Sunday, 07 May 2017 00:00

የአገራችን ፕሬስ፤ ፈተናዎችና ተስፋዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 25 የተከበረውን የዓለም የፕሬስ ቀን ምክንያት በማድረግ የአገራችን ፕሬስ ወዴት እያመራ ነው? ፈተናዎቹና ተስፋዎቹስ ምንድን ናቸው? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ምሁራንን፣የሚዲያ ባለሙያዎችንና የመንግስት ኃላፊዎችን አስተያየት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው
አጠናቅሮታል፡፡

               “መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን፤ ወደ ኋላ አንመለስም”
                  አቶ ዘሪሁን ተሾመ (የዛሚ ሬዲዮ ባለቤትና የፖለቲካ ተንታኝ)

      የ25 ዓመቱ የፕሬስ ነፃነት እድገትና ጉዞ ቀጥ ያለ መስመር አይደለም፤ ወጣ ገባ የበዛው ነው፡፡ በፕሬስ ነፃነቱ ማግስት የበቀለበት ሜዳ፣ የፖለቲካ ዳመናው የበዛና ጎራ ያስለየ ስለነበረ ፕሬሱ የዚያ ሰለባ ሆነ። ይሄን ለመቅጣት ደግሞ በመንግስት በኩል ወደ አስተዳደራዊ እርምጃዎችና መጋተቶች የተሄደበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ተመጋግበው ብቅ ያለውን ያህል የላቀ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ሳይሰጥ በመቅጨጭ በመነሳት ሂደት ውስጥ ነው የመጣው፡፡
እንደ ጅምር በውድቀትም በስኬትም መለማመድ መቻላችን ትልቅ ግኝት ነው፡፡ ሊከበር፣ እውቅና ሊሰጠው ይገባዋል፡፡ ግን በሁለቱ ዋና ተዋናዮች ማለትም በፕሬሱና ተቆጣጣሪ በሆነው የመንግስት ክፍል እንዲሁም በሦስተኛ ደረጃ በአንባቢውም በኩል የነበሩ ችግሮች፣ፕሬሱ እስከ ዛሬ ለሆነውና ዛሬ ላይ ለሚገኝበት ምክንያት ናቸው፡፡
በእርግጥ የዕድገት ሂደቱ በብዙ ሀገሮች ቀጥተኛ አይደለም፡፡ የኛ ሀገርን ለየት የሚያደርገው ጥርሱን የነቀለው በፖለቲካው ነው፤ ሲኮስስም ሲነሳም በፖለቲካው ነው፡፡ በተለምዶ ፕሬስ ከፖለቲካ ወገንተኝት የራቀ ነው የሚለውን ትንታኔ ባልቀበለውም፣ በአመዛኙ ፖለቲካዊ ወገንተኝነቱ እንዳለ ሆኖ፣ ፕሬስ ለማንም ፓርቲ ቃል አቀባይ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ በተረፈ በተለይ ዛሬ ላይ ህገ መንግስቱ ያሰፈረውን የፕሬስ ነፃነት ልክ የመዘንጋት አዝማሚያ በሥራ አሥፈፃሚው አካባቢ ይታያል፡፡ ይሄ አደጋ ነው፡፡ የመዘንጋት ብቻ ሳይሆን ሆን ብሎም ዘንግቶ፣ ምናልባትም ትናንት የቀድሞ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ በገለጹት፣ ”ሰዶ የማሳደድ አስተዳደራዊ እርምጃ”፣ እየቀጨጨ የመጣውን ፕሬስ፣ አናቱን ለመቀጥቀጥ መሞከር ሌላው አደጋ ነው፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ሙያተኞች፣ የየራሳቸውን ስራ ትተው፣ አብረው ካሁኑ እንዲህ ነው መሆን ያለበት እያሉ መሄድ ይገባል፡፡ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን፡፡ ፕሬስም ይሄንን ተሻግሮ የተሻለ ዘመን ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚህ ወደ ኋላ አንመለስም። እንድንመለስ የሚፈልግ ቢኖር እንኳ አንመለስም። ለወደፊት እንግዲህ የተስፋ ዋንጫ ሁለት ነው፤ ተስፋዬ የተትረፈረፈ ነው አልልም፤ በጣምም የሞላ ነው አልልም፤ ድርብብ ነው፡፡


