ ወደፊት ሥልጣን የሚይዝ መንግስትም ቢሆን አይወዳደረውም የሚል ግምት አለኝ (ይሄኛው እንኳን ጥናት ያስፈልገዋል!) በነገራችሁ ላይ ባለፈው ሳምንት ሙስና ላይ ያነጣጠረ መጣጥፍ በዚሁ ጋዜጣ አንብቤአለሁ፡፡ ፀሃፊው፤ መንግስትም ሆነ ኢህአዴግ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና የመዋጋት ቁርጠኝነት የላቸውም ብለው በእርግጠኝነት መግለፃቸው ግን በእጅጉ አሳዝኖኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? ቆይ ቁርጠኝነት ባይኖረው ኖሮ ይሄን ሁሉ ባለስልጣን በሙስና እየገመገመና እያስገመገመ ከሃላፊነት ያስነሳ ነበር? በእርግጥ አብዛኞቹ ወደ ፍ/ቤት ሳይሆን ወደ ሌላ መ/ቤት ነው የሚላኩት፡፡ ለዚህም ቢሆን አቶ ሬድዋን ሁሴን ሰሞኑን “አጥጋቢ” ምላሽ ሰጥተውበታል “ግለሰቦቹን በፍ/ቤት ለመክሰስ የሚያበቃ በቂ ማስረጃ የለንም!” የሚል፡፡ (ከሌላቸው ምን ያድርጉ?)

በደቡብ ቅድም ከነገርኳችሁ ሙስና ጋር በተያያዘ የተያዙትን ሙሰኛ ሃላፊዎች  በተመለከተ አንዲት ነዋሪ የሰጡት አስተያየት በእጅጉ አስደምሞኛል፡፡ “ሃላፊዎቹን እንደ በፊቱ ከቦታ ቦታ ከማዘዋወር የመዘበሩትን የህዝብ ሃብት ነጥቆ መቅጣት ይገባል” ነው ያሉት፡፡ ልክ ናቸው፡፡ እሳቸው ያልገባቸው ግን የማስረጃ እጦት መኖሩን ነው፡፡”

እኔ የምላችሁ… የሙስናና የሽብርተኝነት መመሳሰል አልገረማችሁም? ቁጭ አንድ ናቸው እኮ! ሁለቱም ማስረጃ በቀላሉ የማይገኝባቸው ወንጀሎች ሆነዋል! (ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ምን እንዳሉ ልብ ይሏል) “በሽብርተኝነት መሰማራታቸውን እያወቅን በማስረጃ እጦት ያልከሰስናቸው የ”መድረክ” አመራሮች አሉ (ልብ አድርጉ! የጠ/ሚኒስትሩን ሃሳብ እንጂ ቃላቸውን ቃል በቃል አልቀዳሁም!)

ስለሽብርተኝነት ሲነሳ የአሜሪካ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የነበሩት ኮሊን ፖል የተናገሩት ትዝ አለኝ፡፡ በአንድ አገር ላይ ሽብርተኝነት የሚስፋፋው የሰዎች የነገ ተስፋ ሲጨልምና ድህነት ሲበዛ ነው ብለዋል፡፡ (ለጠቅላላ ዕውቀታችሁ ብዬ ነው!) እኔ የምለው … ሰሞኑን በድህነት ላይ ይፋ የተደረገውን የጥናት ሪፖርት እንዴት አያችሁት? የእናንተን ባላውቅም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ክፉኛ አብጠልጥለውታል፡፡ በነገራችሁ ላይ በድህነት ላይ ጥናት መደረጉን የሚነቅፉ አንዳንድ ወገኖች እንዳሉ መረጃ አለኝ (እዚህ ሳይሆን ባህር ማዶ) ቢል ቫግሃን የተባለ አሜሪካዊ ከእነዚህ ወገኖች ይፈረጃል፡፡ “ድሆች፤ እሱን ለማጥናት ከሚወጣው ወጪ ግማሹ እንኳን ቢደርሳቸው እንዴት አሪፍ ነበር” ሲል ይተቻል፡፡ (ልብ በሉ! ግለሰቡ የአገራችን ጥናት ላይ ያለው ነገር የለም) የነፃነት ታጋት የነበሩት ደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ ስለ ድህነት ያሉትን ደግሞ ልንገራችሁ! “እንደባርነትና አፓርታይድ ሁሉ ድህነትም ተፈጥሮአዊ ሳይሆን ሰው ሰራሽ ነው፡፡ ስለዚህም የሰው ልጅ በሚወስደው እርምጃ ሊጠፋ ይችላል” የሰሞኑን ጥናት ያደረጉት የአ.አ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ግን ድህነት ይቀንሳል እንጂ አይጠፉም!” ሲሉ ሰምቻለሁ (ለምን ተስፋ ያስቆርጡናል!)

