Sunday, 14 May 2017 00:00

የሀሳብ ልዩነትን ያለመቀበል = አንባገነንነት

Written by  በድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(2 votes)

  “የሀሳብ ልዩነትን ያለመቀበል፣ በሀሳብ ድህነት ለአንባገነንነት የሚቀመጥ የመሰረት ድንጋይ ነው”
                   
     እርግጥ ነው የአንባገነንነትና የዲሞክራሲ ጽንሰሀሳብ አብዛኛውን ጊዜ የሚተነተነው፣ ከፖለቲካዊ ያስተዳደር ሁኔታ ጋር ተቆራኝቶ ነው፡፡ በዲሞክራሲና በአንባገነንነት ተከታዮች መካከል ውይይት የለም፤ በመሠረታዊ ባህርያቸው የተነሳ የተቀመጡበት ጽንፍ ወደ ውይይት አያንደረድራቸውም፡፡ የአንዱ ፈቃድ በሌላው ክልክል ነው፡፡ የዲሞክራሲውን ጉዳይ እዚሁ ልግታውና (ምንም እንኳን ስለ አንባገነንነት ስንናገር ስለ ዲሞክራሲ አሉታዊ ጥንፍ እያወራን ቢሆንም) የጽሁፌ መሰረት በሆነው አንባገነንነት ላይ ብቻ ላተኩር፡፡ አንባገነንነት ለተቃራኒ ሀሳብ ቦታ የለውም፡፡ በአመንክዮ ሊሟገተው ፈቃዱ አይደለም፡፡ የሚሟገተውን ይጨፈልቃል፤ አቅም ካለው፡፡ አቅም ከሌለው ይረግማል፤ ያሳቅላል፡፡  
ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያው ብቻ ሳይሆን፣ በማህበር የምንተነፍሰውንም አየር ‹‹ቡድናዊ አንባገነንነት››  አውዶታል፡፡ ‹‹ይህን ዘፈን የሚወድ የሀገርና የወገን ወዳጅ፣ የሚጠላው የሁለቱም ጠላት›› እየተባባልን ነው፡፡ ይህ አዲስ አይደለም፣ በተደጋጋሚ ተከስቷል፤ በየአጋጣሚው፡፡ በኪነጥበብ ስራ፣ በፖለቲካ ጉዳይ ‹‹ቡድናዊ አንባገነንነትን›› ተመልክተናል፡፡ ሰሞኑን የወጣውን የቴዎድሮስ ካሳሁን ዘፈን በተመለከተ፣ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን፣ የርእዮት ፕሮግራም አዘጋጅ ላይና፣ በሙዚቃ ባለሙያው በሰርጸ ፍሬ ስብሀት ላይ (ውሎ አድሮ ሀሰት ነው ቢባልም)፣ ዘፈኑን በመንቀፋቸው ምክንያት የተሰነዘረባቸው ትችትና ማሸማቀቅ በማህበረሰባችን ውስጥ ቡድናዊ አምባገነንነት የደረሰበትን የሚያሳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የቴዲ ዘፈን የጽሁፌ ቆስቋሽ እንጂ ዋናው ጉዳይ አለመሆኑን ነው፡፡ ዘፈኑ በባለሙያ ግምገማ የራሱ ቦታ ይኖረዋል፡፡ እስከዚያው አድማጩ እንደየ የሙዚቃ ስልት ምርጫው፣ እንደየ የፖለቲካዊ አመለካከቱ (ግጥሞቹ ወቅታዊውን የፖለቲካ ጉዳይ የተንተራሱም በመሆናቸው) የተለያየ ስሜት ያሳድሩበታል፤ ነገር ግን ሰው የኮካኮላ ጠርሙስ ወይ ሸራ ጫማ አይደለም፤ በፋብሪካ አንድዓይነት አንጎል የተገጠመለት፡፡ በመሆኑም እኛ የወደድነውን ጠላህ ብሎ፣ ያውም ‹‹ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!›› እያሉ እየዘፈኑ፣ ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ውጭ የሆነ ነውር እየጠቀሱ፣ አንድን ሰው በሀሳቡ የተነሳ፣ አካላዊ ጉድለቱን እየጠቀሱ ማሸማቀቅ ከአንባገነናዊነት ውጭ ትርጉም የለውም ነው፡፡ መንግስትን በአንባገነንነቱ እየተቸን፣ ዲሞክራሲያዊ አገዛዝን ለማምጣት የተሰለፍን ሰዎች፣ የአንድን ዜጋ የሀሳብ ልዩነት መቀበል ካቃተን፣ ወደፊት እድሉን ብናገኝ፣ ከእኛ የሚጠበቀው ዲሞክራሲያዊ አስተዳደራችን ሳይሆን፣ አንባገነናዊ ፈላጭ ቆራጭነታችን ነው፡፡
