Sunday, 14 May 2017 00:00

የፍትህ ስርአቱ - በህግ ባለሙያዎችና በፖለቲከኞች ዓይን

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሰሞኑን “የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የፍትህ ሳምንት ለ7ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው፡፡ ይሄን መነሻ
በማድረግ የፍትህ ሥርዓቱ ምን ደረጃ ላይ ነው? የህግ የበላይነት ሰፍኗል? ዜጎች በህግ የበላይነት እምነት አሳድረዋል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የህግ ባለሙያዎችና የፖለቲከኞችን አስተያየት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

         ‹‹የሚፈለገውን ያህል የህግ በላይነት የለም››
                     ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

    በአጠቃላይ ያለንበት አገዛዝ አብርሃም ሊንከን፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን በተነተነበት፣ “ለህዝብ ከህዝብ በህዝብ” በሚለው ደረጃ ላይ ያለ አይደለም። የኮሚኒስት አስተሳሰብ ያለው፣ ራሱን ነፃ አውጭ ነኝ ብሎ የሚያስብ መንግስት ነው እስካሁን ያለን፡፡ እንደነዚህ ያሉ የመንግስት አይነቶች ደግሞ በባህሪያቸው ቀኖችንና መፈክሮችን እየፈለጉ፣ ህዝብን ለማደናገር መሞከራቸው የተለመደ ነው። የባንዲራ ቀን፣ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ የነፃ ፕሬስ ቀን፣ የፍትህ ቀን ወዘተ---እያሉ ያከብራሉ፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ሲባልና ለህዝቡ በየጊዜው አጀንዳ ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት እንጂ ቀኑን ሲያዘጋጁ ከልባቸው አምነውበት አይመስለኝም፡፡ ፍትህን፣ ዲሞክራሲን ነፃ ፕሬስን ከመንግስቱ ባህሪ አንፃር በተግባር ለመተርጎም አስቸጋሪ ስለሚሆን በሙሉ ነፃነት ሊፈቅዱ አይችሉም፡፡ ሊያደርጉ የሚችሉት ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ስራ መስራት ብቻ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የሚባለው ነገር በኛ ሃገር ገና አልመጣም፡፡ ህግ እውነተኞችን ለማጥቂያ ብቻ ነው እየዋለ ያለው፡፡
የህግ የበላይነት ላለመኖሩ ማሳያ የሚሆኑት የሃገሪቱ ታላላቅ የፖለቲካ መሪዎች እስር ቤት መሆናቸው ነው፡፡ ጋዜጠኞች እስር ቤት ናቸው፡፡ በህግ የተቋቋሙ ተቋማት፣ ኢ-ፍትሃዊ በሆኑ ህጎች እንዳይሠሩ ተሸብበዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበራት የመሣሠሉትና ንፁህ ‹‹አክቲቪዝም›› የሚያራምዱ ሰዎችን፣ ሚዲያውን የሚያፍኑ ህጎች ወጥተው ለፍትህ መረጋገጥ ምሰሶ የሆኑ ነገሮች ሁሉ የተሸበቡበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ለምሳሌ ከጋዜጠኞች እነ እስክንድር ነጋ፣ ከፖለቲከኞች እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ በቀለ ገርባ፣ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናን የመሳሰሉ ሰዎች እስር ቤት ናቸው፡፡ አሁን እንደውም ለህግ የበላይነት ገና መታገል ያለብን ጊዜ ላይ እንጂ የህግ የበላይነት ሰፍኗል ተብሎ በአል የሚከበርበት ወቅት ወይም አገር ላይ አይደለንም፡፡
የህዝቡ ባህል ከእምነቱ የተቀዳ እንደመሆኑ የመከባበርና የመቻቻል እንዲሁም እውነትን የመፈለግ ስነልቦና አለው፡፡ በእርግጥ አሁን የሚታየው ውሸትን ስርቆትን የሚያበረታታና ሽምግልናን የሚያዋርድ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ሰዎች ለህግ ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ስለወደቀ፣ እነዚያ የሞራል መመዘኛዎች እየተሸረሸሩ በመሆኑ፣ የህግ የበላይነት ማስፈን የማይቻል መስሎ ይታያል። በኔ እምነት የህግ የበላይነትን በዚህ በተያዘው መንገድ ማስፈን አይቻልም፡፡ አሁን ያለው መንግስት ብዙ የሞራል ጉዳዮችን ሸርሽሯል። የሃገር ታሪክን፣ የእምነት ተቋማት ቅቡልነትን፣ ብሄራዊ ስሜትን፣ በህግ ላይ ሰዎች የነበራቸውን መተማመን ሸርሽሯል። እነዚህ ነገሮች ህዝብን ለስልጣን ያሰባስባሉ በሚል እሳቤ ነው እንዲሸረሽሩ የተደረጉት፡፡ ይሄ ለወደፊትም በሚደረግ የሃገር ግንባታ ጥረትና የህግ የበላይነትን የማስፋት ሂደት ላይ ችግር የሚፈጥር ነው የሚሆነው፡፡ ባህላችን ከሃይማኖት የተቀዳ ስለሆነ እንደ አንዳንድ ሃገሮች ፈታኝ የሆኑ የቡድን ወንጀሎችና አስፈሪ ሽብሮች ሲፈጠሩ አናይም፡፡ ይሄ በቀጣይ ለሚገነባው የህግ የበላይነት ተስፋ እንድንሰንቅ ያደርገናል፡፡

