Sunday, 14 May 2017 00:00

በላይአብ ሞተርስ በአገር ውስጥ የገጣጠማቸውን የኪያ ሞዴል መኪኖች ለገበያ አቀረበ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

    አገር በቀሉ በላይአብ ሞተርስ የኪያ ሞተርስ ኮርፖሬሽን ሞዴል የሆኑትን ሁለት አውቶሞቢሎች ሪዮና ፒካንቶ የተባሉትን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
ከትናንት በስቲያ ማምሻውን በሸራተን አዲስ በተካሄደው መኪኖቹን የማስተዋወቅ ሥነ - ሥርዓት የበላይአብ ሞተርስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቃዱ ግርማ፣ በአሁኑ ወቅት  “ታይገር ኖዝ” የተባሉትን ሁለት የኪያ ሞዴል መኪኖች፡- ሪዮና ፒካንቶ ገጣጥመው ለገበያ ማቅረባቸውን ጠቅሰው፤ በ2010 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ታዋቂ የሆኑትን ሴዳን የመኪና ሞዴል ማለትም ሴራቶ፣ ለስፖርት አገልግሎት የሚውሉና ዘርፈ ብዙ
አገልግሎት ያላቸውን መኪኖች ለማቅረብ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡
ኪያ ሞተርስ ኮርፖሬሽን በአሜሪካ ቀዳሚ ከሆነው የመኪና አምራች ኩባንያ ከፎርድ ጋር በጋራ መሥራት ከጀመረ በኋላ፣ በዓመት 1.5 ሚሊዮን መኪኖችን እንደሚያመርት ጠቅሰው፣ ኪያ፣ በ8 አገሮች 13 የመኪና ማምረቻና መገጣጠሚያ፣  በ172 አገሮች መሸጫና አገልግሎት መስጫዎች ፣
ዓመታዊ ገቢው 14.6 ቢሊዮን ዶላርና 40,000 የሙሉ ሰዓት ተቀጣሪ ሠራተኞች እንዳሉትና የኪያ መኪኖች በ2013 “ኢንተርናሽናል ካር ኦፍ ይር አዋርድ” ማሸነፉን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በ150 ሚሊዮን ብር ገጣጥሞ ለገበያ ያቀረባቸው መኪኖች ለኢትዮጵያ መንገዶች ፋሽን ናቸው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ መኪኖቹ ሰፊ የቀለም ምርጫ፣ ውበት፣ ጥንካሬ፣ ምቾት፣ በፈለጓቸው ጊዜ መገኘት የሚችሉ፣ በአውቶማቲክና በእጅ ማርሽ የሚሠሩ መሆናቸውን፣ የሚገጣጠሙት መኪኖች ለ150 የአንድ ፈረቃ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን፣ ፈረቃው ከአንድ በላይ ከሆነ የሰራተኞቹ ቁጥር ከዚህ እንደሚበልጥና እነዚህን መኪኖች የሚገዙ ሰዎች በአገር ውስጥ ከሚሸጡ ተመሳሳይ መኪኖች ጋር ሲነፃፀሩ ከ15-20 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ፤ ሌሎችም ጥቅም አሏቸው በማለት አብራርተዋል፡፡
በላይአብ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የ11 ወንድማማችና የአንድ እህት የቤተሰብ ቢዝነስ ሲሆን “በላይ አብ” የሚለው ስም ለሟች አባታቸው ለአቶ በላይ ሀብተ ጊዮርጊስ መታሰቢያ የተሰየመ ነው፡፡ ኢንቨስትመንት ግሩፑ፣ 11 ኩባንያዎች ሲኖሩት፣ አምስቱ ትላልቅ ኩባንያዎች፣ በላይአብ ኤሌክትሪክና ዳታ ኬብል፣ በላይአብ ሞተርስ፣ ጎልደን ቱሊፕ አዲስ አበባ ሆቴል፣ ሊኮን ኮንስትራክሽን ግሬድ BC-2 ኮንትራክተርና ሌዊስ
ኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ ሳፕላይ ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡
እነዚህ አምስቱ ኩባንያዎች የተመሰረቱበት ካፒታል 579 ሚሊዮን ብር ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታላቸው መስሪያ ካፒታላቸውን ጨምረ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ ከ1ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ 

Read 11739 times