Sunday, 14 May 2017 00:00

አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት፡ የሁለት ባህሎች ወግ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(4 votes)

 ብሩህ ዓለምነህ(በአ.አ.ዩ. በማስተርስ የፍልስፍና ተማሪ እና“የፍልስፍና ፩ እና ፪” መፅሐፍት ደራሲ)

       “የአክሱም ሐውልትን እዩት በራሱ የተማመነ፣ ወደ ሰማየ ሰማያት በድፍረት አንጋጦ አማልክቱን፣ ከዋክብቱንና ጨረቃን ወደ ላይ አፍጥጦ “እኔ እንዲህ ነኝ፤ ይሄንንና ያንን ማድረግ ችያለሁ፤” ብሎ የሰውን ልጅ ምድራዊ የበላይነትና ኩራት የሚያበስር ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ላሊበላ አፈርና ዲንጋይ ፈልፍሎ፣ ወደ ምድር አጎንብሶ፣ ራሱን ዝቅ በማድረግ እላዩ ላይ የመስቀል ምልክት ጭኖ ፈጣሪን “አንተ የሁሉም የበላይ ነህ” የሚል ሲሆን ይሄም የመለኮትን ኃያልነትና የሰውን ልጅ ዝቅተኛነት የሚያስተጋባ ነው፡፡”
በሐምሌ 2002 ዓ.ም የአክሱምንና የላሊበላን ኪነ ህንፃዊ ተምሳሌታዊነት በዚህ መልኩ የተነተኑት የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡
የፍልስፍና መምህሩ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት” የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ሥነ ፅሁፍ ውስጥ ያስተዋወቁትም በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ይሄንን ፅንሰ ሐሳብ የተዋሱት “ሄለኒዝምና ሂብራይዝም” ከሚለው የማቲው አርኖልድ (Matthew Arnold)  ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አመለካከት፤ የጥንታዊው ግሪክ ሥልጣኔ (ሄለኒዝም) እና አክሱማዊነት የሚመሳሰሉ ሲሆን ዋነኛ መገለጫቸውም፡-
ለምድራዊ ክብረት የሚጥሩ፣
ለአእምሯዊ ትሩፋት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ፣
ቁሳዊው ነገር የበላይነት አለው ብለው የሚያምኑና
ለዓለማዊ ደስታ የሚተጉ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የአይሁዳውያን መንፈሳዊ ሥልጣኔ (ሂብራይዝም) እና ላሊበላዊነት ተመሳሳይ ይዘት ሲኖራቸው ዋነኛ መገለጫቸውም፡-
በዓላማ ደረጃ፡— የመንፈሳዊ ፍፁምነትን ለመጎናፀፍ የሚመኙ፣
በስነ ምግባር ደረጃ፡— ታዛዥነትንና ተቀባይነትን ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጡ፣
በግንዛቤ ደረጃ፡— ከፅንሰ ሐሳብ ይልቅ ተግባራዊ ህይወት ላይ የሚተጉና
ዓለማዊ ህይወትንና ደስታን የሚቃወሙ ናቸው፤
በመሆኑም ዶ/ር ዳኛቸው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት ተሸጋግሯል ሲሉ ከላይ በጠቀስናቸው ሁለንተናዊ የዓለም አመለካከቶች ላይ ስር ነቀል የሆነ ሽግግር መምጣቱን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ አክሱማዊነት የሰውን ልጅ ምድራዊ የበላይነት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ ላሊበላዊነት ደግሞ የሰውን ልጅ ምድራዊ ዝቅተኛነት የሚያመላክት ፅንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የዶ/ር ዳኛቸው ትምህርት ለሦስት ጥያቄዎች መልስ አልሰጠም፡፡
የመጀመሪያው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት የተሸጋገረው መቼ ነው? የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት” የሚለውን ፍልስፍናዊ ድምዳሜ ታሪክ ይደግፈዋል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ሦስተኛው ጥያቄ፣ ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት ያደረግነው ሽግግር በ17ኛው ክ/ዘ ከተነሳው የኢትዮጵያ ፍልስፍና ጋር ዝምድና አለው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ለእነዚህ ሦስት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል፡፡
ዶ/ር ዳኛቸው፣ በአፄ ኢዛና ዘመነ መንግስት ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የመንግስት ሃይማኖት የሆነበትን ጊዜ (4ኛው ክ/ዘ) የሽግግር ጊዜ ያደርጉታል፡፡ ሆኖም ግን ከአፄ ኢዛና እስከ አፄ ካሌብ ድረስ ያለውን 200 ዓመታት ስናጠና፣ አክሱማዊነት ይበልጥ ያደገበትና እንዲያውም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በመሆኑም ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት የተደረገው ሽግግር በክርስትና መምጣት ምክንያት የሆነ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሽግግሩ 4ኛው ክ/ዘ ላይ አልነበረም ማለት ነው፡፡
የታሪክ ምሁራን ለአክሱም ሥልጣኔ መውደቅ ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት የአክሱማውያን የቀይ ባህር የንግድ መስመር በ7ኛው ክ/ዘ በሙስሊሞች መያዙን ነው፡፡ ሆኖም ግን የቀይ ባህር የንግድ መስመር ከሙስሊሞቹ በፊት በ6ኛው ክ/ዘ አጋማሽ ላይ በፐርሺያኖች ተይዞ ነበር፡፡ በሌላ በኩል አፄ ካሌብ በ525 ዓ.ም ወደ የመን ከመዝመቱ በፊት ፐርሺያኖችን ከቀይ ባህር የንግድ መስመር ለማባረር ከቢዛንታይኑ ንጉስ ጀስቲኒያን ጋር በ517 ዓ.ም ስምምነት አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አፄ ካሌብ ለዚህ ስምምነት ተገዥ ከመሆን ይልቅ የመንን ድል ካደረገ በኋላ ሥልጣኑን ለልጁ ለአፄ ገ/መስቀል በማውረስ እንደ አባቱ እንደ ዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ መመንኮስን መርጧል፡፡ የአፄ ገ/መስቀልም ዋነኛ ትኩረት ገዳማትን ወደ ደቡብ ማስፋፋት ሆነ፡፡ በስተመጨረሻም እሱም እንደ አባቱና እንደ አያቱ የብሕትውና ህይወትን መረጠ፡፡
ይሄም የሚያሳየን 6ኛው ክ/ዘ ላይ አክሱም ላይ ስር ነቀል የሆነ አዲስ ዓይነት የባህልና የእሴት ለውጥ መምጣቱን ነው፡፡ የዚህ ለውጥ ምክንያት ደግሞ ለክርስትና አዲስ ዓይነት አተረጓጎም መሰጠቱ ነው። ይሄም አዲስ ትርጉም “ክርስትና ማለት ምንኩስና ነው” የሚለው ነው፡፡