------------------

                    “በህግ ልገዛ የሚል አስተሳሰብ አልመጣም”
                     አቶ ተማም አባቡልጉ (የህግ ባለሙያ)

       ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ስርአት ማለት በህግ ብቻ መስራት ማለት ነው፡፡ መንግስትም ቢሆን ከተመረጠ በኋላ ለመረጡትም ላልመረጡትም በእኩል የሚያገለግል፣ በህግ የተገዛ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይሄ ሊሆን የሚችለው በህግ የበላይነት ስር ባሉ መንግስታት ነው፡፡ ወደኛ ሀገር ስንመጣ ይሄ አለ ወይ ብለን በጥልቀት መጠየቅ ያሻናል፡፡
ፍትህ ደግሞ ከዚህም በላይ ነው፡፡ እንዳልኩት የህግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ስለ ፍትህ ብዙ ማውራት አስቸጋሪ ነው፡፡ የሶሻሊዝም ባህሪ ያለው መንግስት፤ ነፃና በህግ የሚመራ የህግ የበላይነት ያመጣል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን እኛ ሃገር ያለው የጭቆና እና የነፃ አውጪነት አስተሣሠብ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ‹‹የአብዮቱን ጥቅም እስከነካ ድረስ አንታገሠውም›› ይባል እንደነበረው፣ አሁንም የመንግስት ስልጣን እስካተነካ ድረስ የህግ ትዕግስት የለም፡፡ በህግ ልገዛ የሚል አስተሣሠብ አልመጣም። ህዝቡን አንቀጥቅጦ ለመግዛት ነው ህጉ ጥቅም ላይ የሚውለው፡፡ አሁን ባለው የኢህአዴግ አስተሳሰብ የህግ የበላይነት በምንጠብቀው መልኩ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ምናልባት አዲሱ ትውልድ አስተሣሠቡ ተለውጦ፣ የህግ የበላይነትንና ነፃነትን ተቀብሎ፣ ለኔ የሚገባው ለሌላውም ይገባል የሚለውን የሚያመጣ ከሆነ ያኔ የምንፈልገው የህግ የበላይነት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ጠላትና ወዳጅ ተባብሎ መፈራረጅ ባለበት በዚህ ወቅት እንዴት ነው የምንመኘው የህግ የበላይነት የሚመጣው? አስቸጋሪ ነው፡፡ የሶሻሊስት አስተሳሰብና የፊውዳል አመለካከት በተጣመሩበት በዚህ ወቅት የህግ የበላይነት መጠበቅ አስቸጋሪ ነው።
ዳኞች ሙሉ ነፃነት አላቸውን? ህገ መንግስቱ እንዲህ ነው የሚለው ብሎ ለየት ያለ ሀሳብ ያቀረበ ዳኛ እኮ በይፋ ተባርሯል፡፡ የፍርሃት ችግር ባለበት ሁኔታ ነፃና ገለልተኛ መሆን እንዴት ይቻላል? ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ገና አልፈጠርንም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የግለሰቦች ነፃነትና ገለልተኛነት እንዴት ይታሰባል? ነፃ አስተሳሰብስ እንዴት ሊመጣ ይችላል? እነዚህ ሁሉ በሌሉበት ስለ ህግ የበላይነት ብዙ መናገር አይቻልም፡፡

--------------------

                     “ህብረተሰቡ ቅሬታ የሚያነሳባቸው አዋጆች መፈተሽ አለባቸው”
                       አቶ አመሃ መኮንን (የህግ ባለሙያ)

      በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የፍትህ ስርአት ያለበትን ደረጃ ለመመለስ ጥናት የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የኔን ምልከታ ለመግለፅ ያህል፣ እንግዲህ የህግ የበላይነት ስንል ብዙ ባለድርሻዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በሂደቱ ውስጥ የህብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የሚያግዙ እንዲሁም የዜጎችን መብት የሚያስከብሩ ህጎችን በማውጣት በኩል ህግ አውጪው (ፓርላማው) ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ አካል እንደማንኛውም ሀገር ባለፉት አመታት ጠቃሚ ህጎች ሲወጡ እንደነበረው ሁሉ አጨቃጫቂ የነበሩና በሰዎች መብት ላይ ጫና የሚፈጥሩ፣ በዜጎች የመደራጀት መብት ላይ ጫና የሚፈጥሩና አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ቅሬታ የሚያነሳባቸው፣ እኔም በግሌ ጥያቄ የማነሳባቸው ህጎች ሲወጡ ነበር፡፡ ምናልባት ህዝብን ለማስተዳደርና የሀገሪቱን ፀጥታ ለማስከበር አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ህጎችን በተመለከተ ብዙም ማለት አልችልም፡፡ ለየት ባሉትና የግለሰቦች መብት ላይ ጫና የሚያደርጉ ህጎችን በተመለከተ በምሳሌነት የፀረ ሽብር አዋጁን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሄ አዋጅ የሽብርተኝነት ድርጊትን በጣም በሰፊው ትርጉም ከመስጠት አንስቶ በሽብርተኝነት የሚጠረጠር ሰው ላይ ምርመራ ለማካሄድ ተብለው የሚቀመጡ በግለሰብ መብት ላይ ጫና የሚያደርጉ እርምጃዎችን ከማካተቱ አንፃር በህግ የበላይነት መረጋገጥ ላይ ጫና ከሚፈጥሩት አንዱ ነው፡፡ የዚህ ህግ በስራ ላይ መዋል በበርካታ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ቅሬታን የፈጠረ ነው፡፡
ሌላው የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት (ሲቪክ ሶሳይቲ) አዋጅ ነው፡፡ ይሄም በግለሰቦች የመደራጀት መብት ላይ ጫና የፈጠረ ነው በሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረ ነው፡፡ የፕሬስ አዋጁም እንደዚሁ ሀሳብን በመግለፅ መብት ላይ ጫና እንደሚያደርግ ቅሬታ ይነሳል፡፡ እኔም አብዛኛውን ቅሬታ እጋራለሁ፡፡ እነዚህ ቅሬታዎች ምን ያህል ታይተው ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቷል? የሚለው መልስ የሚያሻው ነው፡፡  ወደ ህግ አስፈፃሚው ስንመጣ፣ የሚወጡ ህጎችን በእውቀት ላይ በተመሰረተና በቅንነት ከማስፈፀም አንፃር ችግር ይታያሉ፡፡ በተለይ ፍ/ቤት በሚመጡ ጉዳዮች ደግሞ የፍ/ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበር ብዙ ችግሮች ሲታዩ ቆይተዋል። በግልፅ የተቀመጡ ህጎችንም በመጣስ በግለሰቦች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት በመሆን የታዩ በርካታ ጉድለቶች አሉ። ለምሳሌ ከተፈቀደው ጊዜ በላይ ሰውን ማሰር፣ የታሰሩ ሰዎችን መብት አለማክበር የመሳሰሉ ሰፊ ጉድለቶች አሉ። ተጠያቂነትን በማስፈን በኩልም በህግ አስፈፃሚው አካል የህግ ጥሰት የመፈፀሙ ጥቆማ ሲደርስ፣ ችግሩን በፈጠረው አስፈፃሚው አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዳተኛ በመሆን ረገድ እኛም የታዘብናቸው ሰፊ ጉድለቶች አሉ፡፡
