Print this page
Sunday, 14 May 2017 00:00

በጫት ተሸነፍን ይሆን?

Written by  በሲቲና ኑሪ
Rate this item
(11 votes)

     ሰሎሞን የኔነህ (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተቀየረ) ኑሮውን መቐለ ከተማ ያደረገ፣ ወደ አዲስ አበባ በሚመጣባቸው የስራ  አጋጣሚዎች የመገናኘት ዕድሉ ያለን የረጅም ዓመታት ወዳጄ ነው።  በቅርቡ እንደ ወትሮው ሁሉ ከሰሎሞን ጋር ተገናኝተን ስለ ሥራ፣ ኑሮና ልጆች ከተጠያየቅን በኋላ፤ በድንገት:
“ጫት አቆምኩ” አለኝ በድል አድራጊነት ስሜት።
እኔም፤ ‹‹በእውነት?›› አልኩት፤
ፈጠን ብሎ፤ ‹‹አዎ! አቃተኝ! ልጆቼን ከትምህርት ቤት ማምጣት ተሳነኝ፣ እንዴት ልነሳ ጫቱን ትቼ” አለኝ እጆቹን እያወራጨ።
ጫት ሁለመናውን ሽባ አድርጎት እንደነበር ለማወቅ ፊቱን ማየት ብቻ በቂ ነበር፡፡ ሰሎሞን ጫት በዘመናችን ያመጣው ጣጣ አይነተኛ ማሳያ (microcosm) ነው፡፡ ከሰሎሞን ተነስተን ስንቶቹ ከስራ ገበታቸው እንደተፈናቀሉ፣ ትዳራቸውን እንደበተኑና ከኑሯቸው እንደተጣሉ መናገር የአደባባዩን እውነታ መድገም ነው የሚሆንብን።
“The poison leaf”
ብሪታኒያ ወደ አገሯ በዓመት ከሚገባው 2560 ቶን ጫት 2.5 ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ የታክስ ገቢ እንደምታስገባ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ነገር ግን ይህ ትርፍ ጫትን ወደ አገሯ እንዳይገባ ከማድረግ አላገዳትም። ከአንዳንድ የፓርላማ አባላት የቱንም ያህል ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ በመጨረሻም ጫት በአደንዛዥ እፅነት ተመድቦ፣ ከተከለከሉ እፆች ተርታ ለመካተት በቅቷል።  ለክልከላው መሰረት የሆነውም የዓለም የጤና ድርጅት ጥናቶች ናቸው፡፡
ጫትን አስመልክቶ ሁለገብ ርዕሶችን በማካተት ከስምንት ዓመታት በፊት “The Khat Controversy: Stimulating the Debate on Drugs” በሚል ርዕስ በአራት ፀሃፍት የተዘጋጀው ጥናት፤ የጫትንና የአዕምሮ ጤናን ግንኙነት አስመልክቶ 41 የተለያዩ ጥናቶችን ጨምቆ ያቀረበ ሲሆን በውጤቱም ጫት የአዕምሮ ጤና ችግርን አባባሽ ብቻ ሳይሆን ዋነኛ መነሻም እንደሆነ ያስረዳል::
በጫት የጤና ጠንቅነት ላይ እጅግ ብዙ ጥናቶች በተለያዩ ደረጃዎች የተሰሩ ሲሆን፣ ከላይ ካነሳነው በተጨማሪ በሳኡዲ አረቢያው ጃዘል ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያቀረቡት ዶ/ር ሁሴን አጊሌ፤ በየመን ውስጥ በ1118 አዲስ የተወለዱ ህፃናት ላይ የተደረገ ጥናትን ጠቅሰው እንዳመላከቱት፤ በሕፃናቱ ላይ የክብደት መቀነስ እንደሚታይና ይህም የሆነው በእርግዝና ወቅት እናቶች ጫት ተጠቃሚ ስለነበሩ እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዚህም ሌላ የሆድ ድርቀት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ የአዕምሮ እረፍት ማጣት፣ የጥርስ/ድድ (dental cavities) ጉዳት መድረስና የደም ግፊትን የመሳሰሉ የጤና መዛባቶችን እንደሚያስከትል ዶክተሩ “Health and Socio-economic Hazards Associated with Khat Consumption” በተሰኘ ጽሁፋቸው ላይ አበክረው ገልፀዋል።  ከተለያዩ ጥናቶችና የቤተ ሙከራ ግኝቶች በመነሳት የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ጫት፤ “Cathine” እና “Cathinone” የተባሉ አደገኛና መራዥ ንጥረ ነገሮችን መያዙን በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2006 ባደረገው አሰሳም ይፋ አድርጓል።
