Sunday, 14 May 2017 00:00

ከዛፍ የተቀዳሁ

Written by  ሙሉጌታ አለባቸው
Rate this item
(15 votes)

 እንደ ሀሸንጌ ጫካ ጥቅጥቅ፤ እንደ ራያ ቆላማ መስክ ዝርግት ያለ ነው፡፡ እንደ ብረት ምጣድ የሚፋጅ ደረቱ። አሁን የተኛሁበቱ፡፡ ጣቶቼን በደረት ጸጉሩ ውስጥ ማርመስመስ በሰደድ እሳት በሚቃጠል ደን ውስጥ መግባት ያክል ነው፡፡ አየር በሳበና ባስወጣ ቁጥር እንደ ባንዲራ ቀስ እያለ በሚወጣውና በሚወርደው የአራዶም ደረት ላይ ተዘልሻለሁ፡፡
በፍቅር ላይ እምነት፤ በእምነት ላይ ጋቢ ደራርበን ተጋድመናል፡፡ የቡሉኮው ሰፊ ጥለት ግራ ብብቴ ሥር ረቂቅ ሸካራነቱ ይሰማኛል፡፡ በቀኝ ጎኔ ተኝቼ የመኝታ ቤቴን ዙሪያ ገባ በሙሉ ግራ ዐይኔና በከፊል የቀኝ ዐይኔ ዐያለሁ፡፡ በግራ ጥግ ያለውን ቁም ሣጥን ለማየት ስሞክር የቀኝ ዐይኔን ብሌን እስከ ጥግ ድረስ መግፋት ስላለብኝ አቅፎ ከያዘው የዐጥንት ክርታስ ጋር ሳጣብቀው እንደ መቆርቆር እያለኝ፡፡ ቁም ሳጥኑ አጠገብ  ሰማያዊ የተቀባው ግድግዳ ተልጦ በፊት የነበረው አረንጓዴ ቀለም ይታያል፡፡ የውስጠኛውን ቀለም እጠላዋለሁ፡፡
ከፍ ዝቅ የሚለው ደረቱ ድንገት እንደሞተ ሁሉ ለአፍታ ቀጥ አለና ስሜን ጠራ፡፡ በአስገምጋሚ ድምፁ፡፡
“ጦቢያ”  
“አቤት አቶ አራዶም ሃይላይ” በሙሉ ስሙ ለቀልድ ስጠራው፡፡ ወይም ሳያቆላምጥ ስለጠራኝ ብድር ስመልስ።
ግቢያችን ውስጥ ከዋናው ቤት ጀርባ እንደ ኮረዳ ጥርስ በተሰደሩ ሰርቪስ ክፍሎች ፊትለፊት አጥሩ ጥግ የፈላውን ወፍ ዘራሽ ጦቢያ-ቅጠል ተውሶ አባቴ ነበር ስሜን ያወጣልኝ፡፡ እነኚህ ዕፅዋት ሲመቻቸው በዝተው ግቢውን ይሞሉታል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጭራሹኑ የመጥፋት ቋፍ ደርሰው ይመለሳሉ፡፡ እያደግኩ  ስለስሜ ማሰብ ስጀምር “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል አወላግደው ሲጠሩት ይመስለኝ ነበር፡፡
ተክሉ በጎኑ እንደ ቆለጥ ነገር አንጠልጥሎ የሚያበቅላቸው ፊኛ ነገሮች አሉት፡፡ እነሱን እየገነጠልን ቮሊቦልና ጢባጢቤ ተጫውተናል፡፡ በጥንቃቄ ካልሆነ ከአንድና ከሁለት ምት በላይ አልሄድ እያሉ ያበሽቁኝ ነበር፡፡
አባዬን ስለምን የዕፅ ስም እንደሰጠኝ ስጠይቀው“የዋዛ መስሎሻል፤ ነጭ ደሟ መድኀኒት ነውኮ የኔ ቆንጆ” ነበር ያለኝ፡፡ ዘወትር ሊናገር ወይ ሊሥቅ አፉን ሲከፍት የምትታይ በወርቅ የተተካች  ጥርስ አለችው፡፡ እሷን በጣቴ ጫፍ እየነካካሁ እጠይቀዋለሁ፡
“ለምንድን ነው ነጭ ያልሆነው?”
“ወርቅ ነው ጦቢያዬ”
“ለኔ ግን ወርቅ ጥርስ አያበቅልልኝም?”
“አንቺ ራስሽ ወርቅ ነሻ!” ጣቴን በከንፈሮቹ ነክሶ ይይዘኝና ሀም-ሀም-ሀም ያደርገኛል፡፡
በወርቅ ጥርሱ የተሸለመማር አንደበቱ ሰምና ወርቅ ሆኖብኝ መሰለኝ ስለ መድኀኒትነት የተናገረው ነገር ባይገባኝም/ ባይዋጥልኝም ጓደኛዬ ጀሚላ ፊቷን የወረራትን ኪንታሮት አረገፈላት ሲሉኝ ስሜን ወደድኩት ነገር፡፡ ለረጅም ጊዜ፡፡ ማን የፈውስ ትእምርት መሆንን ይጠላል? ደሞ ሁሌም የሚያማምሩ ዥንጉርጉር ቢራቢሮዎች ዙሪያዋን እንደ ድባብ ይከቧታል፡፡
ያኔ አባቴ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ ቤት ውስጥ የነበርንው እኔ፣ እሱና ታላቅ ወንድሜ፡፡ እናቴ እኔን በወለደች በሳምንቱ ነበር ያረፈችው፡፡ አባቴ “ልጆቼንማ በእናትያ አላሳድግም” ብሎ ከዚያ በኋላ አላገባም፡፡ በልጅነቴ “እናቴ ማነች?” ብዬ ስጠይቅ ጠረጴዛ ላይ ስልኩ አጠገብ ፍሬም ውስጥ የተቀመጠ ፎቶ እያሳዩ ሌላ አገር እንደሄደች ይነግሩኛል፡፡ ሞት ምን እንደሆነ እየተረዳሁት ስመጣ ማንም ሳያስረዳኝ ገባኝ፡፡    
“አብዮትስ?”
አባቴ ከሥራ (ብዙውን ጊዜ “ስብሰባ አለብኝ” ይል ስለነበር ከስብሰባ ብል ይሻላል) ሲመጣ ይጠይቃል፡፡ ቤት ውስጥ ያለው ወንድሜ ከሆነ “ጦቢያዬስ?”፡፡
ይወደኝ ነበር፡፡ ባሰብኩት ቁጥር ይናፍቀኛል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። አየር እስኪያጥረኝ አቅፎ “ጦቢያዬ እወድሻለሁ” ያለኝን እስካሁን አልረሳም፡፡
ከመሄዱ ከአንድ ቀን በፊት ማታ ላይ ልብሶች በሻንጣ ውስጥ ሲከት የት ሊሄድ እንደሆነ እጠይቀዋለሁ፡፡ የትም እንደማይሄድ ነገረኝና እጁን ዘረጋልኝ፡፡ አቀፈኝ፡፡ ሲያቅፈኝ ልገልፀው የሚያቅተኝ ዐይነት ደህንነት ይሰማኛል፡፡ ራት ከበላን በኋላ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ፡፡ እንቅልፍ ሲወስደኝ አላስታውስም፡፡ እሱ መኝታ ክፍል አልጋው ላይ ነኝ። አባዬም አልጋው ላይ ተቀምጧል፡፡ ዐይኔን በቀኝ እጄ አይበሉባ አሻለሁ፡፡ በግራ እጄ ጆሮ ግንዴ አካባቢ እያከኩ አዛጋሁ፡፡
“የኔ ቆንጆ ጥሩ ልጅ ሁኚ እሺ፡፡ ሁል ጊዜ እደውልልሻለሁ፡፡ ደሞ ወንድምሽ አለልሽ፡፡ እዪኝ እስቲ… ገለጥ.. ገለጥ… ጎበዝ! እዪኝ… ዐየሽኝ… እንዳትረሺኝ እሺ፣ እንዳትረሺኝ ጦቢያዬ፡፡ እንዳትረሺኝ… እንዳትረሺኝ…”
አንስቶ አቀፈኝ፡፡ ሙሉ ለሙሉ አልነቃሁም፡፡ በከፊል ሕልም ይመስለኛል፡፡
“የት ልትሄድብኝ ነው አባ?” በእንቅልፍ በተዘጋ ድምፄ፡፡ በሆነ በማላውቀው ምክንያት  አለቅሳለሁ፡፡ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ሁሉ የሚመለስ አይመስለኝም፡፡
“የትም አልሄድም … የትም አልሄድብሽም፡፡ እመጣለሁ እሺ፣ እመጣለሁ፡፡ አሁን ተኚ፡፡ ጦቢያዬ ውድድ አደርግሻለሁ”
መኝታ ቤቱን ዘግቶ ሲወጣ ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት ቡኒ ጫማና ጥቁር ሱሪውን ነበር፡፡ በኮሪደር አድርጎ ሲወጣ እየራቀ የሄደው የኮቴው ድምፅ አሁን ድረስ ጆሮዬ ውስጥ አለ፡፡ የወርቅ ጥርሱን መፈግፈግ በለመደች ጣቴ ጥርሴን እየዳበስኩ ወርቃማ ቀለሙን ላስቀር እለፋለሁ፡፡
እስካድግ ድረስ “ሌላ አገር” ከመሆኑ ውጪ የት እንዳለ አላውቅም፡፡ በየጊዜው ይደውላል፡፡ ስልኩ የተቀመጠበት ጠረጴዛ አጠገብ ሆኜ  ግራና ቀኝ የቆሙትን የስልኩን ባትሪዎች እያነሳሁ እያስቀመጥኩ አዋራዋለሁ፡፡ የት እንዳለ ስጠይቀው ሥራ እንደሆነ ይነግረኛል፡፡ አቢን ስጠይቀው እያባበለ አታልሎ ጥያቄዬን ያስረሳኛል፡፡  ከሦስት ከአራት ዓመት በኋላ አባዬ የሚኖረው  ሐረርየሚባል ሩቅ አገር እንደሆነ ለማንም እንዳልናገር አስጠንቅቆ ነገረኝ፡፡ ለምን እንደተሰደደ ግን ዐሥራ ስድተኛ ዓመቴ ድረስ ማንም አልነገረኝም፡፡
እዚያ አገር ምን ዐይነት ሰዎች እንዳሉ አላውቅም። የአቢ መኝታ ቤት ግድግዳ ላይ ከተንጠለጠለው የኢትዮጵያ ካርታ ላይ ለማግኘት የምሞክረው የምኖርባትን ከተማ ገነቴን ሳይሆን ሐረርን ነው፡፡ ግን አንድም ቀን ተሳክቶልኝ አያውቅም፡፡ አባዬ እዚያ ቦታ በሆኑ በማላውቃቸው ሰዎች በተሞላ መንገድ ብቻውን ሲንከራተት አስባለሁ። ጥቁር ሱሪና ቡኒ ቆዳ ጫማ አድርጎ፡፡ በወርቅ ጥርሱ የደመቀች ጠይም ሣቅ እየሣቀ። ምስኪን ከርታታ አባቴ… በወርቅ ንክር አስገምጋሚ ድምፁ “ጦቢያዬ” የሚለኝ፡፡
“ጦቢያዬ ለምን አንጋባም?”
የአራዶም ድምጽ ጎትቶ መለሰኝ፡፡ የቀኝ ዐይኑ ጎን ያሉትን ሁለት የጠባሳ ጭረቶች እነካካለሁ፡፡ ይለሰልሳሉ። እያፈራረቅኩ አሻቸዋለሁ፡፡  
“ገና ዘጠኝ ወራችንኮ ነው ከተዋወቅን”
“ዘጠኝ ቀን ራሱ ከተዋደድን ብዙ አይደል?”
ቅንድቦቹን ሽቅብ ጎትቶ፡፡ የጠባሳው ልስላሴ አመልካች ጣቴ ላይ ተንሸራተተ፡፡
“እኔ እወድህ አይደል?”
“እኔም እወድሻለሁ”
አራዶም የአዲግራት ልጅ ነው፡፡ ወደ ገነቴ ከመጣ ገና ዓመት አልሞላውም፡፡ ዐየሁት፡፡ አተኩሬ ዐየሁት፡፡ አንገቴ ላይ እንደ ማተብ የተጠመጠመብኝ እጁ ጭምቅ አደረገኝ፡፡ እቅፉ ሳላውቀው የሚናፍቀኝን የእናት እቅፍ ይመስላል፡፡ ፈራሽ ሥጋዬ ላይ እንደሚጣበቅ ላብ አይደለም የማይ ብዛት ጠራርጎ እንደሚወስደው፡፡ ጎኑ ሲሸጉጠኝ በአንድ ጊዜ እረጋለሁ፤ እቀልጣለሁም፡፡ ይህ እቅፍ ሕይወት ያለው እቅፍ ነው፡፡ የዚያ የወጣትነት ጊዜዬ በድን እቅፍ ባዳ ነው፡፡ በውርዝውና ዘመኔ አንገት ያስደፋኝ ጨካኝ እቅፍ ተቃራኒ፡፡ ያ የዐሥራ ዘጠኝ ሰማኒያ ስምንቱ አስቀያሚ እቅፍ፡፡
*   *   *
ያኔ ዐሥራ ስድስት ዓመቴ ነበር፡፡ የጠዋት ፈረቃ ተማሪ ስለነበርኩ ርቦኝ ቤት ስደርስ ግቢው ጭር ብሏል፡፡ ተከራዮች ወደየሥራቸው ሄደዋል፡፡ አባዬ እያለ ተመላላሽ የነበረችው ሠራተኛችን ደስታ የለችም፡፡ ታች ሰፈር ያለች በላይነሽ የምትባል እህቷን በሥራ ልታግዝ እንደምትሄድ ማታ ነግራኝ ነበር፡፡ ቤት ከፍቼ ስገባ ሳሎን ውስጥ ጠረጴዛ ላይ የተከደኑ ሁለት ሳሕኖች ዐየሁ፡፡  አጠገባቸው ነጭ ጆግ አለ፡፡ ከጆጉ አጠገብ ደግሞ ሁለት የውሀ ብርጭቆዎች፡፡ ከሁለቱ ሳህኖች ውስጥ የጭልፋ እጀታዎች በስላች ወደ ውጭ ተቀስረዋል፡፡ የሮብ ዓርብ ጾም ጀምሬ ተርቤያለሁ። አብዮትን መጠበቅ አልቻልኩም፡፡ ዩኒፎርሜን ሳልቀይር እጄን ታጥቤ ተቀመጥኩ፡፡
አንድ ቁርጥ እንጀራ ሳሕን ላይ በፍጥነት ዘርግቼ የመጀመሪያውን ሳሕን ከፈትኩ፡፡ አልጫ ምስር ወጥ፡፡ አንድ ጭልፋ አፈሰስኩበትና በጥድፊያ መጉረስ ጀመርኩ። ጨው በዝቶበት ሆርጧል፡፡ ምን ቢያደርጓት ይሻላል ይቺን ልጅ? ጨዉን ወጥ ነው ብላ ማቅረብ ነው የቀራት። ሁለተኛው ጉርሻ ደረቴ ላይ ቆመ፡፡ እንጀራ ቆርሼ አንድ ሁለቴ አሸተትኩ፡፡ አቢ ነው ይሄን ያሳየኝ፡፡ (ኋላ ሲገባኝ የምግብ ሽታ ምራቅ አመንጪ ዕጢዎችን  ብዙ ምራቅ እንዲያመነጩ ስለሚደርጋቸው ነው) ጉርሻው በደረቴ ውስጥ ቀስ እያለ ሲወርድ ይሰማኛል፡፡ ዐይኔ ውስጥ እንባ ሞልቷል፡፡ ሦስተኛ ጉርሻ ስጠቀልል ኮቴ ሰማሁ፡፡ ደንገጥ ብዬ ወደ በሩ ሳይ አቢ ኮቱንና የያዛቸውን ወረቀቶች በሩ አጠገብ ያለ ጠረጴዛ ላይ ያስቀምጣል፡፡
“ዛሬ ደግሞ መጠባበቅም ቀረ?”
