Sunday, 14 May 2017 00:00

‹‹ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ›› በአንድ ጊዜ 17 ተሽከርካሪዎች የሚያስተናግድ ማደያ አስመረቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

   በሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያን ባልና ሚስት በአቶ ቴዎድሮስ የሺዋስና በወ/ሮ ገነት ገ/እግዚአብሔር በ53 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው ‹‹ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ››፤ ባለፈው እሁድ የተመረቁት ሁለት ማደያዎች 300 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ይግዛው መኮንን በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፣ ባለፈው እሁድ ከቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ወጣ ብሎ የተመረቀው ጎመጁ ማደያ፣ እጅግ ግዙፍና በአገሪቷ ተወዳዳሪ እንደሌለው ጠቅሰው፣ በአንድ ጊዜ ለ17 ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት ይችላል ብለዋል፡፡
ባለፈው እሁድ የተመረቁት ሁለት ማደያዎች በቱሉ ዲምቱ የተሰራው 23ኛ ዘመናዊ ማደያ 40 ሚሊዮን ብር መፍጀቱን፣ ከቢሾፍቱ ከተማ 5 ኪ.ሜ ያህል ወጣ ብሎ የተሰራው 24ኛው ግዙፍ ማደያ 260 ሚሊዮን ብር የወጣበት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ስም ጠፍቶ ማደያ ተባለ እንጂ በጣም ትልቅ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ 17 ማደያዎች ስላሉት የትራፊክ መጨናነቅ አይኖረውም፡፡ ወደፊት የምናከፋፍላቸውን ቡታ ጋዞች፣ ዘይቶች፣ ቅባቶች፣ … የምናስቀምጥበት 3 ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ ያረፈ ትልቅ መጋዘን፣ ከምድር በታች ነዳጅ መያዣ ታንከሮች መቅበሪያ ቦታ (እስካሁን ድረስ ታንከሮች እየገዛን ነበር፡፡ አሁን ግን የራሳችንን ታንከሮች መሥሪያ ፋብሪካ እዚያው አቋቁመናል፤ ወደፊት ለሚፈልጉ ድርጅቶችም መሸጥ እንችላለን) አለን በማለት አስረድተዋል፡፡
ማደያውን ትልቅ ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራው እንደሆነ ገልጸው፤ በዚያ መንገድ የሚያልፉት መኪኖች ተሳቢ የጭነት መኪኖችና ፈሳሽ መጫኛ ትላልቅ ቦቴዎች ስለሆኑ ሾፌሮች መኪኖቻቸውን ያለ ስጋትና ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ የሚያቆሙበት ሰፊ ስፍራ አለው ብለዋል፡፡ የመኪና ማጠቢያ ቅባት መለወጫ ጋራዥ አለው፡፡ ከነመሰረቱ 8 ፎቅ ያለው ህንፃ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛ ፎቅ ደርሷል፡፡ ሁሉም ማደያዎች ዘመናዊ የመኪና እጥበትና ዘመናዊ የጎማ ጥገና አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም ማደያዎች ዘመናዊ የገበያ አዳራሾችና ደንበኞች ዘና የሚሉባቸው ካፌና ሬስቶራንቶች ይኖራቸዋል፡፡ ይኼንና ሌሎችንም አገልግሎቶች ስለምንሰጥ ነው በጣም ትልቅ ነው ያልነው፡፡ ይህ ማደያ ከቢሾፍቱ ወደ ሞጆ ሲኬድ 5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወይም በፈጣን የክፍያ መንገድ ወደ ደቡብ መውጫ ፊት ለፊት ይገኛል በማለት አስረድተዋል፡፡  ባለፈው እሁድ ከተመረቁት ጋር በመላ አገሪቱ 24 ማደያዎች እንዳላቸው ጠቅሰው፣ በሀዋሳ የሚሠራው ማደያ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ በሞጆና  በባህርዳር ሁለት ማደያዎች በቅርቡ ይመረቃሉ፡፡ ከደረቅ ወደብ ፊት ለፊት ግንባታ ተጀምሯል፤ በዱከም፣ በትግራይ አዲግራት፣ መቀሌ እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
እኛ ትልቅ ነን የምንለው በማደያዎቹ ግንባታ ነው፡፡ በማደያ ግንባታ እንኳን የአገር በቀሎቹ የውጪዎቹም ድንበር ዘለል የነዳጅ ኩባንያዎች የኛን ዓይነት ማደያዎች አልሰሩም፡፡ በገበያ ረገድ፣ በአገሪቷ ካሉ 13 የነዳጅ ማከፋፈያ ኩባንዎች በ10 ወር 6ኛ ደረጃ ላይ ነን፡፡ በአጭር ጊዜ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረስን፣ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመት፣ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ከሚይዙት ውስጥ አንዱ እንደምንሆን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የእኛ ፍላጎት ጥራት ያለው ዘይትና የመኪና ቅባት ለደንበኞቻችን ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከዓለም ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ያሉ ምርጥ ድርጅቶችን አወዳድረን ከአንዱ ጋር ስምምነት ላይ የደረስን ስለሆነ በቅርቡ ለደንበኞቻችን እናሳውቃለን በማለት አቶ ይግዛው መኮንን አብራርተዋል፡፡   

Read 685 times