Print this page
Sunday, 14 May 2017 00:00

የኢትዮጵያና የኤርትራ መጻኢ እጣ ፈንታ

Written by  ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)
Rate this item
(11 votes)

 “ኢትዮጵያና ኤርትራን በፖለቲካና በኢኮኖሚ የማያስተሳስርና የኢትዮጵያን የባህር በር መብት የማያስከብር              ፖሊሲ ፋይዳቢስ ነው”
               ያዕቆብ ኃይለ ማርያም (ዶ/ር)

      ለዚህ ጽሁፍ መንስኤ የሆኑት በቅርብ ጊዜ የተከሰቱ በኢትዮጵያ ሉዐላዊነት ላይ ጫና ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁለት ኩነቶ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢህአዴግ መንግሥት ኤርትራን አስመልክቶ ከቀድሞው የተለየ አዲስ ፖሊሲ ቀርጾ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ መግለጹ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የኤርትራና የኢትዮጵያ የአልጀርሱ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ የሰጠበትን አሥራ አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በድርድሩ ወቅት በታዛቢነት የተሳተፉት የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ፣ ኤፍ ሞገሪን፣ ሰሞኑን ሁለቱ አገራት ውሳኔውን አክብረው፣ የመጨረሻ የሆነውን የወሰን ችካል ወይንም ምሰሶ እንዲተክሉ ያሳሰቡበት ጥሪ ነው፡፡
ኢህአዴግ ኤርትራን አስመልክቶ የቀረጸው ወይንም ወደፊት የሚቀርጸው ፖሊሲ፤ ወንድማማችና እህትማማች የሆኑት የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የ1998-2000 ዓ.ም የጦርነት እልቂት የማያዳግምና የመጨረሻው የማያደርግ፤ ኤርትራና ኢትዮጵያን በፖለቲካና በኢኮኖሚ የማያስተሳስርና የማያቆራኝ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያን የባህር በር መብት የማያስከብር ከሆነ፣የተጻፈበትን ወረቀት ያህል ዋጋ አይኖረውም፡፡
በ1998-2000 ዓ.ም በሁለት አምባገነን መሪዎች እልህ ምክንያት በተከሰተው አሳዛኝ ጦርነት፣ ከሁለቱም በኩል እጅግ ብዙ ወንድሞቻችን አልቀው፣ ብዙ ንብረት ከወደመ በኋላ የሁለቱ አገራት መሪዎች፣ ካልጠፉ የአፍሪቃ አገራት የኢትዮጵያና የኤርትራ ትስስር ወደ ማይዋጥላት፣ ቀድሞ የነበረውን ትስስርም ለማፍረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ወደ አደረገችው ወደ አረቢቷ አልጀርስ አቀኑ፡፡ ከዚያም የግልግል ዳኞች ሰይመው፣ የሚዳኙበት ሕግ መርጠው፣ የድንበርና የካሣ ኮሚሽን አቋቋሙ፡፡
ይህ ኮሚሽን ከመነሻው በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምን አስፍኖ፣ ሁለቱን ሕዝቦች ሊያቀራርብና ሊያስተሳስር የማይችል ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ተወካዮች ድክመት ወይንም በኢሕአዴግ መሪዎች ትዕዛዝ የድርድሩ አልፋና ኦሜጋ መሆን ይገባው የነበረውን የኢትዮጵያ የአሰብ ባለቤትነት ጉዳይ ከእነ አካቴው ሳያነሳ፣ ሕገ ወጥ በሆኑ ውሎች ተመርኩዞ ውሳኔ ሰጠ፡፡ በኢሕአዴግ አሳሳቢነት ኮሚሽኑ ለውሳኔው መሰረት ያደረጋቸው በአፄ ምኒልክ ላይ በጣልያኖች በግድ በተጫኑ፤ ጣልያን ኢትዮጵያን ወርራ የጣልያን ምስራቅ አፍሪቃ ኤምፓየር ስታቋቁም ያፈረሰቻቸው፤ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም ውድቅ ያደረጋቸው፤ ኢትዮጵያም በ1952 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ ቁ. 6/1952 የሰረዘቻቸው ውሎች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የተሻሩ ወይንም የተሰረዙ ውሎች ፓርላማው ተወያይቶባቸው እንደገና ነፍስ ተዘርቶባቸው ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረገ ነገር የለም፡፡ በእነዚህ በተሻሩ ውሎች ላይ ተመርኩዞ የተሰጠ ውሳኔ፣ “የመርዛም ዛፍ ፍሬ መርዛም ነው” በሚለው የሕግ ብሂል መሠረት፤ ውሳኔው ሕገ ወጥ ስለሆነ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ላይ አሳሪነት ሊኖራቸው አይገባም ነበር፡፡
የድንበር ኮሚሽኑ በአልጄርስ ስምምነት የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት፤ ድንበሩን በጽሑፍና በካርታ ወይም በማፕ ማካለልና (Delimit ማድረግ) በተካለለው ድንበር ምሰሶ ወይንም ችካል ተክሎ (Demarcate) የሁለቱን አገራት ድንበር ወይንም ወሰን መለየት ነበር፡፡ ሆኖም ኮሚሽኑ አቶ ኢሣያስ በጋረጡበት የተለያዩ መሰናክሎች ምክንያት በስምምነቱ በተደነገገው መሠረት፣ ችካል ሳይተከል ወይንም ምሰሶ ሳያቆም፣ዘመናዊ የወሰን አከላለል ስልት ተጠቅሜ ከአውሮፕላን በተነሱ ፎቶግራፎች ላይ ተመርኩዤ የማስመሰል ማካለል (Virtual Demarcation) አድርጌያለሁ ብሎ ጠቅልሎ ከአካባቢው እብስ አለ፡፡ ይህ የማስመሰል ማካለል ልብ ወለድ (Fiction) ከመሆን አልፎ በውሉ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ማካለል የሚባል ነገር ካለም፣ በስምምነቱ አልተጠቀሰም ነበር፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ተካልሎ ችካል ተተክሎ የተጠናቀቀና ፍጻሜ ያገኘ ጉዳይ አይደለም።
በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት፤ችካል ተተክሎ የሁለቱ አገሮች ድንበር እንዳልተለየና እንዳልተጠናቀቀ በመገንዘብ ነበር፤ የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ተወካይ ማሳሰቢያ የሰጡት። ማሳሰቢያውም ተዋዋዮቹ ማለትም ኤርትራና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያክብሩ ሳይሆን በወሰኖቹ ላይ ችካል ወይንም ምሰሶ ይትከሉ የሚል ነው፡፡ በራሳቸው ቋንቋ፤ “In this regard, European union encourages all concrete steps that could lead to finally demarcating the border” ነበር ያሉት፡፡ … ይህ የአውሮፓ ኅብረት አቋም ኤርትራ በተለያዩ መድረኮች ከምታሰማው ስሞታ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ኤርትራ በወረቀት ላይ የተሰመረውን እንደ መጨረሻ ማካለል በመቁጠር፣ ኢትዮጵያ ይህንኑ አክብራ ባድመና ሌሎች በውሳኔው ለኤርትራ የተሰጡ አካባቢዎችን እንድታስረክባት በተለያዩ መድረኮች አቤቱታዎች እያሰማች ትገኛለች፡፡ ሆኖም የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይንም በድርድሩ ወቅት ታዛቢ የነበሩት አገሮች፣ የኤርትራን ስሞታ ያልደገፉት ወይንም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ያላደረጉት የድንበሩ የመጨረሻ የማካለል ስራ በተገቢው መንገድ አለመሰራት ማለትም ችካል ወይንም ምሰሶ አለመተከሉን በመረዳታቸው ነው። በወረቀት ወይንም በማፕ ላይ ማካለልና ችካል ወይም ምሰሶ ወይንም ድንጋይ ተክሎ ቦታውን ረግጦ ማካለል የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በወረቀት ላይ የሚሰመረው መስመር ት/ቤቶችን፣ የመቃብር ቦታዎችን፣ የግል ቤቶችን ሳይቀር ለሁለት ሊከፍል ይችላል፡፡ ይህንን የመሳሰሉት ጉራማይሌ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሁለቱ አገራት ተስማምተው፣ ትምህርት ቤቱን ወይንም ቤተ ክርስቲያኑን ወይም መስጊዱን ወደ አንዱ አገር እንዲታጠፉ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጉራማይሌ ሁኔታዎች ሊታወቁ የሚችሉት ቦታውን እረግጦ ችካል በሚተከልበት ጊዜ ነው፡፡
ስለሆነም ይህ በሁለቱ እህትማማች ሀገሮች መሀከል ሰላምን የማያሰፍን፣ ወደ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የማያሻግርና የኢትዮጵያን የባህር በር መብት የማያረጋግጥ፣ ከመነሻው ህገ ወጥ የሆነው ስምምነት ተሽሮ በምትኩ የሁለቱን አገራት ሰላም የሚያረጋግጥ፣ በሂደት በዘለቄታ እይታም ቢሆን ፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን እስከመፍጠር ሊደርስ የሚችል ትስስር የሚፈጥር ስምምነት ማድረግ ለሁለቱም አገራት ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ ይህ የማይጨበጥ ህልም ነው የሚሉ ይኖሩ ይሆናል። ግን ማንኛውም ትልቅ ሃሳብና ክንውን ከትልቅ ህልም እንደሚጀምር ባይረሱ መልካም ነው፡፡
ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን አርቆ ተላሚነትና ሰፊ ራዕይ ከአቶ ኢሣያስም ሆነ ከኢህአዴግ መሪዎች መጠበቅ እውነትም የህልም እንጀራ ፌሽታ ይሆናል። የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር መብት በተለያዩ ጊዜያት ያሉትን በመመልከት፣ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል አስመልክቶ ራዕያቸው ምን እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡
በአንድ ወቅት አቶ በረከት ስምኦን ስለ ኢትዮጵያ የባህር በር መብት ተጠይቀው፤ “እኛ የአሰብን ወደብ አንፈልገውም፤ መንግሥታችን አቋሙን በግልጽ ነው ያስቀመጠው” ብለው ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ “ተቃዋሚዎች የሚያነሱት የአሰብ ይገባኛል ጥያቄ፣ ኢሕአዴግ አያምንበትም” ብለዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ፤ “አሰብን ካልያዝን የሚሉ ዘውዳዊ ትምክህተኞች ናቸው” ሲሉ ተቃዋሚዎችን ዘልፈው ነበር፡፡ እንግዲህ የእነዚህ የኢሕአዴግ ቱባ ባለስልጣናት አቋም ይህ ሆኖ ሳለ፣ እነዚሁ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የባህር በር አስከብረው፣ በአካባቢው ሰላም ያሰፍናሉ ማለት ዘበት ይሆናል፡፡
በእግር መንገድ ርቀት የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን ለኢትዮጵያውያን የሚዋጥላቸውና የሚቀበሉት ጉዳይ ባለመሆኑ፤ እነዚህ ሁለት አገሮች በጠላትነት እስከተሰለፉ ድረስ የአሰብ በኤርትራ እጅ መሆን ለጦርነት መንስኤ ወይንም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የሁለቱ አገራት በፖለቲካና በኢኮኖሚ መተሳሰር ግን የአሰብን ጉዳይ ከአጀንዳነት ያወጣዋል፡፡ ለሰላም መደፍረስና ለእልቂት ምክንያትም አይሆንም፡፡