እያላመጥኩ በግራ እጄ ሳሕን አንስቼ እያዘጋጀሁለት፡
“ውይ በጣም ራበኝ አቢዬ”
ጓዳ ገብቶ እጁን ታጥቦ መጣ፡፡
“አንቺን ብሎ ጿሚ… መነኩሴ ልትሆኚ ነው?”
በረጅሙ ተንፍሶ አጠገቤ ተቀመጠ፡፡
“ደከመህ አ? ሥራ እንዴት ነው?”
“ሥራ ጥሩ ነው፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ልወዳደር አስቤያለሁ” ሁለት ቁርጥ እንጀራ አንስቶ እየተረተረ የሳህኑን አበባ ሸፈነው፡፡
“ልወዳደር?! ፕሬዝዳንት ምናምን እንዳትሆን ብቻ ስታድግ” የመጨረሻ ጉርሻዬን  እየጠቀለልኩ ከጆጉ ውሀ በብርጭቆ ቀዳሁ፡፡
“ሃሃሃ… እንዴ ያንችን ስልጣንማ አልይዝብሽም”
“ውይ ስንቴ ልንገርህ አንተ ግን… እኔ ዶክተር ነው የምሆነው”
“ቀረብሻ! ደስታ አልመጣችም እንዴ?”
“ምሳ አቀራርባ ነው የሄደችው፡፡ ትውላለች መሰለኝ። ቡና ላፍላ?”
ማኘኬን አቋርጬ፡፡ ወጥ ጨልፌ ሳሕኑ ላይ አደረግኩለት፡፡ ሁለተኛው ጎድጓዳ ሳሕን ውስጥ ድንች በቀይ ሥር ነበር፡፡
“አይ አይ እቸኩላለሁ፡፡ አንቺም ፈተና እየደረሰ አይደል… አረፍ በይና ወደ ጥናትሽ” በሩ አጠገብ ወዳለው ወንበር እየጠቆመ “ያልኩሽን ወረቀት አምጥቼልሻለሁ”
አጫጭር ኖቶች ለማውጣት ሁል ጊዜ ብዙ ወረቀት እጠቀማለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት በነበረው ምርጫ አቢ በምርጫ ጣቢያ ስለሠራ ኩራዝ፣ የእጅ ባትሪ፣ አገልግል፣ ጋሻ ምናምን ምስል ያላቸው የመምረጫ ወረቀቶች በጀርባ ገጻቸው እንድጠቀምባቸው ያመጣልኝ ነበር፡፡  አቢ አንዱን ወረቀት በቁመቱ ለሁለት አጥፌ መጠቀም እንደሚኖርብኝ ነግሮኝ ወደ ቢሮ ሊሄድ ተነሳ፡፡ ትንሽ አረፍ እንዲል ብነግረውም አስቸኳይ ሥራ እንዳለበት ነግሮኝ ወጣ፡፡ የበላንባቸውን ዕቃዎች ማነሳሳት ጀመርኩ፡፡ ከደጅ እጁን  ሲታጠብ ውሃ ከቧንቧ ሲፈስ ይሰማኛል፡፡  
አቢ ከግቢ እንደወጣ የምወደውን ባዮሎጂ ትምህርት ለማጥናት አጋዥ መጽሐፌን ከመደርደሪያው ላይ አነሳሁ። ከኋላዬ ጥላ ነገር ከበደኝና ስዞር የመጀመሪያዋን ሰርቪስ ክፍል የተከራየው ጥቁር ልጅ በር ላይ ቆሟል። አቢ እስኪወጣ ይጠብቅ የነበረ ይመስላል፡፡ ደንገጥ አልኩ፡፡ ፊት ለፊት ያለውን ጸጉሩን እየጠቀለለ ዐሥር የሚሆኑ ዘለላዎችን ግንባሩ ላይ አስተኝቷል፡፡  እንዴት ያለ ኮቴ ቢስ ነው በእመቤቴ፡፡ ደፉ ላይ ቆሞ በሩን በቀኝ እጁ ተደገፈ፡፡ ምን እያንሿከከ ያመጣዋል?
