Sunday, 14 May 2017 00:00

ኢቢሲ የፓርላማውን ጉዳዮች ለምን በአግባቡ እንደማይዘግብ እንዲያስረዳ ታዘዘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በኮርፖሬሽኑ አሰራር ጣልቃ የሚገቡ እጃቸውን ይሰብስቡ ተብሏል
         ኢቢሲ የፓርላማውን ጉዳዮች ለምን በአግባቡ እንደማይዘግብ የሚያስረዳ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮቹ ምክር ቤት በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ታዘዘ፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን ቀደም ሲል የሠብአዊ መብት ኮሚሽንና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከህዝብ ክንፍ ጋር ያደረጉትን ምክክር ሙሉ ይዘት ያለማቅረብና በምክር ቤቱም ሆነ በቋሚ ኮሚቴዎች የሚተላለፉ ማናቸውም ውሣኔዎች ተገቢውን ትኩረት አግኝተው፣ ይዘታቸው
ሳይዛነፍ፣ የማስተላለፍ ጉድለት እንደታየበት የገመገመው ም/ቤቱ፤ ለዚህ ችግር ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በመለየትና እርምጃ በመውሰድ ችግሩን በተሟላ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሄ ሃሳብ ያካተተ ሪፖርት በ15 ቀን ውስጥ ይቅረብልኝ ብሏል፡፡
በምክር ቤቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ለምን የአንድ ሰዓት ቋሚ የአየር ጊዜ ተመድቦላቸው እንደማይተላለፉ ለማወቅ እንደሚፈልግም ም/ቤቱ ኢቢሲን በተመለከተ ከባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሣኔ ሃሳብ ባፀደቀበት ወቅት አስታውቋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ አሠራር ላይ በተለየ መልኩ ጣልቃ የሚገቡ አካላትም እጃቸውን እንዲሰበስቡ ም/ቤቱ አሳስቦ፤ ተቋሙ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በግልፅነት እንዲወጣ አሳስቧል፡፡  በተቋሙ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ስለሚያስፈልግም ኮርፕሬሽኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ አሳስቧል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ኮርፖሬሽኑ የህዝብንም ሆነ የመንግስትን ፍላጎት በተገቢው ማርካት አልቻለም ያለው ምክር ቤቱ፤ በምርመራ ሪፖርቱ ሚዛናዊና ትክክለኛ የሆነ መረጃ ለህብረተሰቡ የማድረስ ችግር፣ እንዲሁም የጋዜጠኞች የስነ ምግባር ጉድለትና የብቃት ማነስ እንዳለበትም ጠቁሟል፡፡


Read 3584 times