Wednesday, 04 April 2012 09:37

ከኢህአዴግ 4 ድርጅቶች በሙስና የሚመራው ይነገረን! የጎረቤት ነዳጅ የራስ ነዳጅ ማለት ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

ጐረቤታችን ኬንያ ሰሞኑን ትልቅ ፌሽታ ላይ ትመስላለች (ፌሽታ ይነሳት!) ለዘመናት ተሰውሮ የኖረ የነዳጅ ዘይት በከርሰ ምድሯ አግኝታለች እኮ! ደግሞ ዝም ብሎ እንዳይመስላችሁ! ኬንያ ውስጥ ተገኝቷል የተባለው ነዳጅ እኮ “ጥቁር አረቦች” ሊያሰኛቸው የሚችል ነው ተብሏል - በማስረጃ ባይደገፍም፡፡ በእውነቱ ይሄን የብልፅግና ዜና ስሰማ፣ ነዳጁ ልክ ጋምቤላ የተገኘ ያህል ነው በደስታ ጮቤ የረገጥኩት፡፡ የጐረቤት ስኬት እኮ የራስ ስኬት ያህል ነው፤ የጐረቤት ደስታ የራስ ደስታ ነው፡፡ የጐረቤት ነዳጅ የራስ ነዳጅ ማለት ነው፡፡ (የምን ጠጋ ጠጋ)!

አይገርማችሁም… ከጥቂት ሳምንት በፊት እኮ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እዚያው ኬንያ ነበሩ፡፡ በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትና የጋራ ወደብ በመገንባት ዙሪያ ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር ሲመክሩ ሲዘክሩ፤ “ችግራችሁ ችግራችን!” ሲሉ ሰንብተው ነው የተመለሱት፡፡ አሁን ደግሞ የኬንያው አቻቸው አዲስ አበባ መጥተው “ነዳጃችን ነዳጃችሁ” እኮ ነው ይሏቸዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ማንም ሊክደው የማይችለውን አንድ ሃቅ ግን ልንገራችሁ - ጠ/ሚኒስትር መለስ እግራቸው እርጥብ ነው፡፡ እንዴት ብትሉ? እሳቸው ኬንያን ረግጠው ሲመለሱ፣ ነዳጅ ተገኘ የተባለው!

እኔማ አንዲት የሞኝ የምትመስል ሃሳብ ይዤ ሳመነዥካት ሰነበትኩላችሁ፡፡ ምን መሰላችሁ? ያው ከኬንያው ነዳጅ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እናም… ምነው ጠ/ሚኒስትሩ እዚያው ኬኒያ ትንሽ በቆዩ ነበር አልኩኝ (ለራሴ!) በቃ እግራቸው ከኬንያ ሳይወጣ የነዳጁ መገኘት የምስራች ቢበሰር፣ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ታሪካዊ ያደርገው ነበር፡፡ ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊም ማድረጉ አይቀርም! (በነዳጅ!)

እኔ የምላችሁ… ፈጣሪ አፍሪካን በቃሽ ሊላት ነው እንዴ? በኡጋንዳም እኮ ነዳጅ ተገኝቷል እየተባለ ነው! ብቻ ይሄ የነዳጅ ወሬ ደስ ይላል!  አያችሁ ነዳጅ እስክናገኝ ነዳጅ ባላቸው አገራት መከበብ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ሃብታም እስክንሆን በሃብታም ጐረቤት መከበባችንም ሃብታምነትን (ጥጋብን) ለመለማመድ ይጠቅመናል እንጂ ሃባ ጉዳት የለውም፡፡

አንድ ሃሳብ ድንገት ብልጭ አለልኝ (አሁን!) ምን መሰላችሁ? አገራችን ውስጥ ነዳጅ ሊኖርባቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎች አሉ አይደል? ለምን ጠ/ሚኒስትሩ በእነዚያ ሥፍራዎች ደጋግመው መለስ ቀለስ አይሉም? (ማን ያውቃል… እንደኬንያው ቢቀናንስ!)

እውነቱን ልንገራችሁ አይደል…የኬንያንና የኡጋንዳን ነዳጅ መገኘት ከሰማሁ በኋላ ድሎት አምሮኛል… በቃ ምቾት! እኛንና ኢህአዴግን የሚያጋጨን የኑሮ ውድነቱ፣ የዋጋ ግሽበቱ፣ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄው ወዘተ የድህነት ውጤት እኮ ነው! በኦጋዴን ወይም በጋምቤላ መጠነኛ ነዳጅ ብናገኝ እኮ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት የሚፈለገው 85ቢ. ብርም አያሳስበንም ነበር፡፡ ድህነትን በአቋራጭ ማሸነፊያው መንገድ ሌላ ሳይሆን ነዳጅ ብቻ ነው! (ነዳጅ ከሌለ ግን ሥራ!) ግን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ ተገኘ ቢባል ስለሙስና አስቦ የማያውቀው ጨዋ ባለስልጣን ሁሉ ዓይኑን ጨፍኖ ሙስና ውስጥ መዘፈቁ ይቀራል ብላችሁ ነው፡፡ እንዴ…አየነው እኮ በመሬት! አየነው እኮ በግብርና በቀረጥ! (ሙስናን እኮ አየነው - ከእግር እስከራሱ!)

እናንተ… ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ዓመት ሞላው እንዴ? (ጊዜው እንዴት ነው የሚከንፈው ባካችሁ!) እርግጠኛ ነኝ “የአርቲስቶች ሠራዊት” እንደኔ ተሸውዶ ነው ከህዳሴው ግድብ በአንድ ዓመት ወደ ኋላ የቀረው፡፡ ዓመት ሙሉ ለህዳሴው ግድብ ምንም የሰራሁት የለም ሲል ሂሱን የዋጠው የአርቲስቶች ሠራዊት፤ የባከነውን አንድ ዓመት እንደሚክስ የአርቲስቶቹ ተወካይ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ሰሞኑን ከሌሎች የመንግስት አካላት ጋር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ (እንደ አፍ አይቀናም አሉ!)