ሌላው ህብረተሰቡ ትልቅ አመኔታ ሊያሳድርበት የሚገባው የዳኝነቱ አካል ነው፡፡ ይሄ አካል ብቸኛው ወይም የመጨረሻው የግለሰቦች መመኪያ አካል ነው። ህግ አውጪው አስቀድሜ እንዳልኩት፤ ከተለያዩ መነሻዎች ግለሰቦች ላይ ጫና የሚያሳርፉ ህጎች ሊያወጣ ይችላል፤ ህግ አስፈፃሚውም በአግባቡ ህጎችን ላይፈፅም ይችላል። የዜጎች የመጨረሻው ዋስትና ማለትም ከነዚህ በደሎች የሚጠበቅበት፣ በደል ተፈፅሞበትም ከሆነ የሚከስበት በአጠቃላይ ፍትህ የሚጠይቅበት የህግ ተርጓሚው ወይም የዳኝነቱ አካል ነው፡፡ በዚህ በኩል እንደ ህግ ባለሙያ፣ የእለት ተዕለት ተሞክሮዬም ስለሆነ በጣም የሚያሳስብ ደረጃ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ እንኳ ይሄን ቃለ ምልልስ ስናደርግ፣ ጠዋት በነበረኝ ቀጠሮ ብቻ ከ6 ወር በፊት የአቃቤ ህግን ምስክር ለመስማት የተቀጠረና ተጠርጣሪውም ላለፉት 2 ዓመታት በእስር ቤት ባለበት ጉዳይ ዛሬም ዳኛ አልተሟላም ተብዬ ነው የተመለስኩት። ስለዚህ ሰዎች ህግ ጣሱ ተብለው ይታሰራሉ፤ ነገር ግን የተፋጠነ ፍትህ አግኝተው ንፁህነታቸው ወይም ጥፋተኝነታቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ጥፋተኛ የተባሉም በየደረጃው በተቀመጠው አካል አግባብ ባለው ጊዜ ውስጥ መብታቸውን መጠቀም አለባቸው ግን ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በአጭር ጊዜ ፍትህ አያገኙም፡፡ ውሳኔ አገኙም ከተባለ ውሳኔ ላይ የሚጠቀሱ ሰፊ የጥራት ችግሮች አሉ፡፡ የሙስና ጉዳይም በስፋት የጥራት ችግር የሚነሳበት ነው፡፡ ይሄ እኔ ብቻ የምለው ሳይሆን የፍ/ቤቱ አስተዳደርም በተለያየ ጊዜ የሚገልፀው ነው፡፡ የፌደራል የፀረ ሙስና ኮሚሽንም በአንድ ወቅት ባደረገው ጥናት፤ ኪራይ ሰብሳቢነት ከሚንፀባረቅባቸው አካላት አንዱ የዳኝነት አካል መሆኑን ጠቅሷል፡፡  ከጥናቱም ውጪ እኛ የምንመለከታቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንፃር ሲታይ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 25 ዓመታት የህግ የበላይነት ከማስከበር አንፃር በሶስቱም የመንግስት አካላት በኩል በልዩ ሁኔታ ሊጨበጨብለት የሚያስችል ስራ ተሰርቷል የሚል እምት የለኝም፡፡ ይሄን ስል ምንም የተሰራ ስራ የለም ማለቴ አይደለም፡፡
በየዓመቱ እንግዲህ የፍትህ ሳምንት እንደሚከበር እናያለን፡፡ ግን የፍትህ ሳምንቱ እየተከበረ ያለው ምንን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ በቂ መረጃ የለኝም፡፡ በጥብቅና ሙያ ያለን ሰዎችን እንደ ባለድርሻ አድርጎ የማሳተፍ ችግር አለ፡፡ በአሉ እንግዲህ የቀድሞ የፍ/ቤት ዳኞች የነበሩ ግለሰቦችን ወይም የተለያዩ ስብሰባዎችን ፎቶዎች በመስቀል ሲከበር እንጂ ጠንካራ ጥናቶች ተደርገው ችግሮች በተጨባጭ እንዲፈቱ የሚያስችል መድረክ ሲሆን አላየንም፡፡ የፍትህ ሳምንት ሲከበር ከስኬት ጋር መያያዝ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡

------------------

                “የዳኞች ሥነምግባር ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል”
                   አቶ ወንድሙ ኢብሳ (የህግ ባለሙያ)

      አሁን የፍትህ ሳምንትን ለማክበር የተመረጠው “የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት” የሚለው መሪ ቃል ችግር የለበትም፡፡ ነገር ግን በአሉ ሲከበር ለ7ኛ ጊዜ እንደመሆኑ፣ ይህን መሪ ቃል በሚመጥን መልኩ የህግ የበላይነቱ ከፍታ ማሳየት ነበረበት፡፡ ፖለቲካው ደግሞ እየሰለጠነ ለህግ ብቻ እየተገዛ፣ የህግ የበላይነትን እየተቀበለ፣ ህዝብን እንመራለን የሚሉ ፖለቲከኞች ለህዝቡ ትህትና የሚያሳዩበት ሁኔታ መፈጠር ነበረበት፡፡  
በሌላ በኩል የፍትህ ሳምንቱ እየተከበረ ያለው ሀገሪቱ በአስገዳጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባለችበት ወቅት ነው፡፡ የህግ የበላይነትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አብሮ የሚሄድ አይደለም። አሁን ሀገሪቱ የህግ የበላይነትን በወረቀት እንጂ በተግባር እየተረጎመች አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ ህግ አውጪው፣ ህግ አስፈፃሚውና ህግ ተርጓሚው ለህግ ትህትናን አላሳዩም፡፡ የህግ የበላይነትን ከልብ አልተቀበሉም፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡
ዜጎች ጫና ተፈጠረብን፤የህግ የበላይነት አጣን ብለው በተንቀሳቀሱበት ዘመን፣እንዴት የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ማለት ይቻላል? አሁን ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ስለ ህግ የበላይነት ዜጎች ምን ይላሉ የሚለውን እንዴት ነው መንግስት ያጤነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ’ኮ በመደበኛ ህግ ሀገሪቷን ማስተዳደር አልተቻለም ብለው ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው፡፡
እኔ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በርካታ ደንበኞች አሉኝ፡፡ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ዜጎች በፀረ - ሽብር አዋጁ መሰረት፤4 ወር ወይም 112 ቀናት፣ለ4 ጊዜ ብቻ የምርመራ ቀጠሮ እንዲሰጥ ነው ህጉ የሚደነግገው። ነገር ግን ይሄ አዋጅ በወረቀት ላይ ቀርቷል፡፡ ይሄን የምለው በምሳሌ አስደግፌ ነው፡፡ አንድ ማዕከላዊ የነበረ ተጠርጣሪ፤ 4 ወር ጨርሶ፣ ፍ/ቤት 7 ሺህ ብር አስይዞ ከእስር ይለቀቅ ብሎ ካዘዘ በኋላ፣ ብሩንም አስይዘን ሳይለቀቅ 3 ወር ቆይቷል፡፡ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ባለመፈፀሙ፣ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ አቅርበን ነው የተለቀቀው፡፡ ይሄ የህግ የበላይነትን መፃረር ነው፡፡ የህግ የበላይነት ላለመኖሩም ማሳያ ነው፡፡
እያንዳንዱ ነገር ጥበብ አለው፡፡ ፖለቲካችን ጥበብ የለውም፡፡ ጥሬ ነው፡፡ አልበሰለም፡፡ ፖለቲካው አልበሰለም ማለት ደግሞ ለህግ መታዘዝ የለም ማለት ነው፡፡ የህግ የበላይነት የለም የምልበትን ሌላ ማሳያ በራሴ ከደረሰው ልጥቀስ፡፡ አንድ ወረዳ ዳኛ ጥብቅና በቆምኩበት አጋጣሚ ፀያፍና ክብረ ነክ ስድብ ሰድቦኝ፣ ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ከስሼ፣ እስካሁን ምንም እርምጃ አልተወሰደም፡፡ አንድ ዳኛ የህግ ባለሙያ ጠበቃን እንዲህ ከሰደበ፣ ሌሎችን ሊገርፍም ይችላል ማለት ነው፡፡
ይሄ የሚያሳየው የህግ የበላይነቱ ተግባራዊ ገፅታ እንደሌለው ነው፡፡ ይሄን ስል ትጋት ያላቸው ዳኞች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በፌደራል ደረጃ በትጋት የሚሰሩ አሉ፡፡ የዳኞች ስነ ምግባር ላይ ገና ብዙ ይቀራል፡፡ ሰዎችን ማንጓጠጥ፣ አልባሌ ቃላትን መጠቀም በስፋት ይታያል። ይሄ ለፍትህ አሰጣጡ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኔ በንጉሡ ጊዜ ከአባቴ ጋር ወደ ፍ/ቤቶች እሄድ ነበር፤ በደርግና አሁን ደግሞ ራሴም የህግ ባለሙያ ሆኜ እሰራለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዳኛ ደንበኛን ሲሳደብ ያየሁት አስቀድሜ የገለፅሁት ግለሰብ ነው፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነው። የዳኞች ስነ ምግባር ጉዳይ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ የፍትህ ሂደቱም በጣም አሰልቺና የተራዘመ ነው፡፡  

