Sunday, 14 May 2017 00:00

“ፊልም ያለ ማጀቢያ ሙዚቃ ጎደሎ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ሱልጣን ሶፊ፤ በ4ኛው የ”ጉማ ፊልም ሽልማት” ላይ በምርጥ የፊልም ሙዚቃ ስኮር ዘርፍ አሸናፊውን ለመሸለም ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ በወጣ ጊዜ፤‹‹በዚህ ዘርፍ ቢያሸንፍ ደስ የሚለኝ አንድ ትልቅ ሰው አለ፤ይህ ወጣት ትልቅ ባለሙያ ታደለ ፈለቀ ነው›› በማለት ነበር ይህ የጥበብ ሰው እንዲሸለም ያለውን ምኞትና ጉጉት የገለጸው፡፡ ሱልጣን ሶፊ ምኞቱ ተሳክቶለትም ወጣት ታደለ ፈለቀ፣ የዘንድሮው የጉማ ፊልም ሽልማት፣ ምርጥ የሙዚቃ ስኮር ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በሁለተኛውና በሦስተኛው የጉማ ፊልም ሽልማት፣ በዘርፉ እጩ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ወጣቱ ባለሙያ ከ70 በላይ ፊልሞችን የሙዚቃ ስኮር ሰርቷል፡፡ በኮምፒዩተር ሳይንስ ቢኤ ዲግሪ ያገኘው ወጣቱ ሙዚቀኛ፤በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስሚዲያ ተቋም በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስልጠና ወስዶ የምስክር ወረቀትም አግኝቷል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆነው ታደለ፤‹‹ዋቲራ›› በተባለው የግል
ስቱዲዮው የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ ይናገራል፡
   የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ አርቲስቱ እንዴት ወደ ሙያው እንደገባ፣ ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው ስለሚለው የሙዚቃ ስኮር ሙያ፣እንዲሁም ስለ ወደፊት እቅድና ህልሙ እንዲህ አነጋግራዋለች፡፡

      ከሙዚቃ ጋር እንዴት ነው የተዋወቅኸው?
እኔ ተወልጄ ያደግሁት በተለምዶ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተባለው አካባቢ ነው፡፡ ፈረንሳይ አንቺም እንደምታውቂው ብዙ የጥበብ ሰዎች የወጡበት ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም ፈረንሳይ አካባቢ ባሉ ት/ቤቶች ነው የተማርኩት። ሙዚቃን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የኪነ-ጥበብ ስራዎች መሞከር የጀመርኩት በት/ቤቴ ውስጥ ነው።
ሌሎች የኪነ-ጥበብ ስራዎች ስትል ----- ?
ሙዚቃን የጀመርኩት 1ኛ ደረጃ ት/ቤት በሙዚቃ ክፍለ ጊዜ በመዝፈን ነው፤ ነገር ግን ድራማዎችና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች በት/ቤት በማቅረብ ንቁ ተሳትፎ ነበረኝ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለይ የሙዚቃ መሳሪያንና ቅንብርን ራሴን በራሴ እያሰለጠንኩ ነው እዚህ የደረስኩት፡፡
በኮምፒዩተር ሳይንስ ቢኤ ድግሪ እንዳለህ አውቃለሁ፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህ በኋላ በቀጥታ ወደ ዩኒቨርስቲው ነው የገባኸው?
በቀጥታ ወደ ዩኒቨርስቲ አልገባሁም፤ወደ ሙዚቃው ነው የገባሁት፡፡ በመጀመሪያ ከ1ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ መካከለኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስገባ፣ የፊልም ባለሙያው ታላቅ ወንድሜ ዮሐንስ ፈለቀ ለጥበብ የተለየ ፍቅር ስላለው ክራር ወደ ቤት ይዞ ይመጣ ነበር፡፡ እሱ ይህን ሲሞክር ሲሞክር አልመጣለትም፡፡ ያው የሱ ጥሪ ሌላ ስለሆነ ክራሯን ያስቀምጣታል፡፡ እኔ ያቺን ክራር አንስቼ ያለምንም አስተማሪ መለማመድ ጀመርኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አሁን አሜሪካ የሚገኝ ቴዎድሮስ ጂጆ የሚባል ሳክስ ተጫዋች ነበር፤ በእርሱ አማካኝነት ዋሽንት መጫወት ጀመርኩኝ፡፡ የሁለት ባህላዊ መሳሪያዎች ባለሙያ ሆንኩ ማለት ነው፡፡ በ1992 የሀይስኩል ትምህርቴን እንደጨረስኩኝ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚያስገባኝ በቂ ነጥብ ስላልመጣልኝ ፣ ‹‹ፕሮፕራይድ›› የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ለመስራት ገባሁ፡፡
ፕሮፕራይድ ውስጥ በርካታ ሙያዎችን ተምረህ መውጣትህን ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ በድርጅቱ ውስጥ ስለነበረህ ቆይታ አጫውተኝ?
