Sunday, 14 May 2017 00:00

ንግድ ባንክ በዘጠኝ ወር 11.2 ቢ. ብር ከታክስ በፊት ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

    የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 11.2 ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ፣ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ሪፖርት፤ የሀገሪቱን የልማት ፕሮጀክቶች በፋይናንስ በመደገፍ፣ የባንክ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ በማስፋፋትና በቴክኖሎጂ የተደገፉ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸም የተቀማጭ ሂሳብ በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ለተያዙ ፕሮጀክቶች ብድር ለማቅረብ የሚረዳውን አቅም በማጎልበት ከ58.6 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን፣ ይህ ክንውን የባንኩን ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት 288.5 ቢሊዮን ብር ወደ 347.1 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስታውቋል፡፡፡
ባንኩ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 48.1 ቢሊዮን ብር ከብድር ተመላሽ የሰበሰበ ሲሆን ተመላሹን ገንዘብ በብድር መልክ ወደ ኢኮኖሚው በማስገባት ስኬታማ ተግባር በማከናወን 64.3 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ለልዩ ልዩ መስኮችና ደንበኞች ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ከወጪ ንግድ፣ ከሀዋላ፣ ከምንዛሬ ግዢና ከሌሎች አገልግሎቶች የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ባደረገው ጥረት 3.3 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቅሶ፣ ከዚህ
ውስጥ 469.3 ሚሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ፣ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ከሀዋላ የተገኘ መሆኑን ገልጿል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 49 አዲስ ቅርንጫፎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመክፈት የባንኩን ቅርንጫፎች ብዛት ወደ 1,186 ያደረሰ መሆኑን ጠቅሶ፣ በባንኩ ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞች ቁጥር 15 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡  

Read 3070 times