ጥቁር ከንፈሩን በሽገናም ጥርሱ እንደ መንከስ፤ እንደ ኑግ ልጥልጥ በጠቆረ ምላሱ እንደመላስ፤ ባዶ ፈገግታ ፈገግ እንደማለት እያለ ዐየኝ፡፡ አፈጠጠብኝ ልበል እንጂ። ደስታ ለምንድን ነው ቶሎ የማትመጣው? ዐይኖቹ ተቅበዘበዙ። ፈራሁት፡፡ በቀኝ እጁ የያዘውን ያልተለኮሰ ሲጋራ ወደ ክርታሱ መልሶ ወደ ቤት ገባ፡፡ “ግባ እንጂ” ብዬ ስጋብዘው ትዝ አይለኝም፡፡ ጉሮሮዬ በአንዴ ደርቋል፡፡
በሩን ከኋላው ዘግቶ እየተጠጋኝ ሲመጣ ወደ ኋላ እየሸሸሁ ባለኝ ዐቅም ሁሉ “አቢ!” ብዬ ጮህኩ። ሰካራሞቻቸው በጌሾ ተሞልተው በተደባደቡ ቁጥር ድርብ ኡኡታ የሚያሰሙትን የእነ ደስታን ዐይነት እሪታ መንታ ምላስ ኖሮኝ ባወጣ ተመኘሁ፡፡ ግድግዳው ጀርባዬን ሲነካኝና አፌን በሻካራ እጁ ሲያፍነኝ አንድ ሆነ፡፡  ላብ ላብ ይሸታል፡፡ መጽሐፌ ወደቀ፡፡ ልታገለው ሁሉ አልቻልኩም፡፡ በቀኝ እጁ ቀኝ እጄን ይዞ በፍጥነት ሲጠመዝዘኝ ጀርባዬ ወደ እሱ ፊት ሆነ፡፡
ምን እየተደረገ እንደሆነ ለመረዳት ብዙ ጊዜ ወሰደብኝ፡፡ ስለመደፈር ሲወራ እሰማለሁ፡፡ አንድ ቀን እኔ ላይ እንደሚደርስ አላስብም ነበር፡፡ ስዞር አፌን ለአፍታ ያክል ለቀቀኝ፡፡ ደግሜ ጮህኩ፡፡ ምን ነበረበት አቢ ቡና ቢጠጣ? ግራ እጁ በትከሻዬ ዞሮ መልሶ አፈነኝ፡፡ በአፍንጫዬ ከላይ ከላይ እተነፍሳለሁ፡፡ በቀኝ እጁ ሁለት እጆቼን አስሯል፡፡ በሰውነቱ ከግድግዳው ጋር አጣብቆ ያዘኝ፡፡ ሊያጠቃኝ የተዘጋጀ ደም የወጠረው ገላው ቂጤ ላይ ይሰማኛል፡፡ ምን ነበረበት ደስታ ዘመዶቿ ጋ በጠዋት ደርሳ ብትመጣስ? አፉ አንገቴ ላይ ነው፡፡ ያለከልካል። የዚህ ልጅ ድፍረቱ ሁለት ነው፡፡ ከግድግዳው ጋር በሰውነቱ አጣብቆ ያዘኝ፡፡ ደፍሮ ቤቴ ይገባል? ግራ እጁ አሁንም አፌን አፍኗል፡፡ ደፍሮስ እንዲህ ያደርገኛል?  አየር እያጠረኝ ነው፡፡ በፈጠጠ ዐይኔ በጉንጬ የተደገፍኩት አረንጓዴ የግድግዳ ላይ አፍጥጫለሁ፡፡  ጠረጴዛው ላይ የእናቴ ፎቶ ይታየኛል፡፡ አባዬ ትዝ አለኝ፡፡ ላቤ ችፍ ብሏል። ልቤ ይደልቃል፡፡ አማራጭ አጥቼ እፈራገጣለሁ፡፡ ቀኝ እጁ እጆቼን ለቆ ወደ ደረቴ መጣ፡፡ የቀኝ ጡቴን በኀይል ጨበጠ፡፡ ሊፈርጥ ሁሉ መሰለኝ፡፡ የታፈነ የሕመም ድምፅ አወጣሁ፡፡ እጆቼ ምንም ማድረግ አቅቷቸው ግራና ቀኝ አየር ላይ ተንጠልጥለዋል፡፡ እንባ ከዐይኖቼ ይወርዳል፡፡ አፌን ቢለቀኝ ምን ብዬ እደምጮህ አላውቅም፡፡
ወደ ኋላ ጎትቶ በሚያስገርም ፍጥነት ወለሉ ላይ በድንገት ጣለኝ፡፡ በቂጤና በእጆቼ ተዘረፈጥኩ፡፡ ላዬ ላይ ወደቀ፡፡ አየር ስቤ ትርጉም የሌለው ነገር ከለቅሶ ጋር ቀላቅዬ ለመጮህ ሞከርኩ፡፡ ለራሴም አልሰማ አለኝ። አንድ እጁ ተመልሶ አፌ ላይ ሆነ፡፡ ወደ ቀኝ ዞርኩ። መጽሐፌ በአፉ ተደፍቷል፡፡ ማጓራቴን አላቆምኩም። ግራና ቀኝ ስወራጭ አምፖሎዬ ተበታትኖ ወለል ይወለውላል፡፡ በእጆቼ ልገፋው፣ ልቧጭረው፣ ልመታው እሞክራለሁ፡፡
አፌን ያላፈነውን እጁን ወደታች ላከ፡፡ ሕመም ወደ ውስጤ ገባ፡፡ እጁ እንዳፈነኝ ሰውነቱ ይመላለሳል፡፡ ሕመም ይጠዘጥዘኛል፡፡ ነጩ ኮርኒስ ላይ የዝናብ ጠብታ የፈጠረው  ውል የሌለው ቡናማ ቅርጽ ይታየኛል፡፡  
ሁለት ደቂቃ? ዐሥር ደቂቃ? አምስት ቀን? ምን ያክል ጊዜ እንዳለፈ አላውቅም፡፡ አፌን አንዳፈነ እያለከለከ ከላዬ ለመነሳት ሞክሮ አቃተው፡፡ በጉልበቱና በቀኝ እጁ ወለል ተደግፎ ዝቅ ብሎ ወደ ታች ዐየ፡፡ ድፍርስ ዐይኖቹ ፈጠው ዐየኝ፡፡ ደንግጧል፡፡ የሆነ ነገር ልክ እንዳልሆነ ገባኝ። አፌን ያፈነ እጁን አንስቶ ሀፍረቱን ከውስጤ ሊያወጣ እጁን ሰደደ፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜ ሞከረ፡፡ ጮህኩ፡፡
“የሰው ያለህ! ኧረ ድረሱልኝ!”
“በገወርጊስ… ምንዲን ነው ያረግሺኝ አንቺ ውሻ?”
ጠንካራ የባላገር ቅላጼ እንዳለው አላውቅም ነበር። ሊወጣ እየለፋ ይርበተበታል፡፡ ለምን ያክል ደቂቃ እንደቆዬ አላውቅም፡፡ ከውጭ የሚንደረደር ኮቴ በፍጥነት እየቀረበ ሲመጣ ይሰማኛል፡፡ ግን ቶሎ አይደርስም፡፡
“ምንድን ነው ጦቢያዬ?!”
አቢ በሩ አጠገብ ተሰማኝ፡፡ ደፋሪዬ ቀና ብሎ ወደ በሩ አፈጠጠ፡፡
“አቢዬ ድረስልኝ!”  
በሩ ተበረገደ፡፡ ተንጋጥጬ ዐየሁ፡፡ አቢ ተዘቅዝቆ ይታየኛል፡፡
ተወርውሮ መጣና በጫማው አገጩ ላይ ጠለዘው፡፡ አለቅሳለሁ፡፡ ልጁ ላዬ ላይ ያቃስታል፡፡
“ተነስ አንት ውሻ፡፡ እገድልሃለሁ”
ከልጁ አፍንጫዎች ደም ደረቴ ላይ ይንጠባጠባል፡፡
“ተነስ!”
አቢ የልጁን ልብሶች ጨምድዶ ሊያነሳው ሞከረ፡፡ ልጁ የሚያደርገው ነገር ጠፍቶበታል፡፡  
“እምቢኝ ብሎኝ ነውኮ!” የሞት ሞቱን ተናገረ፡፡
“ምን አባክ ነው እምቢ የሚልህ አንት ግማታም ባላገር…. የእኔን እህት?! አንት ልክሥክሥ!?”
አቢ ሊያነሳው ይለፋል፡፡ እኔ እየጮህኩ አለቅሳለሁ፡፡ ከሕመሙ በላይ ሀፍረቱ ሊገለኝ ደረሰ፡፡
ሀፍረቴ ከዚህም ይብሳል፡፡ ምክንያቱም ትንሽ ቆይቶ ሊያሳብደኝ ጥቂት የቀረው ነገር ሆነ፡፡ ክፍሉ ውስጥ አንድ ቄስ፣ ሁለት ፖሊሶችና ሁለት የሰፈራችን ሽማግሌዎች ተጨመሩ፡፡ ሽማግሌዎቹ “ጉድ!” ለማለት፡፡ ፖሊሶቹ ወንጀል ለመመርመር፡፡ ቄሱ ደግሞ የታሰረውን በፀሎታቸው ሊፈቱ፡፡ ከየት ከየት ተሰባሰቡ በእመቤቴ!