ፕሮፕራይድ በ17 ዓመቴ አካባቢ ወጣት በጎ ፈቃደኛ ሆኜ ነው የገባሁት፡፡ ብዙ ነገር የተቀየረው እዚያ በቆየሁበት ረጅም አመት ነው፡፡ ቤዝ ጊታር፣ ፒያኖ መጫወት፣ ሙዚቃ ማቀናበርና ሌሎች ተጓዳኝ በርካታ ሙያዎችን የተማርኩበት ድርጅት ነው፡፡ እነሱ ስልጠና ይሰጡኝ ነበር፤እኔ ደግሞ ረዥም ጊዜዬን ቢሮ ውስጥ ኢንተርኔት በመጠቀምና በርካታ ለስራዬ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በመፈልፈል  አሳልፍ ነበር። ይህ ጊዜ አንድ ሰው ስራዬ ብሎ ዩኒቨርስቲ ገብቶ፣ ተምሮ ከሚመረቀው በላይ እውቀት ያገኘሁበት ነው፡፡ ቤቱ የተሟላ የሙዚቃ መሳሪያና ባንድ ነበረው፤ ራሴን በራሴ አሳድጌ ሙያዬ ከፍ ሲል የባንድ መሪ ሆኜም አገልግያለሁ። በነገራችን ላይ ፕሮፕራይድ ውስጥ ሙዚቃ ብቻ አልነበረም ስራዬ፤ እዚያው እያለሁ ኮምፒዩተር ሳይንስ መማር ጀምሬ ስለነበር ኮምፒዩተር እጠግናለሁ፣ አካውንታንት ነበርኩኝ፣ ለኤድስ ቀንና ለመሰል በዓላት የሚለበሱ ቲ-ሸርቶች ላይ የህትመት ስራም እሰራ ነበር፤ የህትመት ስራውን እዛው ነው የሰለጠንኩት፤ ግን ትልቅ ሙያ ነው፡፡ ብቻ በዚህ ድርጅት ውስጥ በብዙ እውቀት የመታነፅ እድል ገጥሞኝ ነው የወጣሁት፤ የማልረሳው ባለውለታ ቤት ነው፡፡
ከዚህ ድርጅት እንዴት ወጣህ?
በዚህ ድርጅት ውስጥ ሳለሁ ጥረቴንና ፍላጎቴን የምታውቅና የምታደንቅ አንዲት ነርስ ነበረች፡፡ ሲስተር ውቢት ትባላለች፡፡ ይህቺ ነርስ ከፕሮፕራይድ ወጥታ ‹‹ቁልጭ›› የተሰኘ የህፃናት መርጃ በጎ አድራጎት ድርጅት ከፍታ ነበር፡፡ እኔ 2001 ዓ.ም አካባቢ በኮምፒዩተር ሳይንስ ዲግሪዬን ካገኘሁ በኋላ ፕሮፕራይድ በደረጃም በደሞዝም እንዲያሳድገኝ ጠይቄ ነበር፡፡ ከስድስት ዓመት ቆይታ በኋላ ስመረቅ ነው እድገት የጠየኩት፡፡ በድርጅቱ ውስጥ “ይበቃል” የተባለ ታዋቂ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ድራማ እሰራ ነበር፤ ስቱዲዮው ሲቋቋም እቃ ከመግዛትና ከማደራጀት ጀምሮ ጉልህ ሚና ነበረኝ፤ ለድራማዎቹ ማጀቢያ ሙዚቃ እሰራ ነበር፤ ይሄ ብቻ ሳይሆን የመድረክ ቴአትር ሲኖር ከመድረክ ጀርባ ሆኜ ቴአትሮችን በፒያኖ አጅብ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ እድገት ስጠይቅ የሰጡኝ ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም። ምክንያታቸውን ስላላወቅኩ አሁን ለወቀሳ ሳይሆን ረጅም አመት የሰራሁበትን፣ በሙያም ያደግሁበትን ቤት እንዴት እንደለቀቅኩ ለመናገር ነው፤በወቅቱ በሰጡኝ ምላሽ ስለተከፋሁ መልቀቂያም ሳልወስድ እንደወጣሁ ቀረሁ፡፡
ከዚያስ?