------------------

                       “የህትመት ሚዲያው ተስፋ ይኖረዋል ብዬ አላስብም”
                           እንግዳወርቅ ታደሰ (የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር)

      አሁን ብዙ ሰው ጥገኛ የሆነው በማህበራዊ ድረገፆች መረጃ ላይ ነው፡፡ የህትመት ሚዲያውን ለመከተል ቴክኖሎጂው ያሰነፈው ይመስላል፡፡ የህትመት ሚዲያው ደግሞ በህትመት፣ በስርጭት የራሱ ችግር አለበት፡፡ በሌላ በኩል ጋዜጦች ይሄን ሁሉ ተቋቁመው አንገታቸውን ቀና አድርገው ሊሰሩ ሲፈልጉ፣ አንገታቸውን ይመታሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁመው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቀጠሉ 3 እና 4 ጋዜጦችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ደግሞ አስቸኳይ የሆነ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖሩ ነው፡፡ ፍላጎቱ ያለ አይመስልም፡፡
ልማታዊ የሚለው ፅንሰ ሀሳብ ብዙ ነገሮች ውስጥ እየገባ ነው፡፡ “ሚዲያዎች ሊቀጥሉ የሚችሉትም ልማታዊ በሚለው አስተሳሰብ ውስጥ ብቻ ነው” የሚለው ገዥ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። በልማታዊ አስተሳሰብ መስመር ውስጥ ያልገባ ሚዲያ፤ ለወደፊትም የመቀጠል ዕድሉ አነስተኛ ይመስላል፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት 7 መፅሔትና ጋዜጦች ተዘግተው፤ ወደ 30 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ተሰደዱ፣ ግማሾቹም ክስ ተመስርቶባቸው ታሰሩ። ይሄ ግብታዊ እርምጃ ነበር፡፡ መንግስት ነገሮችን ችሎ የማስተናገድ አቅም እንደሌለው ያሳያል፡፡ ደረቅ እውነታው ይሄ ነው፡፡
እኛ የምናስተምራቸው ልጆች ወደ ስራው አለም ገብተው ስናያቸው፣ የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው የሚሰሩ ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ ኢቢሲ ላይ የሚሰሩ ተማሪዎቻችን ሁኔታ እናስተውላለን፡፡ ለእንጀራ ብለው ነው የሚሰሩት፡፡ የቤቱን ስርአት ለመከተል ሲሞክሩ ነው የሚታዩት፡፡ በህትመት ሚዲያው ግን ጥቂቶች ናቸው ቀጥለው የቆዩት፡፡ የቀጠሉትም ቢሆኑ የቆዩበት የየራሳቸው ምክንያት አላቸው፡፡ ግን አካሄዳቸው ደህንነት ያለውና ጤናማ አይመስልም፡፡
በብሮድካስቱ በኩል አሁን ላይ እንደ አሸን እየፈሉ ያለ ይመስላል ግን አሁንም ማነቆዎችና ገደቦች አሉ፡፡ ለምሣሌ የፖለቲካ ጉዳይ የሚያነሱ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሃይማኖት ተቋማትም የራሳቸው መሰል መገናኛ አውታሮች እንዲኖራቸው አልተደረገም፡፡ ልክ ህግ የማይገዛው ይመስል እነዚህ ጉዳዮች አሁንም ለኛ ሀገር አስፈሪ ተደርገው ነው የሚወሰዱት፡፡
ለወደፊትም ቢሆን የህትመት ሚዲያው ተጠናክሮ የሚመጣ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የሚዲያ ፖሊሲው ለዚህ የተመቻቸ አይደለም፡፡ ጋዜጦችን የሚያነበው ሰው አብዛኛውን ጊዜ ወይ ፖለቲከኛ አሊያም በፖለቲካ ጉዳይ ፍላጎት ያለው ሰው ነው፡፡
ሌላ ፍላጎት ያለው አብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ጥገኛ ሆኖ ነው የምናየው፡፡ የህትመት ሚዲያ ባህርይ ደግሞ ትንተና ማቅረብ ነው፡፡ አሁን ያሉት ጥቂት ጋዜጦች የዚህ ባህሪ አላቸው፡፡ እኔ የመንግስት ቁርጠኝነት ካልታየ በስተቀር በነፃ ሚዲያው ማበብ ላይ ተስፋ የለኝም፡፡ ማህበራዊ ድረገፆች ተቆጣጣሪ ስለሌላቸው የበርካቶችን ቀልብ እየገዙ ነው፤ የበለጠ እየተስፋፉ እንደሚሄዱ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ኢንተርኔት ያለ ቁጥጥር መረጃ ማስተላለፊያና መቀበያ መንገድ ነው፡፡ የህትመት ሚዲያው ግን ተስፋ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡

-----------------

                 “የታሰሩ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው”
                  አቶ ወንድወሰን መኮንን (የኢነጋማ ፕሬዚዳንት)

     አሁን ባለው ሁኔታ ስለ ሀገራችን ፕሬስ ብዙ ማውራት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ 3 ጋዜጦች ናቸው ያሉት። ሚዲያው በሞኖፖል የተያዘ ነው፤ ብዝኃነት የለውም። ይህም ብዙ ድምፆች እንዳይሰሙ አድርጓል፡፡ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ መስክ በልማቱ ያስመዘገበቻቸው ታላላቅ ስኬቶች አሉ፤ ፕሬሱን በተመለከተ ግን ይሄ ስኬት የለም፡፡ ጥቂቶች ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት እየታሰሩም እየተንገላቱም ቢሆን የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ አሁን ያሉት ጋዜጦች ግን ተደራሽነታቸውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እርግጥ ነው በህግና በፖሊሲ ደረጃ ወደ ዘርፉ ለመግባት እድሉ አለ፡፡ ሆኖም በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያለው እምብዛም ነው፡፡
ጋዜጠኛው አለ ነገር ግን በየቦታው ተበትኗል፤በሀገር ውስጥም በውጭም፡፡ አሁን እንደውም የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሙያዎች ማህበርን ለማቋቋም እየታሰበ ነው፡፡ ይሄ ምናልባት ባለሙያውን በማሰባሰብ ረገድ ሚና ይኖረው ይሆናል። ግን አሁን የግሉ ፕሬስ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ የግሉ ፕሬስ ቢኖር ኖሮ፣ ይሄ የምንሰማው የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና፣ የፍትህ እጦት ችግሮች በቀነሱ ነበር፡፡ እውነታው ግን ጠንካራ የግል ፕሬስ እንዲኖር አይፈለግም፡፡
ምናልባት ኤፍኤም ጣቢያዎች አካባቢ አንድ ሁለት የምንጠቅሳቸው፣ ማህበራዊ ጉዳይን አንስተው የህዝብ አጀንዳ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ግን እሱም ቢሆን በቂ ነው ማለት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ የዓለም የፕሬስ ቀን በዋናነት በዓለም ዙሪያ የታሰሩ፣ የተገደሉ፣ በእስር ቤት ውስጥ እየተሰቃዩ የሚገኙ ጋዜጠኞች የሚታወሱበት ነው፡፡ ስለ ፕሬስ ነፃነት የበለጠ የሚቆምበት ቀን ነው፡፡ ጋዜጠኛ መልዕክተኛ ነው፡፡ ጋዜጠኛን ማሰቃየት ለማንም የሚጠቅም አይደለም፡፡
አሁን ለምሳሌ ከሰሞኑ የወጣ አለማቀፍ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት ከአለም 150ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ይሄ ገፅታን ያጠፋል፡፡ መንግስት ይሄን ለማሻሻል መስራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን ያህል ጋዜጠኞች አስራለች የሚለው ለአገሪቱ ገፅታ ጥሩ አይደለም። የታሰሩ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው፡፡ የእነሱ በእስር መቆየት ለሀገሪቷ የሚበጃት ነገር የለም፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች ከእስር ቢፈቱ ምን አለበት? ምን ችግር ይፈጥራሉ? የሚመጣ መአት አለ? የለም! መንግስት ሆደ ሰፊ ሆኖ ጋዜጠኞቹን መፍታት አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮች ከቀጠሉ ህመም ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የሚዲያ ካውንስል መቋቋም አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም የሚዲያ ካውንስል ተብሎ የተቋቋመው ትክክለኛ አይደለም፡፡ የአሳታሚዎች ማህበር ቁጥር 2 ነው የተቋቋመው፤ ስለዚህ እውነተኛ የሚዲያ ፕሬስ ካውንስል መቋቋም አለበት፡፡ የሚዲያ ካውንስል ባለድርሻ መሆን ያለባቸው ባለቤቶች ሳይሆኑ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡

-----------------------

                    “በፕሬስ ነፃነት ወደ ኋላ እየተመለስን ነው”
                        በላይ ማናዬ (ጋዜጠኛና ጦማሪ)

      የፕሬስ ነፃነት ቀን ግንቦት 25 በአለማቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ መሰረት ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል እንደመሆኗ በስም ደረጃ ቀኑን እንደምታከብር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ቀኑን ከማክበር በዘለለ ቀኑ የሚከበርበትን አላማ በሀገራችን እያየን ነው ወይ? የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር ዋና መርሆው ነፃነቱን ማስተጋባት፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም፣ መንግስታት ለፕሬስ ነፃነት የሚኖራቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንፃር ኢትዮጵያን ስናይ በጣም ወደ ኋላ የቀረን ነን፡፡ እንዲያውም ወደ ኋላ እየተመለስን ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ነፃ ፕሬስ የለም ቢባል ይቀላል፡፡ በጣም ጥቂቶች ናቸው ያሉት፤ እነሱም ቢሆኑ የፈለጉትን ሀሳብ በነፃነት ይፅፋሉ ለማለት አያስደፍርም፡፡
ይሄን በምንነጋገርበት ሰዓት እንኳ በሀገራችን በአስሮች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ነው ያሉት፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ጌታቸው ወርቁ፣ ካሊድ መሃመድ፣ ዳርሰማ ሶሪ፣ ኤልያስ ገብሩና ሌሎችም ጦማሪያን የሆኑ እንደ ዘላለም ወ/አገኘው አይነትም አሉ፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች ሀሳባቸውን በመግለፃቸው እንደታሰሩ ነው እኔ የማምነው፡፡ ለምሳሌ ተመስገን ደሳለኝ በፍ/ቤት ሲበየንበት ሙሉ ለሙሉ የቀረበበት ማስረጃ፣ በጋዜጣው ያተማቸው ፅሁፎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች በፃፉት ምክንያት ለእስር ይዳረጋሉ የሚለውን በሚገባ ያሳያል፡፡ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውም ቢሆን የፃፋቸው ፅሁፎች ናቸው ፍ/ቤት ማስረጃ ሆነው የመጡት፡፡ ሌሎቹም ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ስለዚህ የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፤ ወደ ኋላ እየተመለሰ ነው ማለት ይቀላል፡፡ ለወደፊት ያለው ተስፋ ላይም አሁን ከሚታየው የተለየ እንድንጠብቅ የሚያደርጉ ነገሮች የሉም፡፡ ምክንያቱም የሚወጡ ህጎች ከህገ መንግስቱ የተጣረሱ ናቸው፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 29 (የፕሬስ ነፃነትን የሚገልፀውን) ለመተግበር አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ለእስር የተዳረጉትም ይሄ አዋጅ ተጠቅሶባቸው ነው፡፡ ይሄም በሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ከለላ ያለን መተማመን እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ ለወደፊትም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምንቀጥል ይመስለኛል፤አዲስ አይነት የህግ አሰራር እስካልተዘረጋ ድረስ ማለት ነው፡፡