“Leaf of Allah”
‹‹ጫት ፈጣሪ የሚወደው ዛፍ ነው፡፡ በፈጣሪ ተባርኮ ለእኛ የተሰጠን ውድ ስጦታ፡፡ ይህ የተባረከ ዛፍ ላይ ሰው ምንም ስልጣን የለውም። የተለያዩ ሰዎች ጫትን ለማጥፋትና ለመቆጣጠር ዋጋውን በማናር ጭምር ሞክረዋል፤ ማንም ግን አልተሳካለትም። ጫት እኮ ተራ አትክልት አይደለም፤ ጫት የአላህ ቅጠል (leaf of Allah) ነው፡፡››
ይህን የሚሉን  አደም አልዩ ጄላን የተባሉ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሽማግሌ ሲሆኑ፤ ዶ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳ ከአስራ ሶስት ዓመታት በፊት “Leaf of Allah Khat & Agricultural Transformation in Harerge, Ethiopia, 1875–1991” በሚል ርዕስ ባሳተሙት የጫትን የመቶ ዓመታት የምስራቅ ኢትዮጵያ ታሪክ በሚያወሳው መጽሐፋቸው ካናገሯቸው ግለሰቦች አንዱ ናቸው፡፡ ለሽማግሌው ዓደም ጫት ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና መንፈሳዊ መሰረት የሆነ በፈጣሪ ትዕዛዝ ለሰው ልጆች የተበረከተ ስጦታ ነው። ይህ ስሜት ግን የዓደም ብቻ አይደለም፡፡
ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆቹ መስከረም 2016 የደቡብ ክልልን እንደመነሻ ወስዶ ባስጠናው ጥናት፤ በርካታ ቤቶች የጓሮ አትክልት ልማትን ወደ ጫት ማሳነት መቀየራቸውን ተከትሎ፣ ለምን ወደዚህ ዘርፍ እንደገቡ ጠቅለል ያለ ፅሁፍ አቅርቦ ነበረ። በጥናታዊ ጽሑፉ እንደተመለከተውም፤ በ1980 ከ40 አባወራዎች አንዱ ብቻ የጫት ማሳ እንደነበረው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከ1990 ወዲህ ግን ከ40 አባወራዎች 38ቱ ማሳቸውን ወደጫት ማሳነት እንደቀየሩት ያመላክታል፡፡ ይሄም አዲስ እውነታ ለእንሰትና ለተለያዩ ዛፎች ተይዞ የነበረው ቦታ እንዲቀንስ ማድረጉን ጥናቱ ጠቁሟል። አያይዞም ይህ እውነታ የአካባቢው አርሶ አደሮች ወደ ሌሎች ከተሞች አስቤዛ ሽመታ እንዲወጡ ማድረጉን ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችን ጠቅሶ፣ ይገልጻል። በአስገራሚ ሁኔታም አንድ በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ግለሰብን ጠቅሶ ለ20 ዓመታት በጫት ልማት ላይ እንደነበሩና አሁን ግን ፊታቸውን ወደ ቀድሞ እርሻቸው መልሰው እንዳዞሩ በማተት ለዚህም እንደ ገፊ ምክንያት የሆነው በቤተሰባቸው ውስጥ ለምግብነት የሚውል የአትክልት እጥረት እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ይህ ጥናት  የሲዳማ ዞን ገበሬዎች የጓሮ አትክልታቸውን ወደ ጫት ማሳነት የቀየሩበትን ምክንያት ሲዘረዝር፤ የተሻለ ገንዘብ ማስገኘቱ፣ የዘር አቅርቦትና ማዳበሪያ እጥረት መኖሩ መሆናቸውን የጥናቱን ተሳታፊዎች አጣቅሶ ይገልፃል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ1990 እስከ 2000 ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ የጫት ዋጋ ከ9 ብር ወደ 45 ብር ከፍ ማለቱንና ያም በየ300 ኪ.ሜ ራዲየስ ውስጥ 20 የተለያዩ የጫት ገበያዎች እንዲከፈቱ ምክንያት መሆኑን ያትታል።