ሌላ አስቸኳይ …በጣም አስቸኳይ ጥያቄ አለኝ!! በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ምንድነው? እንዴ… በዚህ ጉዳይማ ማንም ሊገለል አይገባም!  ኢህአዴግም ቢሆን ይጥራና ያሳትፋቸው እንጂ! (ሌላ አገር አላቸው እንዴ?) አሁን ለምሳሌ የግድቡ ሥራ የተጀመረበት አንደኛ ዓመቱን አስመልክቶ የመንግስት ባለስልጣናትና የዲፕሎማቶች የእግር ኳስ ግጥምያ ይደረግ የለ? የተቃዋሚዎች ቡድንም ለምን አይሳተፍም?

እንደውም ኢህአዴግ ለምን ከ”መድረክ” ጋር አይጋጠምም? መቼም እንደምርጫ፣ በሥነምግባር ኮዱ አልተስማማንም ወይም ምህዳሩ ጠቧል ማለት አይቻልም!  (ስታዲየም እንጂ ምህዳር የለማ!) አያችሁ ለመጪው ምርጫም ጥሩ ተመክሮ ሊሆን ይችላል - ምርጫን በእግር ኳስ መለማመድ!

በዚህ አጋጣሚ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን የእግር ኳስ ክለብ አያቋቁሙም? (በቋሚነት ማለቴ ነው) እንደ ሙገር፣ ባንክ፣ ቡና፣ ጊዮርጊስ ወዘተ ኢዴፓ፣ መድረክ፣ አንድነት… የሚሉ የእግር ኳስ ክለቦች! በፖለቲካ እምቢ ሲል በኳስ ነዋ! (ሥልጣን ግን የለም! ዋንጫ ብቻ ነው!)

እንግዲህ ፈርዶብን ይሁን ረፍዶብን ባይታወቅም አንዳንዴ በእውኑ ህይወታችን “ፖለቲካ በፈገግታ”ን የምናይበት አጋጣሚ አይጠፋም፡፡ የምለው ገብቶአችኋል አይደል! እዚህች አምድ ላይ እኔና እናንተ የምናወጋት “ፖለቲካ በፈገግታ” አንዳንዴ በእውን ብቅ ትላለች እያልኩ ነው፡፡ እኛማ ቀድመን እዚህች ያለ ሊዝ የተሰጠን የወረቀት ማሳ ላይ የምናወጋው ከክፉ ከክፉው ለመጠበቅ ነበር - በአብዛኛው ባይሳካም!!

ባለፈው ሳምንት ከሰማናቸው ለጆሮ የማይጥሙ ዜናዎች አንዱ፣ ከቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ እንዲወጡ የተወሰነባቸው 22ሺ የሚደርሱ የአማራ ክልል ተወላጆች ጉዳይ ነው፡፡ (አንድ እርምጃ ወደ ፊት አራት እርምጃ ወደ ኋላ ይሏል ይሄ ነው!) ስላቅ ስላቅን ይወልዳል እንዲሉ … ከተፈናቃዮቹ መካከል 70 የሚሆኑ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክርስቲያን ሄደው ለመጠለል ቢሞክሩም፣ የቤ/ክርስትያኗ የጥበቃ ሠራተኞች (የጥበቃ ነው የጥበብ?) መጠለል አትችሉም ብለው እንዳባረሯቸው ተዘግቧል፡፡ (8ኛው ሺ ገባ እንዴ?) ከዛስ የት ቢጠለሉ ጥሩ ነው? በአዲስ አበባ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፅህፈት ቤት! ከቤ/ክርስትያን የፓርቲ ፅ/ቤት ተሽሎ ቁጭ አለላችሁ!

ሌላውን ምፀት ደግሞ ልንገራችሁ፡፡ በቅርቡ በኬንያ በተነሳ የጐሳ ግጭት ይመስለኛል… ወደ ኢትዮጵያ ክልል የገቡ ኬንያውያን ስደተኞች ነበሩ፡፡ እንግዳ ተቀባዩ “መንግስታችን” በአገር ወግ ተቀብሎ ማስተናገዱን ኢቴቪ ውብ አድርጐ ነግሮናል፡፡ እኔ የምለው ግን… የውጭ ስደተኛ ካልሆነ አናስጠልልም ማለት ነው?

ደግሞ እኮ የመፈናቀሉ ሰበብ ሌላ ሳይሆን መንግስታዊ ነው ወይም ፖለቲካዊ! ስለዚህ ፈጣን ምላሽ መስጠት ያለበት እሱ ነበር - መንግስት! በእርግጥ ማፈናቀሉን የፈፀሙት የቤንቺ ማጂ ዞን ሃላፊዎች ይመስሉኛል፡፡ ግን እኮ ቤንቺ ማጂ ዞን ያለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የሆነስ ሆነና ግን ከ10-30 ዓመት በቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ ኖረዋል የተባሉትን የአማራ ክልል ተወላጆች፣ ከአካባቢው ውጡ ማለትን ምን አመጣው? ነገርዬዋ ጥሩ ጥሩ አትሸትምና “ሳይቃጠል በቅጠል” ማለት ይሻለዋል - ልማታዊ መንግሥታችን!

ቀጣዩ አጀንዳችን የሙስና ነው (አለቅም አለና!)

ለዚህ ወጋችን የሚሆን መረጃ ያገኘነው ከየት መሰላችሁ? መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም የወጣው “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የዜና አምዱ ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዜና “