Sunday, 14 May 2017 00:00

የአውራምባ ማህበረሰብ በአዲስ አበባ የመሬት ጥያቄ አቅርቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ማህበረሰቡ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ምርቶቹን ለማቅረብ አቅዷል
        የአውራምባ ማህበረሰብ መስራች አቶ ዙምረታ ኑሩ፣ ባለቤታቸውና በማህበረሰቡ እንግዳ ተቀባይ በመሆን የሚሰሩት ወ/ሮ እናነይ ክብረት እንዲሁም የማህበረሰቡ የህብረት
ስራ ማህበር ሊቀ መንበር ወጣት ጌታሰው መሃመድ ሰሞኑን ለስራ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አግኝቷቸው
በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

      ስለ አውራምባ ማህበረሰብ ብዙ ይነገራል። እንደማህበረሰብ ምን ያህል ጊዜ ሆናችሁ ከተመሰረታችሁ?
እንግዲህ እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ በዚህ አስተሳሰብ ነው እድሜዬን የፈጀሁት፡፡ በ1964 ዓ.ም ነው ማህበረሰቡን የመሰረትኩት፡፡ ወደ 53 ዓመት ገደማ ይሆነዋል ማለት ነው፡፡
የማህበረሰቡ ቁጥር ምን ያህል ደረሰ?
ሁለት መዝገቦች ናቸው ያሉን፡፡ ነባር አባላትና አዲስ አባላት በሚል ነው፡፡ በስደትም በሌላ ጉዳይም ተበታት ነው ያሉት በቁጥር አይገለፅም፡፡ የማህበር አባል የምንለው ማለትም አንድ ቦታ ያለነው 514 ነን። በትውልድ ካየነውም 3ኛ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡
ማህበረሰቡ በቁጥር እየሰፋ መሄዱ ከቦታ ከመሰረተ ልማት መሟላት አንፃር ምን ያህል እየሰራችሁ ነው?
እንግዲህ ከ1964 ዓ.ም እስከ 1980 ድረስ ጥሩ ህይወት ነበረን፡፡ በ1980 ዓ.ም ደርግ የወያኔ አባላት ናችሁ ብሎ እኛን ሊያጠፋ ሲመጣ፣ ወደ ደቡብ ቦንጋ አካባቢ ተሰደን ነበር፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር፣ በ1985 ነው በድጋሚ ወደ ቦታችን የተመለስነው። ስንመለስ ግን ንብረታችንን መሬታችንን ማግኘት አልቻልንም፡፡ የእርሻ መሬታችንን ባለማግኘታችን ለገቢ ማግኛ ብለን ወደ ኢንዱስትሪ ዞረን፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን መስራት ጀመርን፡፡ አሁንም በዚህ ስራ ነው ያለነው። እድገታችን ብዙም የተራመደ አይደለም፤ ሀሳባችን ግን ብዙዎች ጋ ደርሷል፡፡ አውራምባ ከዜሮ ተነስቶ ማደግ ይችላል የሚል እምነት ነው ያለው። ኢትዮጵያ ሰፊ ሀገር ነች፤ ለሁላችንም ትሆናለች የሚል እምነት አለን፡፡ ፈረንጅ የተለየ ፍጡር ስለሆነ አይደለም ያደገው፡፡ እኛም ስራን ሳንንቅ ከሰራን አለም ከደረሰበት መድረስ እንችላለን፡፡ አውራምባ ማህበረሰብ ይሄን እልህ ይዞ የሚሰራና የሚራመድ ማህበረሰብ ነው፡፡
የጨርቃጨርቅ ስራዎች እንሰራለን ብለዋል፤ ምን አይነት ነው የምትሰሩት? ለወደፊትስ ምን አቅዳችኋል?
የአንገት ልብሶችና ሹራቦች የመሳሰሉትን እንሰራለን የገበያ ትስስሮሽ ከተፈጠረልን ራዕያችን ትልቅ ነው፤ እስከ ኢንዱስትሪ ማድረስ ነው አላማችን፡፡
መንግስት ለዚህ ስራችሁ ምን ድጋፍ አድርጎላችኋል?