በወቅቱ ሰርጎች ላይ “ከተፋ” የሚባለውን ዓይነት ስራ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ ሰርጎች ላይ ፒያኖ፣ ኪቦርድ እየተጫወትኩ የሚከፈለኝን ብር መቆጠብና ማጠራቀም ያዝኩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ በወቅቱ ውድ የሚባለውን ኪቦርድ ከ20 ሺህ ብር በላይ አውጥቼ ገዛሁ፡፡ ያ ኪቦርድ በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ሰዎች እጅ ላይ ብቻ ነበር የሚገኘው፤ ያንን ኪቦርድ ከገዛሁ በኋላ በአጋጣሚ አንድ ኤግዚቢሽን ላይ ከሲስተር ውቢት ጋር ተገናኘን፡፡ ስራ እንደሌለኝ፣ ከፕሮፕራይድ እንደለቀቅኩና ስራ እንደምፈልግ ስነግራት፣ ጥረቴን ታደንቅ ስለነበር፣ “ሆለታና ዝዋይ ለምን ወጣቶችን አታሰለጥንልኝም” አለችኝ፡፡ ተስማማሁ፡፡ ምክንያቱም ይሄ ለእኔ ትልቅ አጋጣሚ ነበር፡፡ ለስልጠና ስሄድ አበልም ክፍያም ስለነበረኝ፣ ተነሳሽነቴን በጣም አሳደገውና ወጣቶቹን በጥሩ ሁኔታ ማሰልጠን ጀመርኩ፡፡ ከዚህ ስራ የማገኘውንም ገንዘብ ለትልቅ አላማ ማጠራቀም ጀመርኩኝ፡፡ “ሳምራዊው 1 እና 2”፣ “ሄሎ ኢትዮጵያ”፣ “Just for one day” የተሰኙ አጭር ፊልምና በርካታ ፊልሞችን ፅፎ በማዘጋጀት የሚታወቀው ታላቁ ወንድሜ ዮሐንስ ፈለቀ፤ ይህን ፍላጎቴን ያደንቅ ስለነበር፣ የስቱዲዮ እቃዎች ማለትም ኮምፒዩተሮች ሳውንድ ካርዶችና መሰል አስፈላጊ ነገሮችን አሟላልኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በጣም ነው የማመሰግነው፤ ከዚህ በኋላ ነው የኔ ታሪክ የተቀየረው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮፌሽናል ደረጃ ያቀናበርከውን ሙዚቃ ታስታውሰዋለህ?
ለመጀመሪያ ጊዜ የኮሜዲያን ጥላሁን እልፍነህ ታዋቂ ዘፈን የነበረውን “አይ ኮበሌ”ን ነበር ያቀናበርኩት፡፡ በእርግጥ ቅድም እንደነገርኩሽ፣ በፕሮፕራይድ ለድራማ የሚሆኑ ሙዚቃዎችን አቀናብር ነበር፡፡ በዘፈን ደረጃ በጣም ሰው ያወቀውን “አይ ኮበሌ”ን ነው ያቀናበርኩት፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፕራይድ እያለሁ፣ በየከተማው መንገዶች ላይ ይታይ ለነበረ ‹‹አያትዬው›› ለተሰኘ ድራማ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ሙዚቃ ሰርቻለሁ፤ ድራማው ዋሽንት ሁሉ ነበረው፡፡ እነ አርቲስት መኮንን ላዕከ የተወኑበት ነው፡፡ ከዚያ ሜጋ ኪነ-ጥበባት ማዕከል ‹‹የጨረቃ እንባ›› ይመስለኛል ርዕሱ፤ የሚል ድራማ ሰርቶ በመላው አለም ታይቷል፡፡ የመጀመሪያ ክፍሎቹን ማጀቢያ ሰርቻለሁ፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የፊልም አብዮት የተቀጣጠለበት ጊዜ ነበር፤ በዘርፉም ብዙ ባለሙያ አልነበረም (አሁንም በተለይ በፊልም ስኮር ብዙ ሰው የለም) ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጠረልኝ ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአገር ውስጥ የፊልም ስኮር አጭር ስልጠናም የለም፡፡ ሙያውን የምናሳድግበት ምንም መንገድ የለም፡፡ ከኢንተርኔት ላይ ስለ ፊልም የሙዚቃ ስኮር ምንነት ብዙ መረጃ በመሰብሰብና በማንበብ ነው በዘርፉ ስፔሻላይዝ ያደረግሁት፤ በራሴ ጥረት ማለት ነው፡፡
ባለፈው ሰኞ የተመረቀውን ‹‹ማያ›› ፊልምን ጨምሮ እስካሁን ከ70 በላይ ለሚሆኑ ፊልሞች የሙዚቃ ስኮር ሰርተሃል፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን ጥቀስልኝ?
በጣም በርካታ ናቸው፡፡ የማስታውሰውን ልሞክር፡፡ አንቺ ከጠቀስሽው ሰኞ ዕለት ከተመረቀው ‹‹ማያ›› ብጀምር፣ ‹‹አዲናስ››፣ ‹‹በጭስ ተደብቄ››፣ ‹‹ስርሚዜዋ››፣ በጉማ ያሸነፍኩበት ‹‹የነገን አልወልድም››፣ ‹‹ህይወቴ›› የተባለ ትልቅ ፊልም፣ “ባለቀለም ህልሞች”፣ ‹‹አርዲቦ ምዕራፍ ሁለት›› እና በርካታ ትልልቅ በተመልካች የተወደዱ ፊልሞችን ስኮር ሰርቻለሁ፡፡
ዘፈኖችም  ታቀናብራለህ አይደል?
አቀናብራለሁ፤ሰው የሚያውቀኝና ይበልጥ የሚያሰራኝ ግን የፊልም ሙዚቃ ስኮር ነው። በነገራችን ላይ ዋልታ ኢንፎሜሽን ማዕከል፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያስተላልፋቸው የነበሩ ከ40 በላይ ዘጋቢ ፊልሞችን ኦሪጂናል ማጀቢያ ሙዚቃዎች ሰርቻለሁ፡፡ ነፃ በሚባል ደረጃ፣ እጅግ አነስተኛ በሆነ ክፍያ ማለት ነው፡፡ ያውም “ዶክሜንተሪ ስትሰሩ ለምን የውጭ ማጀቢያ ሙዚቃዎችን ትጠቀማላችሁ?” የሚል ጥያቄ አንስቼ፣ ተቀብለውኝ ነው ይህን ሁሉ የሰራሁት፡፡ ከዚያ በፊት የያኒን ሙዚቃዎች ነበር ለማጀቢያነት የሚጠቀሙት፡፡  
‹‹ሞጋቾቹ›› በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የሰራኸው የማጀቢያ ሙዚቃህ ተወዳጅነት አግኝቷል ይባላል-----?
እውነት ነው፡፡ ተከታታይ ረዥም ድራማን በሙዚቃ ሳጅብ የመጀመሪዬ ነው፤ሆኖም አልከበደኝም፡፡ መጀመሪያ የሰባት ክፍሎችን ስክሪፕት ወስጄ ካጠናሁ በኋላ የድራማውን መንፈስ መልዕክት ሊወክል የሚችል ሙዚቃ ሰራሁለት። እስካሁን እየሄዱ ባሉት የድራማው ክፍሎች ሁሉ የኔ ሙዚቃ አለ፡፡ እንደ አጋጣሚ የዚህ ድራማ ሙዚቃ በጣም ተወድዷል፤ ከተለያየ አገር ደውለው አድናቆታቸውን ገልፀውልኛል፤ ከእንግሊዝ ጭምር፡፡ የመግቢያ ሙዚቃውን ብቻ ሰምተው የሚተኙ እንዳሉም ነግረውኛል፡፡ የአገራችን ታዋቂ ዘፋኞች ለምን ዘፈን አንሰራበትም የሚል ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡ ድራማው በአብዛኛው በሆስፒታልና በህክምና ላይ የሚያጠነጥን ስለሆነ ሙዚቃው ሲጀምር የልብ ምት (ቢት) አለው፤ ይሄ ስክሪፕቱን አጥንቼ የሰራሁት ፈጠራ ነው፡፡ በሙዚቃው ውስጥ ክራር፣ ከበሮና ዋሽንት አለበት። ክራሩንም ዋሽንቱንም ራሴ ነኝ የተጫወትኩት። ብዙ ሰዎች ለስልካቸው ጥሪ ሙዚቃውን ተጠቅመውበታል፡፡ ከመግቢያው ውጭ ድራማው ውስጥ ያለውን ሁሉንም ሙዚቃ እየሰራሁ ያለሁት እኔ ነኝ፡፡ የዚህ ድራማ ሙዚቃ፣ ስራዬን በአንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የፊልም ስኮር ሙዚቃ ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው ትላለህ፡፡ እስኪ አብራራልኝ?