ዐይኖቼን መግለጥ አልቻልኩም፡፡ በምስጢር የሚደፈሩ ሴቶች ዕድለኞች ናቸው፡፡ በጸጥታ አለቅሳለሁ። ስድስት ሰዎች ባሉበት እንዲህ ሆኜ ከምገኝ ስድስቴ ብሞትን መረጥኩ፡፡ ግቢያችን በሰው ተሞልቷል፡፡ ልጁ የአፍንጫውን ደም ለማቆም እየሞከረ አሁንም ላዬ ላይ አለ፡፡
ከላይ ሆኖ ፈረስ ግልቢያኛ ሲንቀሳቀስ ያየሁትን አሁን ድረስ ልረሳው አልችልም፡፡ በድንጋጤ፣ በእልህና በሀፍረት መካከል ሆኜም ቢሆን አፈር ብጥብጥ የተነፋበት የሚመስለው የርካሽ ቀይ ሸሚዙ ኮሌታ ላይ የተጣበቀው ዕድፍ ዐይኔ ላይ አለ፡፡ የቆሸሸ ኮሌታ እንዴት ጠላሁ! አሁን ድረስ ኮሌታ ትንሽ እንኳን ቆሸሽ ብሎ ሲታይ አልወድም፡፡
“ሸሚዝህን ልጠብልህ” አራዶም ምቹ እቅፉን ሲያላላልኝ፡፡
በሙጫ ያጣበቁኝ ያህል ተለጥፌበታለሁ፡፡ ከቁምሳጥኑ ትይዩ የተቀመጠ ወንበር ላይ የተከመሩት ልብሶቹ ብርድ እንደገባው ሰው ተጨብጠው ይታዩኛል። የጥቁር ሱሪው አንድ እግር ተንጠልጥሏል። ነጭ ሸሚዙ ላይ ያረፈው ቀጭን የብርሃን ዘንግ እንደ ፍሎረሰንት ያበራል፡፡ አራዶም ጨለማው እኔነቴ ውስጥ እንደሚሆነው፡፡
“ኪሱ ውስጥ ዕቃ አስቀምጠሃል?” ደረቱ ላይ ያረፈው ቀኝ ጆሮዬ ስለተደፈነ ድምፄ ጆሮዬ ውስጥ እንደማስተጋባት እያለ፡፡
“መቼ ነው እንዴ የቀየርኩት? ትናንት ከሰዐት ነውኮ” ደረቱ ላይ ሆኜ ስሰማው ጭንቅላትሽን ካላርገፈገፍኩ የሚለኝን ይሄን የድምፁን ንዝረት እወደዋለሁ፡፡
“‘መቼ ነው እንዴ’ አይባልም… ስንቴ ልናገር?” ፈገግ እያልኩ፡፡
ተነስቼ ሸሚዙን ማጠብ ፈልጌያለሁ፡፡ የሰውነቱ ወዝ ግን ሙጫ ሆኖብኛል፡፡ ጠረኑ እንደ ማስትሽ ከገላው ጋር ሰፍቶኛል፡፡ መነሳቴ ሞት መስሎ ነው የታየኝ፡፡ ከሞት መነሳት ሳይቀል ይቀራል? ሂሂሂ
እንደምንም ተነሳሁ፡፡ ላብ ያጣበቀው ገላችን የኔን አነሳስ ተከትሎ ቀስ እያለ ሲላቀቅ ቆዳ ላይ የተጣበቀ ፕላስተርን እንደ መላጥ ዐይነት ነው፡፡ እየተንጠራራሁ ተነስቼ ከትከሻው ዝቅ ብዬ ሳምኩትና አዛጋሁ፡፡
በላዩ ላይ ድሄ አልጋው ጫፍ ተቀመጥኩ፡፡ የወለሉ ቅዝቃዜ በውስጥ እግሮቼ ይሰማኛል፡፡ እግሮቼ አጠገብ የጡት መያዣዬ መንታ የሸከላ ድስቶች መስሎ ወድቋል፡፡ ፓንቴ የአራድ ጫማ ላይ፡፡ ቆምኩ፡፡
“ኧረ ጦቢያዬ የሆነ ነገር ልበሺ” በሀፍረትና በእንክብካቤ፡፡ ወይስ በእንክብካቤና በሀፍረት? የቱን ነበር ያስበለጠው?
ሱሪዬ አጠገብ የወደቀ ፓንቴን አንስቼ ለበስኩ፡፡ ፒጃማ ደረብኩና ከቤት ወጥቼ ቧንቧው አጠገብ ለልብስ ማጠቢያ ተደራርበው ወደተቀመጡት የመኪና ጎማዎች ተጠጋሁ፡፡ አጥሩ ጥግ አንዲት የጠወለገች የጦቢያ ቅጠል አለች፡፡ አበቦቿ ረግፈዋል፡፡ ፊኛዎቿ እንደ አሮጊት ቆዳ ተኮማትረው ደርቀዋል፡፡ ሸሚዙን በፍጥነት አለቅልቄ ወደ ቤት ተመልሼ ገባሁ፡፡     
አልጋው አጠገብ ያለው ኮመዲኖ ላይ ትልቅ ፓናሶኒክ ቴፕ ተቀምጧል፡፡ ኮመዲኖው ከላይ አንድ ትልቅ በር ከታች ደግሞ ሁለት ትናንሽ ክፍሎች አሉት፡፡ ባየሁት ቁጥር ባለ ሦስት በር ኮመዲኖ አይደለም የማየው። የሚታየኝ አምስት አመታት ወደ ኋላ የሚያስሮጠኝ የትዝታ ድልድይ ነው፡፡  
*   *   *
ሀያ አንድ ዓመቴ ነበር፡፡ ያ ጥንዚዛ አስተኔ ነድፎኝ መርዙ የሕይወቴን ዐምድ አናጋ፡፡ ሰዎች ጥፋተኛዋ እኔ እንደሆንኩ ሁሉ አድርገው ይኮንኑኛል፡፡ አባዬ አልተነገረውም፡፡ አቃቤ ሕግ ሆኖ አባዬ ላይ ባደረገው ምክንያት የተቆራረጥንው አጎቴ አሁን ደግሞ በጠበቃነቱ ወንጀለኛውን ወግኖ ፍርድ ቤት ቆመ፡፡ ይሄን ማን ያምናል? የዕድል መንገድ ስትጠም ውሃ እንኳን ያንቃል፡፡
የሩካቤ ጥሟ እንደማይረካላት ውሻ ሆን ብዬ ያደረግኩት እያስመሰሉ ከእንስሳ አወዳደሩኝ፡፡ መጠቋቆማቸው አልበቃ ብሎ ባወጡልኝ ቅጽል ስም እያቆላመጡ ይሰድቡኛል፡፡ እሱ ሲሰለቻቸው ያወጡልኝን ስም በፉጨት ይሉታል፡፡ አንገቴን እንደ ከዘራ ሰብሬ በቤትና በትምህርት ቤቴ መካከል ከመመላለስ ውጪ ለገበያ እንኳ ከቤት መውጣቴ ቀረ፡፡ ግንባር ቀደም አማራሪም ወጣኝ፡፡ ብቸኝነት ሰለጠነችብኝ፡፡
የልጅነት ጓደኛዬ ጀሚላ ዐረብ አገር ሄዳለች፡፡ ምድር ላይ ያሉኝ ብቸኛ ዘመዶች አክስቴና (የአባቴ እህት) ልጆቿ ጅማ ነው የሚኖሩት፡፡ አቢ ሥራ አምሽቶ ይመጣል። ያለሱ የሚቻል አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ አቃተው መሰለኝ አባዬ ጋ ሐረር ብሄድ እንደሚሻል ተነጋግረን ደወልንለት፡፡ ቢሮ መምጣት ካቆመ ሦስተኛ ቀኑ እንደሆነና የት እንዳለ እንደማያውቁ ነገሩን፡፡ ዕድል ከዚህ በላይ ይጣመማል? ሳምንት ምናምን ቆይቶ አባዬ ደወለ። ከሳሾቹ ተከታትለው ስለደረሱበት ከዚያ ለቅቆ ደብረ ዘይት ከተማ እንደገባ ነገረን፡፡ ቀጥሎ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡ የእኔም ነገር በዚያው ተዳፍኖ ቀረ፡፡
*   *   *
እንደ ኩይሳ ነበርኩ፡፡ የበደል ምስጥ ውስጤን እየሸረሸረ ላዬን ያፀናኝ፡፡ ከሀሜትና ስም ከመስጠት አረፍ ብሎ ከሩቅ ለሚያየኝ ጠንካራ መስዬ እታይ ነበር። አቢ ብቻ ነበር የሚያውቅብኝ፡፡ ባለችው ትርፍ ጊዜ በሽሙጥና በተረባቸው የተዳፋ አንገቴን ሊያቃና ይለፋል። መረተ የሚባለው የዚያ ታቸ ሠፈር ነጋዴ ትንሽ ወንድም ያ ትናንት የተወለደ ውሪ እንኳ ቅጽል ስሜን አውቆ ጮክ ብሎ ጠራኝ፡፡
“ጦቢ ሠረገላ!”
