Sunday, 14 May 2017 00:00

ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በመጪው አርብ ድርድር ይጀምራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

      መኢአድ እና ኢዴፓን ጨምሮ 5 ፓርቲዎች 15 አጀንዳዎችን ለድርድር አቅርበዋል
ፌደራሊዝሙ እንደገና እንዲዋቀር አጀንዳ ቀርቧል

   ከገዥው ፓርቲ ጋር ለድርድር የተቀመጡት ኢዴፓ እና መኢአድን ጨምሮ 5 ፓርቲዎች የፀረ ሽብር አዋጁና የፌደራል ስርአቱ እንዲሻሻሉ የሚጠይቁትን ጨምሮ 15 አጀንዳዎችን ለድርድር ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ኢራፓ፣ መኢዴፓ እና ኢብአፓ በጋራ በመሆን በቀረፁት የመደራደሪያ አጀንዳ ላይ በዋናነት የታሰሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ አወቃቀርና አደረጃጀት እንዲሁም የፓርቲዎች የስነ ምግባር መመሪያ እንዲቀየር ከገዢው ፓርቲ ጋር ድርድር እናደርጋለን ብለዋል ፓርቲዎቹ፡፡
የምርጫ ቦርድ አመራሮች በሹመት ሳይሆን በህዝብ ተገምግመው፣ በሙያ ብቃታቸው ተወዳድረው በህዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የሚጠይቅም አጀንዳ በፓርቲዎች በኩል ቀርቧል፡፡
የምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የፍትህ አካሉን የሚመሩ ግለሰቦች በሹመት ሳይሆን በህዝብ ድምፅ ወደ ስልጣን እንዲመጡ የሚጠይቅ የድርድር ሀሳብም በፓርቲዎቹ ቀርቧል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንዲነሳ፣ የፀረ ሽብር ህጉ፣ የሚዲያ አዋጁ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲለወጡም የድርድር ሀሳብ በፓርቲዎቹ ቀርቧል ተብሏል፡፡
የፌደራል አደረጃጀቱ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ቀርቶ በመልክአ ምድርና በህዝብ ውሳኔ እንዲደራጅና አንድ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲመረጥ ፓርቲዎቹ የድርድር ሀሳብ ማቅረባቸው የተጠቆመ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከንግድ እንቅስቃሴ እንዲወጡም ሀሳብ ቀርቧል፡፡
ፓርቲዎቹ አጀንዳዎቹን ቅደም ተከተል በማስያዝ ጉዳይ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመነጋገር ለመጪው አርብ መቀጣጠራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

Read 4850 times