ለአፍታ ወደ ኋላ፣ ወደ ልጅነታችን ልመልስሽ፤ ዱሮ በየቤታችን ቪዲዮ ማጫወቻ የለም፡፡ 50 ሳንቲም እየከፈልን ነበር ቪዲዮ ቤት ፊልም የምናየው፤ አንቺም አይተሽ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ እነ ዣን ክላውድ፣ ቫንዳም፣ ቻክ ኖሪስ የሚባሉ ፊልሞች ነበሩ፡፡ ፊልሞቹ በአብዛኛው ከፊልም ስኮር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ እዚያ እድሜ ላይ ሆኜ፣ ድብድብ፣ ጦርነት ወይም ሀዘን የሚታይባቸው ትዕይንቶች ላይ ከኋላ የሚሰሙ ሙዚቃዎች ይስቡኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ ፊልሙ ሲያወሩሽ ዳዳዳ…ፓፓፓ… የሚለውንም በድምፃቸው እያሉ ነው የሚነግሩሽ፡፡ እኔም ይሄ ነገር ምንድን ነው እያልኩ አሰላስል ነበር፡፡ እውነት እነዚህ ፊልሞች ይሄ ሙዚቃ ባያጅባቸው ህይወት ይኖራቸው ነበር ወይ? እያልኩኝ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ በጣም የሚገርምሽ አሁን ላይ ሆኜ ሳጤነው፣ የፊልም ስኮር ሙዚቃ ለፊልም ያለው ድጋፍ ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ያረጋገጥኩት፣ ሰዎች የፊልም ስኮር ሙዚቃ ሊያሰሩኝ ፊልሙን ብቻ ይዘው እኔ ስቱዲዮ ይመጣሉ፡፡ ተቀርፆ ኤዲት ተደርጎ ያለቀለት ፊልም ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ በፊት ፊልሙን ባዶውን ያውቁታል፤ ከዚያ ተስማሚውን ሙዚቃ ሰርቼ ስሰጣቸው፣ ማመን በሚያቅት ሁኔታ የፊልሙ ሁኔታ መቶ በመቶ ይቀየራል፡፡ ሰዎቹ ግርምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ፊልም ያለ ስኮር በብዙ ፐርሰንት ጎደሎ ነው የሚሆነው፡፡ እኔም ይሄ ሲገባኝ፣ ለምን ፊልማችንን የውጭ አገር ሳውንድትራክ እየተጠቀምን፣ ቅኝ እናስገዛዋለን በሚል ቁጭት፣ ትኩረቴን በዚህ ስራ ላይ አድርጌ፣ ለሽልማት በቅቻለሁ፡፡
የእኛ አገር ፊልሞች ሲሰሩ ስኮሮቹ ከውጭ ፊልሞች ነው ኮፒ የሚደረጉት፤ ደግሞም ከአንድ ፊልም አይደለም፡፡ አንድ ስኮሩ ኮፒ የተደረገበት አካል መጥቶ ክሬዲት ስጡን ቢል በጣም ያስቸግራል፡፡ ለምን? ከተለያየ ፊልም ነው ኮፒ የሚደረገው፡፡ ምናልባትም ከ10 እና ከ20 ፊልም ኮፒ የተደረገ ስኮር፣ለአንድ ፊልም ስራ ይውላል፡፡ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ በሌላ በኩል ሳውንድ ትራክ መኖሩ እንጂ የፊልሙን ታሪክና መንፈስ የሚወክል አለመሆኑ አይጤንም፡፡ ይሄ ሌላው ስህተት ነው። ይህ እንዲቀየር፣ የራሳችን ቀለም እንዲኖረንና በራሳችን ኦሪጂናል ሙዚቃ እንድንጠቀም  የግሌን ጥረት እያደረኩ ነው፡፡ ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡
በዚህ ዘርፍ የሌላው ዓለም ተሞክሮ ምን ይመስላል?