------------------------

                    “የሚፈለገውን ያህል ሚዲያ መፍጠር አልቻልንም”
                        አቶ ዛዲግ አብርሃ (የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚ/ር ዴኤታ)

     የሀገራችን ፕሬስ የአጭር ጊዜ ታሪክ ያለው ነው። የ26 ዓመት ታሪክ ነው ያለው፡፡ በዚህ አጭር ጊዜም በርካታ ነገሮችን ያሳለፈ ፕሬስ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በርካታ የህትመት ሚዲያዎች እንደ አሸን የፈሉበት ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ፕሬስ ተጣሞ የበቀለ ፕሬስ ነበር፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንደ መልካም እድል ተጠቅሞ ህዝቡን የማገልገል ሚና አልነበረውም፡፡ በጦርነት ስልጣን የማስጠበቅ እድል ያጣው የደርግ ኃይል፤ ይሄን እድል ጠልፎ የወሰደበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡
የግሉ ፕሬስ በመሰረታዊነት በደርግ ፕሮፓጋንዳ መምሪያ ባልደረቦች የተወረረበት ጊዜ ነበር። እንግዲህ የሀገራችን ፕሬስ ነፃነቱን ማጣጣም የጀመረው በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ነው፡፡ በወቅቱ ወደ ነፃነት ያመጣውን መንግሥት፤ በስሙ እንኳ ለመጥራት የሚፀየፍ፣ ለመንግሥት እውቅና የማይሰጥ፣ በየአጋጣሚው የለውጥ ዳንኪራ የሚደልቅ ፕሬስ ነው የነበረው፡፡ ይሄ ሁኔታ እያደር እየጠራ መጥቶ፣ ከ97 በኋላ በተወሰነ መልኩ ለውጥ አሳይቷል ማለት ይቻላል፡፡ ፅንፈኛው ፕሬስ በሂደት እየሞተ፣ ቦታው በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ሚዛናዊ ዘገባ ለማቅረብ በሚሞክሩ ሚዲያዎች የተያዘበት ሂደት ነው የነበረው፡፡ ይሄ ሂደት በአመዛኙ መልካም ቢሆንም ከቁጥር አንፃር ውስንነት ታይቶበታል፡፡ እንደ ህዝባችን ብዝሀነት በርካታ ድምፅ የሚሰማበት፣ በብዛትም በጥራትም የሚፈለገውን ያህል ሚዲያ መፍጠር አልቻልንም፡፡
በብሮድካስቱ ዘርፍ በርካታ ነገሮች ተቀይረዋል። የኤፍኤሞች ቁጥር ጨምሯል፡፡ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም በብዛት እየመጡ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በርካታ ጋዜጦችና መፅሄቶች ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እውቅና እየወሰዱ ነው ያሉት፡፡ እነዚህ የሚዲያ ኢንዱስትሪውን ይቀላቀላሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ በአጠቃላይ መንግስት በዚህ ረገድ ችግር መኖሩንና መቀየር እንዳለበት አምኖ፣ የረዥም ጊዜ የሚዲያ ሪፎርም እቅድ ለማውጣት ዝግጅት እያደረገ ነው የሚገኘው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሀገራችን የፕሬስ ነፃነት እንዲያብብ፣ ፕሬስ በምቹ ሁኔታ እንዲሰራ የሚያስችል ምህዳር ለመፍጠር እየተሰራ ነው፡፡
 ህብረተሰባችን በጣም “ፖለቲካል” የሆነ ህብረተሰብ ነው፡፡ በአገሩ ጉዳይ መምከር የሚፈልግ ህብረተሰብ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ፍላጎትና ዝንባሌ ያለው ህብረተሰብ ቁጥሩ እየጨመረ ነው ያለው። ይሄ ለፕሬስ ነፃነት አንዱ አጋጣሚ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ መንግሥትም ደግሞ መዋቅራዊ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችል የረዥም ጊዜ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሪፎርም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሄ፤ ማነቆዎችን አስወግዶ መልካም እድሎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡

Read 1079 times