-----------------------------------

                       “የፍትህ ስርአቱ ዜጎችን ከመንግሥትም የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት”
                      አቶ ሞሼ ሠሙ (ፖለቲከኛ)

      የፍትህ ስርአትን የመገንባት ሂደት የማህበረሰብን ንቃተ ህሊና ከማዳበር ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ፍትህ ልክ እንደ ጤና ፖሊሲ በአብዛኛው ወንጀልን በመከላከል ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን ነው ውጤታማ የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በስፋት የሚታየው ነገር ፍትህ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው ፍ/ቤት ነው፤ ተቋሞቹ ናቸው፡፡ አሁንም በአብዛኛው ስናይ ልክ ትምህርትን ለማዳረስ ት/ቤት በየቦታው እንደሚገነባው፣ ፍትህን ለማዳረስ የፍትህ ተቋማትን ዝም ብሎ የመገንባት ዝንባሌ ነው ያለው፡፡ ብዙ ፍ/ቤቶች መኖራቸው ብቻ የችግሩ መቅረፊያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በነዚያ ተቋማት ውስጥ የሚቀመጡ ባለሙያዎች ፍትህን ለማስፈን የሚኖራቸው ስነ ልቦናዊ ዝግጅት፣ ገለልተኛነታቸው፣ ለህጉ ያላቸው አክብሮት፣ ለማህበረሰቡ ያላቸው አክብሮት የመሳሰሉት ጉዳዮች የሚጫወቱት ሚና በጣም ጥልቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የፍ/ቤት ህንፃ መገንባት ከግንባታ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ዋናው ከፍትህ ህብረተሰቡ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ማስጠበቅ ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡
የፍትህ ስርአቱ ዜጎቹን ከመንግስትም የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግስት ቀላል የማይባል ጉልበት አለው፡፡ ወታደሮች አሉት፤የታጠቀ ኃይል ነው፣ የኢኮኖሚ አቅም አለው፡፡ ዜጎች ይሄን ፈርጣማ አካል ሊቋቋሙበት የሚችሉበት አንዱ አካል የፍትህ ስርአቱ ነው፡፡ የፍትህ ስርአቱ ገለልተኛ መሆን የሚያስፈልግበትም ምክንያት ይሄ ነው፡፡ መንግስት አልፎ ሄዶ የዜጎችን ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዳይደፈጥጥ መከታ የሚሆናቸው የፍትህ አካሉ ነው፡፡
ይሄ አይነት የፍትህ ስርአት የሚፈጠረው መንግስትን ካለመፍራት ነው፡፡ የመንግሥት ተፅዕኖ አለብኝ ብሎ አንድ ዳኛ ፍ/ቤት ለዳኝነት የሚቀመጥ ከሆነ፣ መንግስትን እንዴት ነው መርታት የሚቻለው? በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን በፍትህ መርታት የቻሉ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በተለይ በፖለቲካው ስንመጣ፣ የአብዛኞቹ የሚጠናቀቀው በእስር ቤት ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየን አንደኛ በማህበረሰቡ ውስጥ ለፍትህ ዘብ የመቆም ባህል አለመዳበሩን ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በፍትህ ላይ እምነት ማጣት የፈጠረው ነው፡፡ በፍትህ ላይ እምነት ማጣት የፍትህ ስርአቱን መፃረር ያመጣል፤ በቀላሉ ለወንጀል ተጋላጭ ያደርጋል፡፡ በደርግ የነበረው ችግር ይሄ ነው፡፡ ደርግ የሽምግልና እና የባህላዊ ዳኝነት ስርአትን ሲያፈርስ፣ ወዲያው ህጋዊ የፍትህ ስርአት መተካት ባለመቻሉ፣ የማህበራዊ መሰረቱ ተንዶ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው ወደዚህ ስርአት የመጣነው፡፡