ይሄንና መሰል ጥናቶች የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር ጫት የኢትዮጵያን ግብርና ምን ያህል ሊቀይረው እንደሚችልና ራሷን መመገብ ያልቻለች አገር ላይ እንዲህ ያለ ተጨማሪ ፈተና ሲደረብ ደግሞ ‹‹በምግብ ራስን መቻል›› የሚባለውን ጉዳይ ወደ ተረትነት ሊቀይረው እንደሚችል ነው።
“The Dollar Leaf”
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጫት ከቡናና ከጥራጥሬ ምርቶች ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ቅጠል ሆኗል። ‘The Dollar Leaf’ የሚለው ቅጥያውም ዘልቆ እየተሰማ ይገኛል፡፡ ለአገሪቱ አዲሱ የኢኮኖሚዋ ዋልታ ጫት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮችን በየዓመቱ የሚያሳፍስ ቅጠል እንደሆነ የቅርብ ጊዜ መንግስታዊ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የጫት ምርትን ከአገራችን ወደ ውጭ መላክ የተጀመረው በደርግ ዘመን ቢሆንም ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘበት 1983 ወዲህ በዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እያደገ ይገኛል፡፡ በ1983 ዓ.ም  በዘርፉ የወጪ ንግድ ከ56 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ቢሮ መረጃዎች ያመላክታሉ፤ በ2007 ዓ•ም ከጫት ንግድ 332 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም  275 ሺ ቶን ጫት ወደ ውጭ በመላክ፣ ከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ መንግስታዊው ዕቅድ ይጠቁማል።
በዓለማቀፍ ተቋማት እንደ መርዘኛ አደንዛዥ እፅ በሚቆጠር የሰብል አይነት ላይ ይሄን ያህል መደገፍ ለጊዜው ለአገሪቱ ዶላር ቢያመጣላትም ቋሚና ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸውን ምርቶች ወደ ገፍቶ የማታ ማታ አገሪቱን ታላቅ ኪሳራ ላይ እንዳይጥላት የሚያሰጋ ነው፡፡
ጫት በዓለማቀፍ ተቋማት በመርዘኝነት የታወቀ ቅጠል ቢሆንም በኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ምክንያቶች የተነሳ ስርጭቱ እጅግ እየሰፋ መሔዱ የማይካድ እውነት ቢሆንም በዚህ ድምዳሜ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው የሚገልፁ ግለሰቦችም አልጠፉም፡፡ ዶ/ር ኤፍሬም ተሰማ ከእነዚህ ተጠራጣሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ኤፍሬም ለዶክትሬት ማሟያቸው በሰሩት ጥናት ላይ የጫትን አዎንታዊ ጎን ለማጥናት ሙከራ አድርገዋል። አያይዘውም በ1960ዎቹና 70ዎች በነበረው የትግል ንቅናቄ ወቅት ጫት የነበረውን አስተዋፅኦ ይገልጻሉ። በትግሉ ላይ ለነበሩ ወጣቶች ጫት የጀርባ አጥንት እንደነበረ አስረግጠውም ይናገራሉ፣ “ወጣቶቹ ፓምፍሌቶችን በማባዛት፣ ማርክሲስት ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለምን ሌሊቱን