ይሄም አዲስ የክርስትና ትምህርት በ9ኙ ቅዱሳን አማካኝነት 5ኛው ክ/ዘ መጨረሻ ወደ አክሱም የገባ ሲሆን፣ 6ኛው ክ/ዘ ላይ ደግሞ ከአክሱም አልፎ በአካባቢው መንደሮች ላይ ሁሉ ተስፋፍቷል፡፡ 9ኙ ቅዱሳን ከመጡበት ከዳግማዊ አፄ እለ አሚዳ እስከ አፄ እለ ገበዝ ባሉት 130 ዓመታት ውስጥ ከነገሱት አምስት ነገስታት አራቱ መንኩሰዋል፡፡ ይሄም የምንኩስና ትምህርት በህብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህል ጉልበት እንደነበረው የሚያሳይ ነው፡፡
ይሄም አዲስ የክርስትና ትርጉም የነገስታቱን የትኩረት አቅጣጫ ከዓለማዊ ገናናነት ወደ መንፈሳዊ ጭምትነት በመቀየር አክሱማዊነት የተመሰረተበትን “የሰውን ልጅ ምድራዊ የበላይነት መጎናፀፍ” የሚለውን መርህ ከውስጥ እየቦረቦረው ሄደ፡፡
ነገስታቱ ከሥልጣን ገናናነት ይልቅ ግላዊ ነፍሳቸውን ለማዳን ያደረጉት ሩጫ፣ ለህዝቡ ትልቅ መልዕክት ነበረው፡፡ የምንኩስና ህይወት ከእምነት አልፎ ለህብረተሰቡ ዓለምን መመልከቻ መነፅር ለመሆን የበቃው ነገስታቱ ከዓለማዊ ድሎት ይልቅ የምንኩስና ህይወትን ሲመርጡ መታየታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብሕትውና ከእምነት ወደ ባህልነት ሰፋ፤ ምንኩስና የተመረጡ ጥቂቶች የሚኖሩበት እምነት ከመሆን አልፎ ህዝቡ ገዳም መግባት ሳያስፈልገው በየዕለቱ የሚኖረው ህይወት ሆነ፡፡
በዚህም ዓለምን የሚጠየፍ፣ ስጋዊ ህይወትን የሚያንቋሽሽ፣ “እኔ የምድር ቆሻሻ ነኝ!!” የሚል ህብረተሰብ ተፈጠረ፡፡ እንኳን የስራ መሳሪያዎችን ሊያሻሽል ይቅርና በአክሱማዊነት ዘመን እንኳ የነበሩትን ጥበቦችና የእጅ ሙያዎች ማስቀጠል የማይችል ማህበረሰብ ተፈጠረ፡፡ ጭራሽ ከዚህ በተቃራኒ ለዓለማዊ ብልፅግና መጣር እንደ ከንቱ ድካም ተቆጠረ፤ ግንበኝነት፣ አናጢነት፣ ቀጥቃጭነትና ሌሎችም የእጅ ሙያዎች ከመከበሪያነት ወደ መሰደቢያነት ተቀየሩ፡፡
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መፅሐፋቸው (ገፅ 12-13) ላይ እንዲህ ይላሉ፣ “በኢትዮጵያ የብሕትውና (የላሊበላዊነት) ዘመን ዲንጋይ እየፈለፈሉ ገዳማትን ከመስራት ውጭ ልክ እንደ አክሱማውያን የታየ ሌላ የሥራ ጥበብ የለም፡፡”
በመሆኑም አክሱማዊነት የከሸፈው የቀይ ባህሩ የንግድ መስመር በውጭ ወረራ ስለተያዘ ሳይሆን ከውስጥ ታንቆ ነው − በምንኩስና!! በምንኩስና ባህል የተነሳ የህብረተሰቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት የተመሰቃቀለ ሆነ፡፡ እናትና አባቱን እየተወ የሚመነኩሰው ወጣት ጨመረ፤ አባወራ ልጆቹንና ሚስቱን እየተወ፣ እናት ልጆቿንና ባሏን እየበተነች መመንኮስ በጣም የተለመደ ሆነ። አፄ እለ ገበዝ (የአፄ ገ/መስቀል ልጅ) ያደረገውም ይሄንኑ ነው፤ ሥልጣኑን ለማንም ሳያወርስ፣ ሀገሪቷንና ህዝቡን የትም በትኖ ከሚስቱ በስተቀር ለማንም ሳይናገር መነነ፡፡ ወዲያውም የእርስ በርስ ጦርነትም ተነሳ፡፡ ምንኩስና ለግብረሰዶማዊነት መነሻ ምክንያት መሆኑንም እንዳንረሳ፡፡