የእነዚህ የሁለቱ አገሮች መለያየትና በጠላትነት ተፈራርጆ መናቆር ችግሩ ከራሳቸው አልፎ በአካባቢውም፣ ቀደም ሲል ያልነበረ ሁኔታ ፈጥሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤርትራ ህልውና እየተሸረሸረ፣ የኢትዮጵያ ሰላምና ህልውናም አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል፡፡ በአንድ ወቅት የተነሳውን የአቶ መለስ ዜናዊ “አሰብ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት የግመል መፈንጫ ይሆናል” የሚል አቋም ተከትሎ፣ የአካባቢውን ስትራቴጂክነትና ጂኦ ፖለቲካዊ ፋይዳ የተረዱ ኢትዮጵያውያን፤ የአቶ መለስን ሀሳብ ተቃውመው፣ አሰብ ለኢትዮጵያ በጎ በማይመኙ ኃይሎች እጅ ትወድቃለች በማለት አስጠንቅቀው ነበር፡፡ (አሰብ የማን ናት፤2003 ዓ.ም ገጽ፤189)
እነሆ ይህ በተባለ አስር አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አሰብ በሳውዲ አረቢያና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እጅ ገብቶ የጦር ሰፈር ተቋቁሞበታል። ግብጽም እንዲሁ በኤርትራ ደሴቶች የጦር ሰፈር አቋቁማለች፡፡ ከበባው በመቀጠል አሁንም ግብጽ ከደቡብ ሱዳን ጋር ውል ተፈራርማለች፡፡ ሶማሌላንድ ውስጥም የጦር ሰፈር ለማቋቋም እየተደራደረች መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ከፕሬዚዳንት ጋማል ናስር ወዲህ ግብጽ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን የሚያሳርፍና የሚያስመነጥቅ የጦር መርከብ ገዝታ ቀይ ባህርን በማሰስ ላይ ትገኛለች፡፡
ለመሆኑ ሳውዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አሰብ ላይ የጦር ሰፈር ያስፈለጋቸው የየመንን አማጺያን ለመውጋት ብቻ ይሆን? ግብጽስ ኤርትራ ውስጥ የጦር ሰፈር ለምን አስፈለጋት? ቀጠናዋን ዘልላ ሄዳ ከደቡብ ሱዳን ጋር ምን ሊፈይድላት ነው ውል የተፈራረመችው? ሶማሊላንድ ውስጥ የጦር ሰፈር ያስፈለጋትስ እስራኤልን ለመገዳደር ነውን? በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ይሄ ሁሉ አደጋ የሚያንዣብበው ኢትዮጵያ በዘር ተሸንሽና፣ ሁሉም በየዘሩ ብሔር ከረጢት ውስጥ ገብቶ፣ ብሄሮቹም ውሃ ቀጠነ ብላችሁ ከእናት ኢትዮጵያ ልትገነጠሉ ትችላላችሁ ተብለው፣ ይህም መብት በህገ መንግሥቱ በተረጋገጠላቸው ወቅት ላይ ነው፡፡ አባይን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን የወረረው የግብጹ አዲቭ ኢስማኤል ፓሻ፣ በጉራና በጉንደት በጀግናው አሉላ አባ ነጋ ጦር ድል የተመታው እኮ፣ አሉላ ከብረት በጠነከረ አንድነት የተሳሰረ ጦር አሰልፈው እንጂ በጎሳና በብሔር በየአቅጣጫው በተከፋፈለ ጦር አልነበረም፡፡
የአልጀርስ ስምምነት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም የጎዳው፤ ከኢትዮጵያም ባልተናነሰ ምናልባትም በከፋ ሁኔታ ኤርትራንም ጎድቷል፡፡ ይኸውም የኤርትራን ሉዐላዊነት ለትልቅ አደጋ ማጋለጡ ነው፡፡ በአልጀርስ ስምምነትና በኮሚሽኑ ውሳኔ መሰረት፣ የኢትዮጵያ ከቀይ ባህር አካባቢ መገለል ኤርትራን ለመዋጥ ለሚሹ ኃይሎች በሩን ከፍቶላቸዋል፡፡ በበረሃ ንዳድ ከመቃጠል ብዛት የአሥመራ ነፋሻማ አየርን ለሚቋምጡ ሳውዲዎችና ኢምሬቶች በሩን ሳያንኳኩ ሰተት ብለው ኤርትራ ለመግባት አስችሏቸዋል፡፡ አሁን የሚከተለው ደግሞ ተቻችሎና ሚዛኑን ጠብቆ የኖረው ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ህብረተሰብ፤ በአክራሪ ወሀቢዎች ጣልቃ ገብነት፣ ዘመናት የተሻገረው ሚዛን ወደ መዛባቱ ሊሄድ የሚችልበት አጋጣሚ መፈጠሩ ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩትን አደጋዎች የአሁኖቹ የኤርትራ መሪዎችም ሆኑ የኢትዮጵያዎቹ የመቋቋም ወኔ የላቸውም፡፡ በዕውቀት ማነስና በራዕይ መኮሰስ ምክንያት ፍጹም መለያየት ያልነበረባቸውን ሁለት ሕዝቦች ያለያዩ መሪዎች፤በዚህ ዓለም የተቆረጠላቸው አልያም የሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ እየተገባደደ ስለሆነ ማለቂያው እሩቅ አይሆንም። ስለሆነም የኢትዮጵያና የኤርትራ ወጣቶች ቂምና ቁርሾውን እረስተው፣ በእኩልነት መቀራረብና መወያየት ይገባቸዋል፣ ነገ የእነርሱ ናትና፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ መጻኢ ዕድል የተሳሰረ መሆኑን እንደ ዛሬዎቹ መርሳት ወይንም መካድ አይገባቸውም፡፡ የቀድሞዎቹ ኤርትራውያን “ኢትዮጵያ ወይንም ሞት” ብለው የተነሱት ኤርትራ ብቻዋን ብትቆም ሊከተል የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ እንጂ አገር ለመክዳት አልነበረም፡፡ እንደ ማንም አገራቸውን የሚወዱ፣ ሕዝባቸውን የሚያስቀድሙ የተከበሩ ዜጎች ነበሩ፡፡ እናም ይህ የአንድነት ትስስር ተማጽኖና ጥሪ የተሰነዘረው ለሁለቱም አገራት ወጣቶች ነው፡፡ ምናልባት ይህን ትስስር ለማስረጽ ጊዜ ይወስድ ይሆናል፡፡ የአገር ጉዳይ በአሥርና በሃያ ዓመት አይሰላም፡፡ አገር ዘላለማዊ እንደመሆኑ መጠን፣ መጻኢ ዕድሉም በዓመታት ቁጥር አይገደብም፡፡  
በመጨረሻም የኤርትራና የኢትዮጵያ ወጣቶች ቁርጠኝነቱ ካላቸው፣ ቂምና ቁርሾ እይታቸውን ሳያንሸዋርረውና ሳይገድበው ሰፊ ራዕይ ሰንቀው፣ እነዚህ በደም፣ በቋንቋ፣ በታሪክ ወዘተ የተሳሰሩ አንድ መቶ ስድስት ሚሊዮን ሕዝቦች በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተሳስረው እጅግ ስትራቴጂክ የሆኑ ሦስት የባህር በሮች ይዘው፣ ሰፊ የእርሻ መሬትና ሰፊ ገበያ ኖሯቸው፣ በማዕድናት በልጽገው፣ በጠላት የማይደፈርና በልማት የዳበረ አንድ ህብረተሰብ መፍጠር እንደሚችሉ ፍንትው ብሎ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ወጣቶች ከዚህ የበለጠ ታሪካዊ ተልዕኮ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህንን ትልቅ ተልኮ ለማሳካት ከአሁኑ ግንኙነት ፈጥረው፣ ውይይትና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ለኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድ ነገር አስረግጬ መልዕክቴን እዘጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ፤ወንድምና እህት ለሆነው ለኤርትራ ህዝብ የማይነጥፍ ፍቅርና የአንድነት ስሜት ነው ያለው፡፡ ለዚህም ምስክሩ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ አለ አግባብ በተባረሩ ጊዜ፣ሲችል እየደበቀ፣ ካልቻለም በእንባ እየተራጨ ወደ አገራቸው መሸኘቱ ነው፡፡
(P.S ይህ መጣጥፍ መታሰቢያነቱ ተለያይተው የነበሩትን ኤርትራና ኢትዮጵያን እንደገና ለማቀራረብና ለማስተሳሰር፣ ፌደሬሽኑም እንዳይፈርስ ትልቅ ትግል ላደረጉት ለክቡር ጸሃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ ይሁን፡፡)    

Read 3903 times