Sunday, 14 May 2017 00:00

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያላትን የሃይማኖት አንድነት ልትመረምር ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

• በሥርዓተ ጥምቀት፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያደረገችው ስምምነት ሲኖዶሱን አወያየ
• “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ” የሚለው ቀኖና፣ ከፍትሐ ነገሥቱ ይወጣል
• በግል አታሚዎች ስሕተት የተጨመረባቸው ፥ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንዲስተካከሉ ታዘዘ
• ስለ አቡነ ጳውሎስ እና ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚያወራው ‘ተኣምረ ማርያም’ ይገኝበታል

በክርስትናው የነገረ መለኰት እና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ፣ የቆየ የታሪክ ግንኙነትና የዶግማ አንድነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በትምህርተ ሃይማኖት ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት መካከል እየታየ ነው ያለው ልዩነት እንዲመረመር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አዘዘ፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ምልአተ ጉባኤው ትእዛዙን የሰጠው፣ ምሥጢረ ጥምቀትን በተመለከተ፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በካይሮ የተፈራሙትን የጋራ ስምምነት የቅርብ መነሻ በማድረግ በተካሔደ ውይይት ነው፡፡
የካቶሊኩ ፖፕ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት፣ ከኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፖፕና የእስክንድርያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ጋራ የተወያዩ ሲሆን፤ ከተፈራረሙት ባለ12 አንቀጾች የጋራ ስምምነት ውስጥ፣ አንዱ የሌላውን ምእመን ጥምቀት ላለመድገም የተስማሙበት አቋም(shared baptism) እንደሚገኝበት ተገልጿል። በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የሥርዓተ ጥምቀቱ አፈጻጸምና የሃይማኖት ምስክርነቱ፣ መሠረታዊ ልዩነት እንዳለው የገለጹ ምንጮች፤ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አካሔድ፣ የነገረ መለኰትና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ባላቸውና ኦሪየንታል ተብለው በሚታወቁት፥ የኢትዮጵያ፣ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶሶች ያልተመከረበት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
በሥርዓተ ጥምቀት ላይ የሚፈጠረው ልዩነት፣ በሌሎቹ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በሚኖረው አንድነት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ምንጮቹ ጠቅሰው፥ በሥርዓተ ቊርባን፣ ከአዳማዊ የሃጢአት ውርስ አንጻር የድንግል ማርያም ቅድስና፣ የካህናቱ ሥነ ምግባር (ሲጋራ ማጤስ)፣ የመሳሰሉት ኻያ ያህል ልዩነቶች በውይይቱ ወቅት እንደተነሡ ከቀደሙት ታላላቅ አባቶች አስተምህሮ ጋራ ያላቸው መጣጣም ጥያቄ ማሥነሳቱን አመልክተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው በሚያካሒደው ስብሰባ፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በትብብር መሥራቱ እንዲጠናከር፣ በተለይም ከግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ለቆየው ግንኙነት ትኩረት እንዲሰጠው ቢያሳስብም፣ በትምህርተ ሃይማኖት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚታዩት ተናጠላዊ አካሔዶች አንጻር ዶግማዊና ቀኖናዊ አንድነቱ እንዲመረመር ስምምነት ተደርሶበታል፤ የሊቃውንት ጉባኤውም፣ ልዩነቶቹን አጥንቶ ለቀጣዩ ዓመት የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ግብጻውያን በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ በጣልቃ(ሥርዋጽ) የጨመሩት ነው የተባለው አንቀጽ በቀጣይ የመጽሐፉ ኅትመቶች እንዲቀር መወሰኑ ተገልጿል። “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ” የሚለው ሥርዋጹ፣ በግብጾች
እንደሚነገረው፣ በኒቂያ ጉባኤ 42ኛ አንቀጽ ያልተወሰነ፣ ሐሰተኛ ቀኖና ነው፤ ተብሏል፡፡
በአራተኛው ክፍለ ዘመን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄና ፈቃድ በግብጽ ከተሾመው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኋላ እስከ 1951 ዓ.ም. ይሾሙ የነበሩት ጳጳሳት ግብጻውያን እንደነበሩ ያስታወሱት ምንጮቹ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ከሥራቸው ለማድረግ ከአገራቸው ነገሥታት ጋራ መክረው ያስገቡት መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከራሷ ልጆች የራሷን ፓትርያርክና ጳጳሳት መሾም ከጀመረች ግማሽ ምእት ዓመት የተቆጠረ በመኾኑ፣ ሥርዋጹ፣ በቀጣይ ኅትመቶች እንዲቀር ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል። በስንክሳር የሚያዝያ 10 ቀን ንባብ፣ ከንጉሥ ሐርቤ ጋራ በተያያዘ ያለውም ያለውን ታሪክ፣ በተመሳሳይ መልኩ ከኅትመት እንዲወጣ መወሰኑ ታውቋል፡፡     
በሌላ በኩል፣ በግል አታሚዎች እየታተሙ በሚወጡ የጸሎትና የሥርዓት መጻሕፍት ውስጥ ተጨምረዋል የተባሉ ተኣምራት፣ አግባብ ያልኾኑ የሕዝቦች መጠሪያዎች የመሳሰሉት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ የተፈጸሙና አስተምህሮዋን የሚፃረሩ እንደኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንደመከረበት ተገልጿል፡፡ በግል አታሚዎቹ የቀድሞዎቹን ትክክለኛ ቅደጂዎች በሚያፋልስ መልኩ ለኅትመት የዋሉት፥ የስንክሳር፣ የራእየ
ማርያምና የተኣምረ ማርያም መጻሕፍት የተጠቀሱ ሲሆን፤ የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስንና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ከቀኖናዊ አሠራር ውጪ በማካተት የታተመው ‹ተአምረ ማርያም› በአስረጅነት ተነሥቷል፤ በሊቃውንት ጉባኤም ተጠንቶ እንዲቀርብ መወሰኑ ታውቋል፡፡


Read 4694 times