ምንኩስና ህብረተሰቡ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ምስቅልቅል ህይወት የፈጠረ ቢሆንም እስከ 17ኛው ክ/ዘ ድረስ ግን ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልገጠመውም ነበር፡፡ በ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የተነሳው ይሄንን ምስቅልቅል ህይወት ለማስተካከል ነው፡፡ 6ኛው ክ/ዘ ላይ የተስፋፋው የምንኩስና ህይወት ተግዳሮት የገጠመው 17ኛው ክ/ዘ ላይ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት የዚህ ሃገራዊ ኃላፊነት ተሸካሚዎች ናቸው፡፡
በርካታ የሀገራችን የፍልስፍና መምህራንና ተማሪዎች ለዘርዓያዕቆብ መነሳት ገፊ ምክንያት 17ኛው ክ/ዘ ላይ የነበረው የሃይማኖት ጭቅጭቅ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ይሄ ግን ስህተት ነው፡፡ የሃይማኖት ጭቅጭቁ ዘርዓያዕቆብን ለግራ መጋባትና ወደ ግል ምርመራ መሄድ ምክንያት ቢሆነውም፣ በዚህ የግል ምርመራ ውስጥ ግን ያፈለቀው ነገር ለጭቅጭቁ የሚሆን መፍትሄ ብቻ ሳይሆን ከ6ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ሲንከባለል ለነበረው ችግራችን የመውጫ መንገዱን የጠቆመ ነው፡፡ በዚህም የችግራችን አስኳል ምንኩስና መሆኑን ዘርዓያዕቆብ ደርሶበታል፡፡ የ17ኛው ክ/ዘ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ለህዝቡ ጉስቁልና ምክንያት ለሆነው የዘመናት ችግር መልስ የሰጠ ነው፡፡
የምንኩስና እምነት የተመሰረተው “ዓለማዊ (ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ) ህይወት ለመንፈሳዊ ህይወት እንቅፋት ነው” በሚል አስተሳሰብ ላይ ነው። ስለዚህ፣ መንፈሳዊ ፍፅምናን ለማግኘት የሀገራችን ሰው ቤተሰቡን እየበተነ፣ ጥሪቱንም ለድሆች እየሰጠ ሲመነኩስ ኖሯል (ማቴ 19፡21)፡፡
ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ከዚህ በተቃራኒ “በመንፈሳዊ ህይወታችን ከፍታን ልናመጣ የምንችለው የተደላደለ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ሲኖረን ነው” የሚል አዲስ አስተሳሰብ ይዘው መጡ፡፡ እንዲያውም “ለመፅደቅ ተብሎ ቤተሰብን ጥሎ መሄድ ኃጢአት ነው” ብለው ተነሱ፡፡ ስለዚህ “መንፈሳዊ ህይወት የተደላደለ ቁሳዊ መሰረት የሚፈልግ ከሆነ ጠንክሮ በዕውቀት መስራት፣ ስራችን ላይ ፈጠራዎችን እየጨመሩ ትርፋማነታችንን ማሻሻል፣ ሐብት ያለ ገደብ ማከማቸትና ህይወትን ከሌሎች ሰዎች ጋር በፍስሃና በደስታ መኖር አለብን” እያሉ አስተማሩ፡፡ ይሄ የኔ ቃል አይደለም − የፈላስፎቹ ነው፡፡
የፈላስፎቹ ጥል ከክርስትና ጋር አይደለም፤ ከምንኩስና ጋር እንጂ!! በፈላስፎቹ አመለካከት በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወት መካከል፣ በአክሱማዊነትና በላሊበላዊነት መካከል ሚዛኑን የጠበቀና የታረቀ ህይወት እንዲኖረን “ክርስትና ማለት ምንኩስና ነው” የሚለው የእነ አባ እንጦንስ ትርጉም መሻር አለበት፡፡
(ይህ ፅሁፍ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ከሚያዚያ 28 — 29፣ 2009 ዓ.ም ባዘጋጀው 4ኛው አገር አቀፍ የባህል አውደ ጥናት ላይ የቀረበ ነው)

Read 989 times