በአንድ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስርአት ውስጥ ለሚታዩ እሴቶች መሰረቱ የዜጋው ሁለንተናዊ የአስተሳሰብና የአኗኗር መንገድ ነው፡፡ በተረቱም በእምነቱም ሙስናን የሚጸየፍ ህዝብ፣ ሙሰኛ መንግስትን አያበቅልም፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል››ን የሚተርትና የአንድ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር የጉምሩክ ጥበቃ ሀላፊ ሆኖ ሲቀጠር፣ ለ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› የሚሰለፍ ማህበረሰብ፣ ሙስናን የሚጸየፍ መንግስት ሊያፈራ ያዳግተዋል፡፡ የተለዩ ግለሰባዊ ሀሳቦችን ከማያዳምጥ፣ እንዲያውም ከሚያጥላላና ከሚያሸማቅቅ ማህበረሰብ፣ አንባገነንነት በቀላሉ ያጎነቁላል፡፡
ለመንግስታዊ አንባገነንነት መሰረቱ፣ የማህበረሰቡ አንባገነናዊ አመለካከትና ተግባር ነው፡፡ አንዳንዴ ይህ ሁኔታ ወደ ባህልነት ሊዳብር ይችላል፡፡ አመንክዮአዊ ባልሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ለአንባገነንነት የአይፈተሼነት መብት ሊደርብለት ይችላል፡፡ በማህረሰባችን ውስጥ የሚታየው ቡድናዊ አንባገነንነትና የተለየነትን የማጥቃት ባህል እየጎለበተ፣ ካለንበት ሉላዊ አስተሳሰብ ጋር እየተጋጨ ነው፡፡
አለም ነጭና ጥቁር አይደለችም፤ ግራጫዋ ይበረክታል፡፡ ነጭና ጥቁር ብቻ ሆና የምትታየን ከሆነ አይናችንን መፈተሽ አለብን፡፡ የአለምን ሁለት ጠባብ የቀለም ጽንፍ ብቻ የሚያሳይ አይናችንን፣ ከጽንፎቹ መካከል ያለውን ሰፊ ግራጫ ውበትና እውነት በሚያሳይ አዲስ አይን መተካት አለብን፤ ቢያንስ ለራሳችን፡፡ በጠባብ ጽንፍ ታጥረን የአለም ሰፊ እውነትና ውበት እንዲያመልጠን መፍቀድ የለብንም፡፡
በሰፈር ተቧድነን ድብድብ ስንገጥም አድገናል፡፡ በእድር ተሰባስበን የሞተ ቀብረን፤ የተቸገረ ረድተን ኖረናል፡፡ በቡድን ስንደባደብ፣ በእድር ስንረዳዳ ከህብረታችን ሀይልና ጉልበት፣ ከውይይታችን ሀሳብና ብልሀት እያገኘን ነው፡፡ አንድ ስብስብ ለዘለቄታ የሚያቆየውን ጉልበት ከህብረቱ፣ የሚያሳድገውን ሀሳብ ከልዩነቱና ከውይይቱ ያገኛል፡፡ ልዩነትን የማይቀበል ቡድን አዲስ ሀሳብ ሊኖረው አይችልም፤ ፍጹም፡፡ በአሮጌው ሀሳብ ሲንገዛገዝ ይቆያል፤ እስኪወድቅ፡፡ ትክክለኛና ለውጤት የሚያበቃ መደምደሚያ ላይ የሚደረሰው የሌላውን ሀሳብ ከማዳመጥና ሀሳቡ ላይ አመንክዮአዊ ሙግት በማካሄድ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡
በዚህም ዘመን ለተለያየ አላማ በማህበረሰብ ውስጥ ትንንሽ ቡድኖች ይፈጠራሉ፤ በዋናነት ጉልበት ለማደርጀት ሳይሆን፣ ሀሳብን ለማበልጸግ ነው፤ የተሻለውን ለመከተል፡፡ ይህ ድንጋይ የሚገፋበት፣ መድፍ በገመድ የሚጎተትበት ዘመን አይደለም፡፡ ድንጋዩንም ሆነ መድፉን ቁልፍ ተጭነን ካሰብነው እናስቀምጣቸዋለን፡፡ በዚህ ዘመን ህብረት የሚያሻው ሌሎች በርካታ ቁልፎችን ለመፍጠር የሚያበቁ ሀሳቦችን ለማበልጸግ ነው፤ በልዩነትና በውይይት፡፡
ሰዎች በፓርቲ የሚደራጁት ጉልበት አደርጅተው መንግስትን በጉልበት ለመጣል አይደለም፤ የተሻለ ፖሊሲ ነድፈው፤ የተለየ ሀሳብ አጽድቀው በማህበረሰቡ ለመመረጥ ነው፤ ዲሞክራሲ ካለ፡፡ የተለየ ሀሳብን የማይፈቅድ ማህበረሰብ ደግሞ፣ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ፓርቲ ማብቀል ፈተና እንደሚሆንበት፣ በየምርጫው ዋዜማ እየተፈረካከሱና እየተናከሱ ወድቀው የቀሩት ተቃዋሚ ፖርቲዎቻችን ማስረጃዎቻችን ናቸው፡፡ የሀሳብ ልዩነትን ባለመፍቀድ፣ አመክንዮዊ ውይይት ባለመቀበል፣ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ከየፓርቲው ጎጆ የሚወጡ ፖርቲዎች ስንታዘብ የኖርነው ለዚህ ነው፡፡
ሰዎች በአንድ ሀሳብ ስር ይሰባሰባሉ፤ ስለ አንድ ጉዳይ ይበጃል ባሉት ሀሳብ ዙሪያ፡፡ መሰባሰቡ ያንን ሀሳብ በምክንያታዊ ውይይት ለማበልጸግና የበለጠ ችግር ፈቺ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡ መሰባሰቡ ለሀሳቡ ዘብ ለመቆምና ሀሳቡን ያልተቀበሉትን፣ የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ለማጥቃት መሆን የለበትም፡፡ ሀሳብን መከላከል የሚቻለው በአመንክዮ በማበልጸግ እንጂ፣ ለሀሳቡ ዘብ በመቆም ወይም የማይቀበሉትን በማጥቃት አይደለም፡፡ ለአንድ የተለየ ሀሳብ የሚቀርብ የሀይል አፀፋ (ሀይል ስድብን፣ አመንክዮአዊ ያልሆነ ትችትንም ይጨምራል) በሀሳብ ድህነት ለአንባገነንነት የሚቀመጥ የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡
ማወቅና አለማወቅ፣ እውነትና ሀሰት በድምጽ ብልጫ አይጸድቁም፡፡ የሀሳባችን ደጋፊ ብዛት ምን ያህል ሰው በሀሳባችን እንደተስማማ እንጂ፣ የሀሳባችንን እውነት መሆን ያለመሆን አያረጋግጥም፡፡ ፓስታ የማይወድ ሰው ሁሉ ፓስታ ምን እንደሆነ አያውቅም ማለት ጭፍንነት ነው፤ ፓስታ ምን እንደሆነ አውቆም መጥላት ይቻላል፡፡ እውቀትና እውነት የየራሳቸው መስፈሪያ አላቸው፡፡ የእውቀትንና የእውነትን ስም በመጥራት ማሸማቀቅ ከቡድናዊ አንባገነንነትን ለመታደግ የሚቀርብ ተጠየቃዊ የመሟገቻ ነጥብ እጦትን መሸፈኛ ከመሆን አይዘልም፤ ያም ከተሰካ፡፡ አንድ ሀሳብ በአንድ መቶ ሰዎች ተቀባይነት ማግኘቱ፣ አንድ መቶ አንደኛው ሰው እንዲቀበለው ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፤ በጭራሽ፡፡

Read 1422 times