በሌላው ዓለም የፊልም ስኮር ትልቅ የሚከበር ሙያ ነው፤ በክፍያም ደረጃ ከፍተኛ ነው፡፡ ስኮር ሲሰራም ስክሪፕቱ ተጠንቶ፣ ዘውጉ ታይቶ፣ በጣም በጥንቃቄና በከፍተኛ በጀት ነው፡፡ ምንም እንኳን የእኛ አገር ፊልም ገና አጭር እድሜ ያለው ቢሆንም ከውጭ ተቦጭቀው የሚመጡት ስኮሮች የሚያበሳጩኝ ለዚህ ነው፡፡ ለምሳሌ ለትልቅ አድቬንቸር ፊልም በመቶና ከዚያ በላይ በሲንፎኒ ታጅበው ለትልቅ ኤቨንት የተሰራን ስኮር እዚህ ያመጡና ልጁ ታሞበት ሆስፒታል ኮሪደር ላይ ለሚራወጥ አንድ አባት ትዕይንት ማጀቢያ ያደርጉታል፡፡ ይሄ በጣም የተሳሳተ ነው፡፡ አንደኛ የፊልሙ መንፈስና ስኮሩ አብሮ አይሄድም፤ በሌላ በኩል ስኮሩ በጣም ለትልቅ ኤቨንት አለያም ለትልቅ አድቬንቸር ፊልም የተሰራ በመሆኑ ያንን ሆስፒታል ኮሪደር ላይ የሚጨነቅን አባት ሲያጅብ ሙዚቃው ይበልጥና ሰውየውን ቁንጫ አሳክሎ ያሳንሰዋል፡፡ አየሽ ሳይንስ ነው የምልሽ ለዚህ ነው። በውጭው አለም ለፊልም ስኮር የሚሰጠው ቦታና የሚያስወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በትንሽ በጀት ፊልም የሚሰሩ ኩባንያዎች እንኳን ለስኮሩ ከፍተኛ ወጪ ነው የሚመድቡት፡፡
አንተ አንድን የሙዚቃ ስኮር ለመስራት ምን ያህል ክፍያ ትጠይቃለህ?
በትንሹ እስከ 30 ሺህ ብር እጠይቃለሁ። ከአገራችን የፊልም እድገት፣ ከፊልም ሰሪዎቹ በጀት አንጻር እንጂ መቶ ሺህ ብር ብጠይቅም በቂ አይደለም፤ ምክንያቱም አድካሚና የራስ ፈጠራን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡
የሙዚቃ ስኮር ሙያን ለማሳደግ ምን ያሰብከው ነገር አለ?
ትልቅ አላማና ራዕይ አለኝ፡፡ እንግዲህ በዘርፉ ስፔሻላይዝድ አድርጌ እየሰራሁ ነው፡፡ ለዚህ ሙያ መስዋዕትነት ከፍያለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በብዙ ፊልም ሰሪዎች ዘንድ ሙያውን እንደ ሙያ ያለመቁጠርና እውቅና ያለመስጠት ችግር አለ፡፡ ነገር ግን ጥቂት ፊልም ሰሪዎች ለሙያው በሰጡት ትኩረትና ዕውቅና፣ አሁን ላይ የተሻለ ዘርፍ ለመሆን በቅቷል። ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ የስልጠና ማዕከልም ሆነ ት/ቤትም የለም፡፡ እኔ ግን እንደ ፈጣሪ ፈቃድ የወሰደውን ጊዜ ወስጄ አንድ የስልጠና ማዕከል በመክፈት፣የተሻሉ የሙዚቃ ስኮር ባለሙያዎችን ለማብዛትና ሙያውን ለማስከበር ጥረት አደርጋለሁ። እኔ አስቤዋለሁ ፈጣሪ ያሳካዋል፡፡ ይህን አምናለሁ፡፡

Read 749 times