ሙሉ እያጠኑ ለመቆየት ጫት አስተዋፅኦ ነበረው” ይላሉ ዶክተር ኤፍሬም። በወቅቱ የነበረው እድገት በህብረት ዘመቻም ወጣቶቹን ከጫት ጋር ለማስተዋወቅ  የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንደነበረው ያትታሉ። በተጨማሪም እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን የሚመዘዝ ታሪካዊ ዳራ ያለውና በአብያተ ክርስቲያናትና በገዳማት እንዲሁም በሙስሊሙ ማሕበረሰብ ውስጥ የተለያዩ አስተዋፅኦ ያበረከተ ቅጠል እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ፡፡ አስከትለውም ጫት ላይ ሕግና ፖሊሲ ከመርቀቁም በፊት ሰፊ ጥናት እንደሚያስፈልግና በዘርፉ ላይ ለመስራት የሚሳተፉ ቡድኖች ጥልቅ ምርምርን አድርገው ‹‹ጫት ይከልከል›› አልያም ‹‹አይከልከል›› የሚለው ነገር ቢወሰን የተሻለ ይሆናል ይላሉ።
ዶክተር ኤፍሬም ለዚህ ሐሳባቸው ሰሚ ያጡም አይመስልም። ባሳለፍነው ዓመት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምሁራን ስብሰባ ላይ የተገኙ ከጎንደር የመጡ መምህር፣ የወጣቱን የጫት ሱሰኝነት ተከትሎ መንግስት ምን እንዳሰበ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የዶክተር ኤፍሬምን ጥርጣሬ በሚያንጸባርቅ መልኩ “ጫትን የመቃወም የመደገፍ አቋም የለኝም፣ ጫት ይጠቅማል፣ አይጠቅምም የሚሉ ወገኖች ምርምር አድርገው ተከራክረው ያሳምኑን። ያኔ በማስረጃ ጎጂ ነው ከተባለ እናስቆማለን፣ እስከዛው ድረስ ግን የሚያስገኘውን ዶላር እየበላን እንቆያለን” የሚል አስገራሚ መልስ ሰጥተው፣ መንግስት ጫትን ለመቆጣጠር ፖሊሲ የማርቀቅም ሆነ ሕግ የማውጣት ፍላጎት እንደሌለው ጠቆም አድርገው ነበር።
ይህ በምዕራቡ ዓለም ከሚታየው የዓለም ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ ከሚነሳው ክርክር ጋር እጅግ ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ ነው ያገኘሁት። ምንም እንኳን ለመቶ ዓመታት እጅግ ብዙ የዓለም ሙቀት መጨመርን አስመልክቶ የተሰሩ ጥናቶች ቢኖሩም አንዳንድ የአየር ንብረት መለወጥን የሚክዱ (Climate change deniers) ሊቃውንት ግን ‹‹የለም፤ የዓለም ሙቀት መጨመር ብሎ ነገር የለም›› ብለው በመካድ ለአንዳንድ ፖለቲከኞች የተሳሳታ የፖሊሲ ግብዓት ሲያቀርቡ ይታያል። ጫትና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶም እጅግ ብዙ ጥናቶች የቅጠሉን ጎጂነት በመግለፅ በአገሪቱ ላለው የአዕምሮ ጤና መዛባት የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝና፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ኪሳራው እጅግ ብዙ እንደሆነ፤ እንዲሁም የንግድና የእርሻ ትስስር ላይ እጅግ አሉታዊ ተጽእኖዎች እንደሚያሳድሩ ቢጠቁሙም ‹‹የጫትን ጎጂነት የሚያመላክት ማስረጃ እስኪቀርብልን ድረስ  የሚያስገኘውን ዶላር እየበላን እንቆያለን›› የሚለው የመንግስት ምላሽ፣ በመግቢያዬ የጠቀስኩት ሰሎሞንና እሱን መሰሎቹ ቤት ሲበተንና የአዕምሮ ጤና መዛባት ከመቼውም ጊዜ በላይ በዜጎች ላይ ከተከሰተ በኋላ እርምጃ ቢወሰድ “ቀድሞውን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” እንዳይሆንብን ያሰጋል።

Read 9285 times