Sunday, 14 May 2017 00:00

የሙዚቀኞች ማህበር፤ የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አስተዳደር ሊመሰርት ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  “ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር፤ ህብረቱ እንዳይቋቋም ጥረት እያደረገ ነው”
                  “ላለፉት 40 ዓመታት የሙያተኛውን ንብረት እየሸጠ ሲጠቀም ቆይቷል”
              
     የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር፤ የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አስተዳደር ለመመስረት በሂደት ላይ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን ትክክለኛ የዘርፉ ባለሙያዎች አባል የሚሆኑበትን አሰራር እንደሚከተልና አዲስ መታወቂያ በቅርቡ አዘጋጅቶ በመስጠት የቀድሞውን ውድቅ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ ፒያሳ ኤሊያና ሆቴል ማህበሩ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፤አስተዳደሩን ለመመስረት እንድንችል በአዋጁ የተደነገገልን መብት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌታሁን በኩል ይሁንታ አግኝቶ ቢፈቀድም ሂደቱን የሚያስፈፅመው አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት፣ “ኦዲዮቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር” ለተሰኘው ቡድን በመወገን፣ በስራችን ላይ እንቅፋት እየፈጠረብን ነው ሲል አስተዳደሩን ለመመስረት የተቋቋመው ኮሚቴ ተናግሯል፡፡
ሙዚቃ በርካታ ዘርፎች ስላሉት ህብረቱን እናቋቁማለን ያለው ማህበሩ፤ህብረቱ ከተመሰረተ በኋላ የአባላትን መታወቂያ በአዲስ መልክ አዘጋጅቶ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው እስከ ዛሬ አማራጭ በማጣት ለነጋዴዎች መጠቀሚያ ሲሆን ቆይቷል ያለው ኮሚቴው፤ከ50 ዓመት ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ማህበራቸው ለዚህ ድል በመብቃቱ  የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡ አዲስ የተቋቋመው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጨምሮ እንደገለፀው፤ “እስከ ዛሬ የሙዚቃ ባለሙያው ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማህበር የተባለውን የንግድ ድርጅት ያልተቃወመው፣ሙዚቃ አውጥቶ ለአድማጭ ለማድረስ ያለው ብቸኛ አማራጭ ይሄው የንግድ ድርጅት ብቻ ስለነበረ ነው፤ላለፉት 40 ዓመታት ያለ አዲስ ውል የባለሙያውን ስራ እየሸጠ ሲጠቀም የከረመው አንሶ፣ አሁን የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አስተዳደሩን ለማቋቋም ባለሙያው የሚያደርገውን ትግል ለማደናቀፍ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ያስታግስልን” ብሏል፡፡
“የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚገኘው የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ ጋር ሚያዚያ 28 ቀን 2009 ዓ.ም ስብሰባ አደርጎ፣የሙዚቀኞች ማህበር የቅጅና ተዛማጅ የጋራ መብት አስተዳደር በአዋጁ መሰረት ራሱን ችሎ እንዲያቋቁም በመወሰኑ ቀኑን ሚያዚያ 27 እንደሚከበረው የአርበኞች ቀን እንቆጥረዋለን” ሲሉም የኮሚቴው አባላት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አስተዳደሩን ለማቋቋም እንዲሰራ በተቋቋመው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ፍቅርአዲስ ነቅአጥበብ፣ ዳዊት ይፍሩ፣ አማኑኤል ይልማ፣ ሞገስ ተካ፣ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) ሄኖክ መሃሪ፣ ብሩክታዊ ጌታሁን ( ቤቲ ጂ)፣ ኤልያስ መልካና ሌሎችም የሙዚቃ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ የሙዚቀኞች ማህበር ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከቤኒሻንጉልና ከሌሎችም ክፍሎች ባለሙያዎችን እያሰባሰበ እንደሆነና ህብረቱን ለመመስረት በሂደት ላይ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

Read 338 times