አንደበቱ እንኳ በቅጡ ያልተፈታ ኮልታፋ ነው፡፡ እንደሆነ እንደ እብድ ነገር ሠራኝና ደብተሬን በትኜ ላንቀው ሮጥኩ፡፡ ሠረገላ ምን እንደሆነ እንኳን አያውቅምኮ፡፡ አልጠበቀም መሰል ተደናብሮ ወደ ቤት ገብቶ አመለጠኝ።   
ጀሚላ አንዳንዴ እየደወለች ለረጅም ሰዐት ታዋራኛለች፡፡ ስለ ሰፈር ሰው፤ ስለ ትምህርት ቤት ጓደኞቻችን፤  ማን እንዳገባ፤ ማን እንደወለደ፤ ማን እንደሞተ ስታስለፈልፈኝ ትውላለች፡፡ የሆንኩትን ጉድ ሰምታለች፡፡ ስታዋራኝ ግን እንዳልሰማ ሆና ነው። ለመጨረሻ ጊዜ የደወለች ጊዜ ታናሽ እህቷ ሐውለት በቀጣዩ ዓመት ስለምታገባ ለሠርግ ልትመጣ እያሰበች እነደሆነ ነገረችኝ፡፡ ብትመጣ ባትመጣ ግድ የለኝም፡፡  
በአማራሪነቴ ስመሰጥ “ለምን ሆነ?” ብዬ እጀምራለሁ…
ለምን እኔ ላይ? መደፈሬ ሳያንስ እንዲህ ያለ እንግዳ ነገር ለምን እኔ ላይ ሆነ? በርካሽ እንስሳ ምሳሌ እንጂ በሰውኛ ልምድ የማይብራራ ነገር ለምን እኔ ላይ ይሆናል? ዕድለ ቢስነት እንጂ ማን የሚወደው አባቱን በዚህ ዐይነቱ ጊዜ ከጎኑ ያጣል? አለመታደል እንጂ የጡቷን አንገር ሳያጣጥም ማን እናቱን በሞት ያጣል? የማንስ አጎት የበዳዩ ጠበቃ ሆኖ ይቆምበታል?  
*   *   *
በወንዱ ውሻ ብልት ጫፍ ላይ ቡልቡስ ግላንዲስ የሚባል እጢ አለ፡፡ ውሻው በሰላ ከመጠመዱ የቁላው ጫፍ ያብጥና ከሴቷ ውስጥ እንዳይወጣ ያግደዋል። እብጠቱ ሟሾ መውጣት እስኪችል ድረስ እስከ ሠላሳ ደቂቃ ሊቆይ ሁሉ ይችላል፡፡ ይህ ነገር በእንግሊዝኛ ዘ ታይ ፊኖሚኖን (the tie phenomenon) ይባላል፡፡ ታዲያ ድፍረቱም ሆነ ውስጤ ገብቶ ለመውጣት አለመቻሉ እንስሳ የሚያስመስለው እሱን ቢሆንም የማኀበረሰብ ፍርድ ግን እኔን ኮንኖኛል፡፡ ስሜቷ ስለማይረካ በቁሌታምነት እያቆየችው አይደለም፡፡ አስኪቱ አብጦ እንጂ ከረቤዛዬ ቆላፊ ሆኖ እንዳልሆነ ለማስረዳት በየቤቱ እየዞርኩ የድቁርናቸውን ካባ መግፈፍ አለብኝ? ይሄንንስ ቤቴ ውስጥ ካስቀመጥኳት ደስታ ከሚሏት ጉድ መጀመር አለብኝ?    
“እንዴው ግን ጦቢ… ዴፈርሽኝ አትበይኝና… ‘ነገር የተበላሸው የጦም ቀን ስለነበረ እንጂ መጀመሪያ ላይ ፈልጋ ነበር ያዴረገችው’ ይላል ሰው…”
ቃል ሳልተነፍስ ትቻት መኝታ ክፍሌ ገባሁ፡፡ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ እንደዚያን ቀን አላለቀስኩም፡፡ ከደስታ ጋር ያለኝ ግንኙነት ላይመለስ ተቀየረ፡፡ ከትእዛዝ ውጪ ከእሷ ጋር ማውራት ተውኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ግንኙነታችንም በዚያው የተቃኘ ሆነ፡፡
*   *   *
በዚህ ሁሉ መሀል ግን አልፎ አልፎ ሴትነቴ እያንሠራራ የሰው ጥማቴ ይጋጋላል፡፡
ግን ማን አለኝ?