“ድህነት በ20 በመቶ ቀንሷል” የሚለውን የመንግስት ሪፖርት የተቃወሙ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አንዷን ጋዜጠኛ ምን አሏት መሰላችሁ? “ህዝቡን ለምን አትጠይቂውም” ለነገሩ ግለሰቡ እውነት አላቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ህዝቡ “ልክ ነው! ድህነቴ ቀንሷል!” ካላለ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት “ዳታ መጋገር ብቻ ነው” የሚሆነው፡፡

እኔ እኮ…ሰሞኑን ይፋ በተደረገው የ”ድህነት ቀነሰ” ሪፖርት ላይ፤ ጥናቱ ያነጣጠረው በከተሞች ላይ ብቻ መስሎኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን 4 ሚ. ህዝብም ከድህነት ወጥቷል መባሉን ሰማሁ፡፡ በነገራችን ላይ በቀናነት ከተሰራ እኮ ድህነት 20 በመቶ መቀነስ ብቻ ሳይሆን ብልፅግና 80 በመቶ ሊጨምርም ይችላል፡፡

እንዲህ ቀደም ሲል እንዳልኩት ድህነት 20 በመቶ ቀንሷል በሚል የወጣውን ጥናት  ተቃዋሚዎች አጥላልተውታል (ህገ መንግስታዊ መብታቸው ስለሆነ!) እኔ እነሱን ብሆን ግን መብቴ ስለሆነ ብቻ ዝም ብዬ አላጥላላም ነበር፡፡ ይልቁንም ለኢህአዴግ የሆነ “ቦንብ ጥያቄ” አቀርብለታለሁ፡፡ ምን የሚል መሰላችሁ? “ሪፖርቱ ትክክለኛ ከሆነ ከድህነት ወጡ የተባሉትን 4ሚ ሰዎች በቴሌቪዥን አቅርቧቸው!” እለውና ጉዱን አይለታለሁ፡፡ ማቅረብ ካልቻለ ግን “ድሮም የፈጠራ ዳታ መጋገር ትችልበታለህ!” ብዬ እወርፈው፡፡ ክፋቱ ግን እኔ ፀሃፊ እንጂ ተቃዋሚ አይደለሁም፡፡

ሃቁን ልንገራችሁ አይደል … አውራው ፓርቲ ድህነትን ለማጥፋት ምንም አልሰራም የሚል አቋም የለኝም - እንደ ተቃዋሚዎች፡፡ የኢህአዴግ ችግር ምን መሰላችሁ? ሰራሁ የሚለውን ነገር ሪፖርት ሲያደርግ ከልክ በላይ የማጋነን አባዜው ነው፡፡ ለምሳሌ እነ IMF የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት 7 በመቶ ነው ሲሉ፤ አውራው ፓርቲ “የለም 11 በመቶ ነው” ይላል - ሽጉጡን ገትሮ፡፡ (ክፉ አመል!)

ኢህአዴግ ልፋ ብሎት ነው እንጂ… ድህነትን ማጥፋትም በሉት የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት …ኦስካር የሚያሸልመው ውድድር ሳይሆን “እንጀራው” ነው፡፡ ያንን ካልፈፀመ የፈለገ “የምርጫ ሠራዊት” ቢያደራጅ “ወግድ ከስልጣን” መባሉ አይቀርም፡፡ (እቺን እንኳን እሱም አያጣትም! እናም አውራው ፓርቲ ማናቸውንም የልማት ስራዎች ሲሰራ፣ የዲሞክራሲ ስርዓት የሚጠናከርባቸውን መንገዶች ሲቀይስ፣ የቁስና የመንፈስ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ሲጣጣር … አገራዊውም ሆነ ዓለማቀፋዊ ዝናን ለመቀዳጀት (ለማትረፍ) ከሆነ ቀልጧል! ለምን መሰላችሁ? ሥራው ነዋ!

