Sunday, 14 May 2017 00:00

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ስለ አክሰስ ኩባንያ ዛሬ ሪፖርት ያቀርባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“ላለፉት 5 ዓመታት ስለ ኩባንያው ምንም መረጃ አልነበረንም” ባለአክሲዮኖች
   የአክሰስ ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ፣ በባለአክሲዮኖች ጥያቄ መሰረት፣ ከ5 ዓመት በኋላ ዛሬ ኩባንያውን በተመለከተ ሪፖርትና ማብራሪያ ያቀርባሉ ተባለ፡፡   
በአክሰስ ካፒታል አክሲዮን ስር አስር ፋብሪካዎችና ድርጅቶች እንዳሉ ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የአክሲዮኑ ባለድርሻዎች፤ላለፉት 5 ዓመታት ግን እነዚህ ድርጅቶች ምን እየሰሩና የት እንዳሉ ምንም መረጃ አልነበረንም ብለዋል፡፡  
ኩባንያው የራሱ ጽ/ቤት እንደሌለው የተናገሩት የአክሲዮኑ ባለድርሻዎች፤ኩባንያው በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ ተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ገልጸው፤በንግድ ሚኒስቴር አማካኝነት ግፊት ተደርጎ፣አቶ ኤርሚያስ በዛሬው እለት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ሊያዝላቸው መቻሉን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ሪል ውሃ፣ የፕላስቲክ እቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ፣ የቁም ከብቶች ንግድ፣ የማዕድን ማውጫ ድርጅትና ‹‹ስናፕ ጁስ›› የተባለ ጁስ ማምረቻን ጨምሮ አስር ያህል ድርጅቶች በአክሲዮን ማህበሩ ገንዘብ መቋቋማቸውን የጠቆሙት ባለድርሻዎቹ፤ የመኪና መገጣጠሚያና የህንፃ ግንባታ ኩባንያም በመቋቋም ሂደት ላይ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡  
አክሲዮን ማህበሩ 15 ያህል ተሽከርካሪዎች እንደነበሩትና ኢምፔሪያል ሆቴልም በኩባንያው ስር እንደነበር ጠቅሰው፤ ላለፉት 5 አመታት ግን ስለ ድርጅቱ የቀረበላቸው የኦዲት ሪፖርትም ሆነ ያገኙት የትርፍ ክፍፍል ድርሻ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ አክሰስ ካፒታል ሰርቪስ አክሲዮን ማህበር፣ በአክሰስ ስም ለሚጠሩ ኩባንያዎች በሙሉ መስራች ድርጅት መሆኑን ያስረዱት ከባለድርሻዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ በቀለ እሸቴ፤ አጨቃጫቂ በሆነው አክሰስ ሪል እስቴት ላይም ማህበሩ የ2 ሚሊዮን ብር ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡    
በ1999 ዓ.ም በተቋቋመው በዚህ ዘርፈ ብዙ የአክሲዮን ማህበር፤ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የ47 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የመጨረሻው የአክሲዮን ማህበሩ ስብሰባ የተካሄደው ታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ ማህበሩ 141 ባለድርሻዎች እንዳሉት መገለጹ ተነግሯል፡፡ ለዛሬ በተጠራው የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከሚደመጡት ሪፖርቶች በተጨማሪ አዳዲስ የቦርድ አባላት ይመረጣሉ ተብሏል፡፡   

Read 6500 times