መንግስት ሰርቶ የማደር መብት ሰጥቶናል። በሌላ በኩል መብራት ውሃ ገብቶልናል፡፡ ግን የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ የተወሰደብን መሬት እንዲሠጠን እየጠየቅን ነው፡፡ በአዲስ አበባም መሬት እንዲሠጠንና ስራችንን እንድናስፋፋ እየጠየቅን ነው።
አዲስ አበባ ላይ የጠየቃችሁት መሬት ለምን ጥቅም የሚውል ነው?
አሁንም የመጣነው ይህን መሬት ለመጠየቅ ነው፡፡ የኛ ስራ ከቱሪዝም ጋር የተገናኘ ነው፤ የእደ ጥበብ ስራዎችን የምናቀርብበትና ታሪኮችን የምናስተናግድበት ቦታ ነው የጠየቅነው፡፡ ማሽኖች አቋቁመን ስራችንን የምንሠራበትን ቦታም ነው የጠየቅነው፡፡ አውራምባ የሃገሪቱ ሃብት ነው። ሁላችንም አስተሳሰቡን እንውሰድ እያልን ነው የምንጠይቀው፡፡
አሁን ወደ አካባቢው ምን ያህል ቱሪስቶች ይመጣሉ?
ያን ያህል አይደለም፡፡ ማደሪያም ስለሌለ አበረታች አይደለም፤ አልፈውን ነው የሚሄዱት፡፡
ለመሬት ጥያቄያችሁ ከአስተዳደሩ ምን ምላሽ ተሰጣችሁ?
ገና ጥያቄ ማቅረባችን ነው፡፡ መልሱን እንግዲህ
ለምንድን ነው “ወያኔ” በሚል ደርግ ያሳድዳችሁ የነበረው?
የምናራምደውን አስተሳሰብ ያዩ የአካባቢው ገበሬዎች፤ “ወያኔዎች ናቸው” በሚል ወንጅለውን ነው እንጂ እኛ ገበሬዎች ነበርን፡፡
ምን ያህል ነበራችሁ ወደ ቦንጋ የተሰደዳችሁት?
መጀመሪያ እኔ ነበርኩ የተፈለግሁትና 13 ሆነን ነበር የወጣነው፤ በኋላም ሌሎች ተጨማምረው 48 ነበርን፡፡ እኔ በ1980 ተሰደድኩ፤ ሌሎቹም በዚያው ተከተሉ፡፡ በ1985 ወደ ቦታው ስንመለስ፣ መሬታችን እንደነበረ አላገኘነውም፡፡ የአካባቢው ገበሬዎች ወስደውታል፡፡ ይሄን መሬት ነው አሁን እንዲመለስልን እየጠየቅን ያለነው፡፡ በወቅቱ ግን ያዋጣል ብለን ወደ ሽመና እና ጨርቃ ጨርቅ ገባን፡፡ ግን ከእለት ፍላጎታችን ያለፈ ኢኮኖሚ አልፈጠረልንም፡፡ ብዙም ውጤታማ አይደለንም። አሁንም ቦታው እንዲመለስልን ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ ማህበረሰቡ እየሰፋ ስለሆነ ጥያቄውም እየሰፋ ነው፡፡
ከመቼ ጀምሮ ነው የመሬት ጥያቄ ያቀረባችሁት?
ለክልሉም ለሌላውም አካል ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ነው ማቅረብ የጀመርነው፤ ግን እስካሁን ምላሽ የለም እኛም ጥያቄያችንን አላቋረጥንም፡፡
“አውራምባ ላይ ውሸትና ማጭበርበር የለም”
ኃላፊነቱን ከአቶ ዙምራ ተረክቦ የማህበረሰቡን የህብረት ስራ ማህበር በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ የሚገኘው ወጣት ጌታሰው አህመድ በበኩሉ፤ ማህበረሰቡ ያለውን የኢኮኖሚ አቅምና ተጠቃሚነት በአሃዞች አስደግፎ ያስረዳል፡፡
የማህበረሰቡ ኢኮኖሚን በተመለከተ መጀመሪያ ሲቋቋሙ በነፍስ ወከፍ በአመት 50 ብር ድረስ ነበር ገቢው፡፡ አሁን በራስ ጥረት በአመት በአማካይ 7 ሺህ ብር ደርሷል፡፡ ይሄም በቂ አይደለም፡፡ በወር 7 ሺህ ብር የሚያገኝ ሰው እንኳ ለኑሮው አይበቃውም፡፡ የአውራምባ ማህበረሰብ በሀገሪቱ ታሪክ ለመስራት ነው ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት የሚከፍለው፡፡
የአወራምባ ማህበረሰብ መስዋዕትነት የከፈለባቸው እሴቶች የትኞቹ ናቸው?