ኢህአዴግ የማጋነን አባዜ ተጠናውቶታል ብያችኋለሁ አይደል! ከቅርብ ክስተቶች አንድ ማስረጃ ላቅርብላችሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ላይ ለመምህራን የደሞዝ ጭማሪ ማድረጉን በየሚዲያው ሲያውጅ ምን አለ? “የደሞዝ ጭማሪው የመምህርነትን ሙያ የሚያስከብር ነው” ብሎ ለእያንዳንዱ መምህር 1ሺ ብር ጭማሪ ያደረገ መስሎ ቁጭ አለ፡፡ ውጤቱስ? መምህሩ ተንጫጫና አረፈው፡፡ ምነው ሲባል? ጭማሪው ከ140 ብር የሚበልጥ እንዳልሆነ ተናገሩ፡፡ አያችሁልኝ የአውራው ፓርቲን ክፉ አባዜ! (ዝም ማለት እየቻለ እኮ ነው) ለነገሩ ስለደመወዝ ጭማሪው የተጋነነ መግለጫ ባይሰጥም ቅሬታው መነሳቱ አይቀርም ነበር፡፡ (የመብት ጥያቄ ነዋ!)

አንዳንዶች እንደሚያምኑት የመምህራን ማህበሩ በአውራው ፓርቲ ጥላ ሥር የተጠለለ  ቢሆን እንኳ የመምህራኑን የመብት ጥያቄ ማፈን እንደማይችል ማወቅ ነበረበት፡፡ መምህሩን በ1ለ5 ቢያደራጅም ለውጥ የለውም፡ ኢህአዴግን ለመደገፍም እኮ መምህሩ በልቶ ማደር አለበት፡፡ ኢህአዴግን ለመደገፍ የኑሮ ውድነቱን ተቋቁሞ መኖር ብቻ ሳይሆን ህይወቱን ማሻሻልና መለወጥ አለበት፡፡ የመደራጀት ጥቅሙም ሆነ ፋይዳው ይሄው ብቻ እኮ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከአርቲስቶቹ ጋር ሲወያዩ ምን እንዳሉ አታስታውሱም? “መብታችሁን ለማስከበር ተደራጁ!”

የዛሬውን ፖለቲካዊ ወጌን ከመቋጨቴ በፊት እስቲ አንድ ጥያቄ ልሰነዝር፡፡ ለኢህአዴግ ሳይሆን ለናንተ - ለአንባቢዎቼ! “አውራው ፓርቲ ቀን ተሌት ተቃውሞ አታሳጣኝ እያለ ይፀልያል የሚባለው እውት ነው እንዴ?” እስቲ አስቡት … ድሃውን የቤት ባለቤት የሚያደርግ የሊዝ አዋጅ አወጣሁ ሲል - ተቃውሞ! የአገሪቱ ድህነት ቅነሳ የሚያሳይ ጥናት ሲያቀርብ - ተቃውሞ! ለመምህራን ደሞዝ ጨመርኩ ሲል - ተቃውሞ! በ1ለ5 አደረጃጀት የምርጫ ሰራዊት የመፍጠር ዕቅዱን ሲናገር - ተቃውሞ!

ከውጭ አገር ቃል በቃል የተቀዳ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ሲያወጣ - ተቃውሞ! ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር አዲስ የግብር አጣጣል ደንብ ጀመርኩ ሲል - ተቃውሞ! ለስድስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርሻው ቆንጥሮ 1ሚ. ብር ሲለግስ - ተቃውሞ! በ95 ነጥብ ምናምን ምርጫ አሸነፍኩ ብሎ ሲያውጅ - ተቃውሞ!... ተቃውሞ! ተቃውሞ!

ይሄ የተቃውሞ ውርጅብኝ በአጋጣሚ የመጣም ይሁን የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ፓርቲው አንድ መፍትሄ ማፈላለግ ያለበት ይመስለኛል፡፡ እስከዛው ግን እኔ የመጣልኝን ሃሳብ ልሰነዝር፡፡ ለምን “የፀሎት ሠራዊት” አያደራጅም?” - ከየሃይማኖት ተቋማቱ የተውጣጡ! ከዚያም… ሁሉም እንደ እምነቱ ለኢህአዴግ ይፀልያል - ከተቃውሞ ውርጅብኝ እንዲላቀቅ!! በዚህ ሃሳቤ ካልተስማማ ግን እንደ ፍጥርጥሩ!! እኔ በበኩሌ ከዛሬ ጀምሮ በግሌ ፀሎቱን እጀምራለሁ (ለፀሎት ፈቃድ ማውጣት የለብኝም አይደል!) ሰናይ ሰንበት ለሁላችንም!!

 

 

Read 2944 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 09:34