ብዙ የሚያውቁና የማያውቁ የሚመስሉ ወንዶች ሊያናግሩኝ ይሞክራሉ፡፡  አንድም ፊት የሰጠሁት ግን አልነበረም፡፡ ምናልባት የሚወራው ነገር እውነት መሆኑን ሊያረጋግጡ ፈልገው ይሆናል፡፡ ያስጠሉኛል፡፡ ብሰጣቸው ሄደው የወሬያቸው ማስረጃ አድርገው ሊያቀርቡኝ ነው፡፡
“ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም…ሃሃሃ” የመሰለ ነገር ቢዘባበቱብኝ ነው፡፡  እንዲሁ በጭንቅላቴ ሀሳብ በእጆቼ ዳንቴል ስተበትብ እውላለሁ፡፡ በማስውበው ክር ሰው ሰርቼ አናግረው ይመስል፡፡ ወይ ደግሞ መደርደሪያ ላይ ካሉት መጽሐፎች (ልብ ወለድ ወይ ባዮሎጂ) አንዱን ሳነብ፡፡ እንዲህ እንዲህ ሲሆን የወሬ ንፋስ ከግራ ቀኝ እያላጋኝ ድፍን አምስት ዓመታት አለፉ፡፡
1992 ዓ.ም. ፀደይ ነበር፡፡ ወቅት ግራጫ ማቁን አሽቀንጥሮ ጊዜን ለፀዓዳ ለባሹ መስከረም የዳረበት ወር። ቀጭን ዝናብ የለበሰችው ምድር መጥገግ የጀመረችበት እሁድ ቀን፡፡ ቆፈን ያኮማተራቸው ዕፅዋት እጆቻቸውን ለመዘርጋት አቆብቁበው፡፡ በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ ኪሮሽና ክር ሳውሰበስብ ቆይቼ አንድ ሽፋኑና ጥቂት የመጀመሪያ ገጾች የጎደሉት መጽሐፍ አነባለሁ፡፡ አሮጌ ነው፡፡ የጀርባ ሽፋኑም ተገንጥሏል። ሳሎን ውስጥ ከተከፈተው ሬዲዮ የእጅጋየሁ ሽባባው “ዐደይ አበባ” ይሰማኛል፡፡ ጠረጴዛው ላይ ሳሙና ላይ ከተሰካው ሣር ጢስ የሚነሳ ማለፊያ ጠረን ከቤት ሞልቶ እየፈሰሰ ያለሁበት ድረስ ከሙዚቃው ተደባልቆ ይመጣል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ አንዲት “ሲልቪ” የምትባል የተቆላች ገጸባህሪ አለች፡፡ አሳፋሪ መጽሐፍ ነው፡፡ ማን እንዳመጣው ሁሉ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ አቢ እንዲህ ዐይነቱት ነገር ያነብ ነበር ብሎ ማመን ከበደኝ፡፡   
በር ተንኳኳ፡፡ ደስታ ኩሽና ውስጥ እንጀራ እየጋገረች በጎን ወጥ ትሠራለች፡፡ አቢ በምርጫ ለመወዳደር እየተዘጋጀ ሥራ ስለበዛበት እሑድ ጭምር ቢሮ ይገባል። ተነስቼ ሄጄ የተንኳኳውን በር ስከፍት በየነ የሚሉት ልጅ የሆነ ሣጥን ነገር ተሸክሞ ቆሟል፡፡ ፊቱ በፂም ተሸፍኗል። ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባሮ ከመጣ ጀምሮ ዐይዳ ዳቦ ቤት አጠገብ ያለች ዛፍ ጥላ ሥር አይጠፋም፡፡ ብዙ ከማንበብ ብዛት ነካ ያደርገዋል ሲሉት ሰምቻለሁ። የማይገባቸውንና የማይረዱትን ሁኔታ በሚገባቸውና በሚያውቁት ሲገልፁ፤ እኔን “ሠረገላ ቁልፍ” እንዳሉኝ ይሆናል በየነንም “ጠሽ ነው” የሚሉት፡፡
“አብዮት ነው የላከኝ”
ደስታ ቤት ውስጥ እንዳለች ባውቅም ፍርሃት ነገር ተሰማኝ፡፡ በሩን በቀኝ እጄ ይዤ ግራ እጄን ወገቤ ላይ አሳርፌ ጮክ ብዬ ተጣራሁ፡፡  እንደተሸከመ ቆሟል፡፡
“ደስታ፤ አትሰሚም?!”
ጥቂት ቆይታ በሊጥ የተጨማለቀ ማዞሪያ ይዛ በሩ ጋ ቆመች፡፡ ሰፋ አድርጌ ከፈትኩለትና ገባ፡፡ በሩን ከኋላችን ዘጋሁ፡፡ ወደ ቤት ውስጥ እንዲያስገባው እሱ እየመራ ወሰድኩት፡፡ የተሸከመው ጀርባው ላይ እንደሌለ ሁሉ ዘና ብሎ ይራመዳል፡፡ “አቢ ክፍል ይቀመጥ?” ሊጥ የተቀባባ ማዞሪያዋን የምታሳርፍበት ቦታ እየፈለገች፡፡
“እዚሁ ጥግ ይዞ ይቀመጥና ቦታ እናስይዘዋለን” ወደ ንባቤ በፍጥነት ለመመለስ ቸኩያለሁ፡፡ ምናልባትም ከነጋ ጀምሮ ከደስታ ጋር የተለዋወጥናቸው ቃላት እኚሁ ብቻ ነበሩ፡፡
“አሆ… መስከረም ለምለሙ መስከረም ለምለሙ
ብሩህ ዕንቁጣጣሽ ደስታ ለዓለሙ
እሰይ መስቀል ጠባ ቅዱስ ዮሐንስ
ብወድህ እኖራለሁ ብጠላህ መሰስ…”
በደስታ እርዳታ ኮመዲኖውን አስቀምጦ ሲወጣ በረንዳ ላይ ጅምር ዳንቴሌ አጠገብ የሳጣራ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠውን መጽሐፍ አንስቶ ዐየት አደረገ፡፡ ከኋላው ቆሜያለሁ፡፡ እንዲህ ዐይነት መጽሐፍ እንደማነብ ማንም እንዲያውቅ አልፈልግም፡፡
“ትኩሳት!” አለ “ዩሬካ!” በሚል ድምፅ፡፡
ርዕሱ እንደሚሆን ገመትኩ፡፡ ግን አንድ ገጽ እንኳ ሳያነብ በዚህ ፍጥነት እንዴት ዐወቀ? ይሄን የባለጌ መጽሐፍ ከማወቅም በላይ ሸምድዶታል? ድጋጤዬ ጠፍቶ ወዲያው ስረጋጋ ይሰማኛል፡፡   
“ስብሐት-ይህን-መጽሐፍ-ሲጽፍ…” ሲናገር ቃላቱን ይቆራርጣል፡፡ “ግዴለም-ተዪው”
መጽሐፉን የነበረበት መልሶ ደረጃውን ወረደ። ደልዳላ ጭኖቹ ላይ የጨቀየ ቤዥ ካኪ ሱሪ ለብሷል።  ጥቁር ግዙፍነቱ ቢትልስ/ታርትል-ኔክ ቲሸርት ውስጥ አንደ ኤሊ ተደብቋል፡፡ ውሀ ውስጥ ነክረው ቢያወጡት ቁንጅናው የሚገለጥ ዐይነት ልጅ ነው፡፡
የልብስ ማጠቢያ ቦታችን አጠገብ ያለች የደረቀች የጦቢያ ቅጠል ጋ ሲደርስ ቆም አለና ፊቱን አዙሮ፡
“ቆይ-ግን-አንቺ-ሁል-ጊዜ-ብቻሽን…” ያላለቀ ጥያቄ እንደ ሴኮንድ ቆጣሪ በሚቆራረጥ ድምፅ፡፡
ምን እንደነካኝ እንጃ በራሱ ድምፅ መለስኩለት፡
“ቆይ-ግን-አንተ-ምን-ያገባሃል?”