ከዚህ አንፃር ባለፉት 25 ዓመታት የፍትህ ስርአቱን በማጠናከርና ማህበረሰቡ በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ በዚህ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የመንግስት አካላት ተገቢውን ኃላፊነት ወስደው ሚናቸውን አልተወጡም፡፡ ለዚህ ነው አዲስ ነገር ያላየነው። ተቋማቱ በቴክኖሎጂ ተራቀው ሊሆን ይችላል፣ ብዙ ፍ/ቤቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ሰው በየቋንቋው ዳኝነት ሊያገኝ ይችላል።
ይሄ ግን በራሱ ሰዎች በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት ኖሯቸው፣ ጉዳያቸውን ወደ ፍ/ቤት በመውሰድ መፍትሄ የሚፈጥሩበትን መንገድ አመቻችቷል ብዬ አላምንም፡፡ ፍትህ ዳኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ፍትህ ማለት ሰዎች ከዚያም በፊት መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ይሄን በስፋት በማህበረሰቡ ውስጥ ማስረፅ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ካልሆነ የመንግስት ባለስልጣን የማይከሰስበት፣ ተጠያቂ የማይሆንበት፣ በሙስና የተጨማለቁ ሰዎች በአግባቡ የማይጠየቁበት አሊያም እስረኞች በጉቦ ከእስር የሚያመልጡበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡  እርግጥ ነው ከፍ/ቤቶች ባሻገር እንደ ህዝብ እንባ ጠባቂ ያሉ ተቋማት በመንግስት ተቋቁመዋል፤ ነገር ግን በግል የሚቋቋሙ የሰብአዊ መብት ተቋማት በስፋት ሀገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቅሰው የፍትህ ስርአቱ ነፃ እንዲሆን የሚያግዙበት ሁኔታ ካልተፈጠረና የፍትህ ስርአቱ ከመንግስት ጉያ ካልወጣ በስተቀር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
በፍትህ ስርአቱ ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ከፍተኛ መሰላቸት፣ የእምነት ማጣት ፍርሃት እንዳለባቸው ይታያል፡፡ በመጀመሪያ በዳኝነቱ ላይ መተማመን መፈጠር አለበት፡፡ በፍትህ አስፈፃሚዎች ዘንድ በሞራል ልዕልና ፍትህን የማስፈን ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ ማህበረሰቡ እነዚህን ተቋማት እንደ መብት ጠባቂዎቹ እንዲያያቸው ሰፊ የስነ ልቦና ስራ መሰራት አለበት። ተቋማት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ጥረት መደረግ አለበት። ሚዲያዎች በቀላሉ መረጃ አግኝተው፣ ፍትህ እንዳይዛባ ማጋለጥ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተቀናጁበት፣ የፍትህ ስርአቱ በመንግስት ጉያ ውስጥ ሆኖ፣ በቂና ውጤታማ የሆነ ነገር ይመጣል ለማለት ያዳግታል።  የፍትህ ስርአቱ ትልቅ ጉዳይ አድርጎ የሚያየው ለፍ/ቤቶች የሚሰጠውን ትኩረት ብቻ ነው። ነገር ግን ማህበራዊ ፍትህ ከማስፈን አንፃር ብዙ አልተራመድንም፡፡ እዚህ ሀገር በአጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን እየመራ ያለው ገንዘብ፣ ጉልበትና ብሄርተኝነት ነው፡፡ ሰዎች እኩል ናቸው ከሚለው አስተሳሰብ የሚነሳ የፍትህ ስርአት ገና አልፈጠርንም።

---------------------

Read 570 times Last modified on Saturday, 13 May 2017 12:59