የህፃናት መብት፣ የሴቶች እኩልነት በአውራምባ በተግባር እየታዩ ያሉ ናቸው፡፡ ጎዳና ላይ አዛውንቶች መውደቅ የለባቸውም በሚል አሁንም ባለው አቅሙ ሁሉ አዛውንቶችን መንከባከቢያ ማዕከል ከፍቶ እየተንከባከበ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የተባሉ በአውራምባ ዘንድ የሉም፡፡ ለስልጣኔና ለቴክኖሎጂ ቅርብ ነው፡፡ ይሄን ለማሳየት ነው መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው። ይሄን ሲያደርግ የሚፈለገውን ያህል የኢኮኖሚ አቅም ኖሮት አይደለም፡፡ 147 አባወራዎች አሉ፡፡ የዚያ ሁሉ አባወራ መኖሪያ ቤትን ጨምሮ 17.4 ሄክታር መሬት ነው መተዳደሪያው፡፡ ስለዚህ እርሻ የሚባለውን ማሰብ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ሽመናን የገቢ ማግኛው ያደረገው፡፡
ይሄ አስተሳሰብ ይጠቅመናል ካልን ሁሉም … መንግስትም ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሀሳቡን ማስፋፋትና ሀገራዊ ማድረግ አለብን ነው ምክራችን።
በአዲስ አበባ መሬት ስንጠይቅ በኢንቨስትመንት ስም ነው፡፡ የከተማ ቦታ የምንጠይቀው በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ የምንጠይቀውም ለማንኛውም ኢንቨስተር እንደሚሰጠው ለኛም እንዲሰጠን ነው፡፡ ምርቶቻችንን ወደዚህ አምጥተን መሸጥ እንድንችል ነው፡፡ አሁን ደግሞ የተጣራ የኑግ ዘይትም እያመረትን ነው፤ የባልትና ውጤቶችም አሉን፡፡ አውራምባ ላይ ውሸትና ማጭበርበር የለም፤ እኛ ወደ አዲ አበባ ስንመጣ ይሄን አስተሳሰባችን ሰንቀን በሃቅ ህዝብን ለማገልገል ነው፡፡
በኑግ ዘይት ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የምግብ ዓይነት ወደ ገበያው መግባት እንፈልጋለን፡፡ የተለያዩ ምግቦችን በጥራት ለማቅረብ እንፈልጋለን። በከተማው ምን ያህል የምግብ ጥራት ችግር እንዳለ እንሰማለን፡፡ ባዕድ ነገር መቀላቀል የመሳሰሉትን እንሰማለን፡፡ እኛ ይሄን ሁሉ ተፀይፈን በሃቅ መስራትና ማስተማር እንፈልጋለን፡፡ ለከንቲባውም ጥያቄያችንን በዚህ መልኩ አቅርበንላቸዋል፡፡
አሁን ላይ ምን ያህል የተማረ ሰው ነው በናንተ ማህበረሰብ ውስጥ የተፈጠረው?
እኔ እንግዲህ በ1989 ነው አንደኛ ክፍል የገባሁት። እኔ የመጀመሪያው ነኝ፡፡ ከዚያ በፊት ማህበረሰቡ ት/ቤት ስለሌለው በብረት ምጣድ ላይ ልጆቹን በቤቱ ያስተምር ነበር፡፡ ከዚያ ነው እያደገ የመጣውና ት/ቤቶች መገንባት የጀመሩት። አሁን ከ30-40 የምንሆን የማህበረሰቡ አባላት ከዲፕሎማ እስከ ማስተርስ ተምረናል፡፡ ተምረንም ማህበረሰባችን በሚያደርገው ለውጥ ውስጥ እያገለገልን ነው፡፡ እኔ በ2002 ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ነው በዲግሪ የተመረቅሁት፡፡   

Read 600 times