“ማለቴ አንቺን የመሰለች ልጅ እንዴት ብቸኛ ትሆናለች ብዬ ነው” ንግግሬ ሽሙጥ መስሎት መሰለኝ አነጋገሩን አስተካከለ፡፡
እጁን ወደ ግራ የሱሪው ኪሱ ሰደደና ሲጋራ አወጣ፡፡ ከቀኝ ኪሱ ክብሪት መዘዘ፡፡  
“ግዴለም ተዪው”
በእጁ የያዘውን ሲጋራ ሊያቀጣጥል ሲል ነፋስ ስላስቸገረው ፊቱን አዞረ፡፡ ትንሽ ጎበጥ እንደማለት ብሎ ለአፍታ ቆየ፡፡  ከማይታየኝ ፊቱ አካባቢ ጭስ ተበተነ፡፡ ፈጠን ፈጠን እያለ ተራምዶ ከግቢ እንደወጣ የትምባሆ ጠረን ከቤት ከሚወጣው የሰንደል መዐዛ ጋር ተቀላቅሎ ለአፍንጫዬ ደረሰ፡፡
ምሽት ላይ አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ የቀን ውሎዬን አብላላለሁ፡፡ ወደ ጭንቅላቴ የመጡት ሦስት ተራ ቃላት ናቸው፡፡ በሦስት አዘቦታዊ ቃላት ገለጸኝ፡፡ አድናቆት አዲሴ ሆኖ አይደለም፡፡ የጎረምሶችን የለከፋ ቃል መስማት ከመጀመሬ በፊትና በአድናቆት ተጎልጉለው ሊወጡ ጥቂት ከቀራቸው ዐይኖች ጥቅሻ መቀበል ከመጀመሬ በፊት ጀምሮ አባቴ ይለኝ ነበር… “የኔ ቆንጆ”፡፡ ይሄም እስከ ዘላለም ላይረሳኝ በልቦናዬ ግድግዳዎች ላይ በደማቅ ቀለም ተነቅሷል፡፡
ይህ ጎረምሳ ሦስት ተራና አዘቦታዊ ቃላት ተናገረ፡፡
“አንቺን-የመሰለች-ልጅ”
እንዴትስ ግልብ እንዴትስ ጥልቅ ናቸው? እኔን የመሰለች ልጅ! እኔ ምን እመስላለሁ? ብዙ ብዙ ነገር አስቤ ተኛሁ፡፡
*   *   *
ከዓመት በኋላ ሌላ ሰው ነበርኩ፡፡ ከልብስ ሁሉ የማዘወትረው አንሶላ ሆነ፡፡ እሱንም እጋፈፈዋለሁ፡፡ ከአለባበስም ሁሉ የሚመስጠኝ በቆዳዬ መታየት ሆነ፡፡ (አንድ ይርዳው የሚሉት የደስታ እና የበላይነሽ ታማኝ የጠላ ደንበኛ፤ የሆነ ተረበኛ ሰካራም “ሴት ልጅ ምን ስትለብስ ደስ ይልሃል?” ብለው ቢጠይቁት ለአፍታ ያክል አሰብ አድርጎ “ቆዳዋን!” ማለቱን  ሰምቻለሁ)፡፡
የከተማው ወንዶች በበትረ ሙሴያቸው እንዲከፍሉኝ እንደ ቀይ ባሕር ሆንኩላቸው፡፡ እንደ ሲልቪ ነፃ ሆንኩ ነገር፡፡ ሰዎች አሁንም እንደ ጦር ማስቲካ ያኝኩኛል፡፡ ወንዶቹ እያሙኝም ይተኙኛል፡፡
“እንዴት እንዲህ ተለወጥሽ?” የሚል ቅን ጠያቂ ቢኖር እንደ ዋቢ የምጠቅሰው ያን በየነ የተባለ መልከኛ ልጅ ነው፡፡ ከዚያች ቀን በኋላ ለራሴ ዐዲስ ብያኔ ሰጠሁ፡፡ አቢ ፓርላማ ተመርጦ ዐዲስ አበባ እስከገባበት እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ግን መለወጤ በድርጊት አልተመነዘረም ነበር፡፡
አቢ አንዳንድ ነገሮችን ካስተካከለ በኋላ እኔ ቆይቼ እንድከተለው ተስማምተን እንደሄደ ደስታን አሰናበትኳት። ብቻዬን መኖር ጀመርኩ፡፡
እኔን የመሰች ልጅ ብቸኛ መሆን አይገባትም፡፡ ቀስ እያልኩ አንገቴን ቀና ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ፡፡ ተነስቼ መራመድ ጀመርኩ፡፡ ቀስ በቀስ የለየልኝ ሂያጅ ሆንኩ፡፡ የዕንቁልጢዬን በር ለሚያንኳኳ ኮለል ሁሉ እምቢ ብሎ የመከላከል ዐቅሜ ተዳከመ፡፡ ልክ ሰውነት ተውሳክ ለመከላከል ዐቅም ሲያጣ እንደሚሆነው ዐይነት፡፡
*   *   *
ኪንታሮት በሽታን የመከላከል ዐቅማችን ሲዳከም የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በተለይ በልጆች ላይ ይታያል፡፡ መንስዔውም በቀላሉ ተላላፊ የሆነ ቫይረስ ነው፡፡ አሁን አሁን ልጆች ፊታቸውና እጆቻቸው በዚህ ነጠብጣብ ሲወረር ሰለጠንን የሚሉ ዘበናይ እናቶች የጦቢያ ቅጠልን ደም ንቀው ኪንታሮቱን የጥፍር ቀለም ይቀቡታል። ቫይረሱን ግን ደሙም ሆነ ቀለሙም ሊገድለው አይችልም። ቀለም ቀቢዎቹም ሽግግራቸው ከባሕላዊ ድንቁርና ወደ ዘመናዊ ድንቁርና እንደሆነ ለመረዳት አይችሉም፡፡ እኔ ግን ከተክሉ ደም ይልቅ ፊኛውን  መሆን መረጥኩ። መልዓክ አባዬ ስሜን ሲያወጣ ከመድኃኒትነቴ ይልቅ ፊኛነቴ በራእይ ታይቶት ይሆናል፡፡ ወንዶች በቮሊቦል የሚቀባበሉኝ እንክብል ሥጋ ነኝ፡፡ ወይም በዘንጋቸው የሚያጎኑኝ የገና ዕሩር፡፡ እንደ በዛብህ ያሉ ግንባር ቀደም ቆሞ ቀሮች ሳይቀሩ የራሳቸው ሊያደርጉኝ “ላግባሽ” ሁሉ ይሉኛል፡፡ የጠያ ቂዎቼ ሁሉ ድምጽ ግን እንደ ቢራቢሮ ክንፎች ጭብጨባ፤ እንደ ሹክሹክታ ነበር።   
ኳስ አበደች እንደሚጫወቱባት ጥን፟ግ በአንዱ እየተጠለዝኩ ሌላው እጅ ስገባ በመጨረሻም ቀልቦ ሊያረጋጋኝ የቻለው አራዶም የተባለ አንድ የወልዋሎ ጉብል ሆኖ ተገኘ፡፡ ፓንት ልገዛ ትንሿ ቡቲኩ ሄጄ በተገናኘንበት የመጀመሪያው ቀን እጄን ጨብጦ ሰላም ካለኝ ጀምሮ በማላውቀው ምክንያት አባዬ ሲናፍቀኝ ዋለ። ይሄው እሱም አገባው ዘንድ ይወተውተኛል፡፡ አሁን ድረስ ሲያቅፈኝና ስሜን ሲጠራ ትዝ የሚለኝ አባዬ ነው፡፡  
“ጦቢያዬ የጠየቅኩሽን መልሺልኝ እንጂ”
አራዶም ራስጌውን ተደግፎ አልጋው ላይ ተቀምጧል። በመስኮት ወደ ውጭ አያለሁ፡፡ ባልንጀሮቿ ሁሉ ትተዋት ሄደው ብቻዋን የቀረች ቢራቢሮ የጦቢያ ቅጠሏ ዙሪያ ታንዣብባለች፡፡
ሳልመልስለት በር ከፍቼ ወጣሁ፡፡
ዐጥር ጥግ ያለችውን ተክል ነቅዬ ጣልኳት፡፡

Read 8316 times
More in this category: « ቀዩ ቀበቶ ሱስ »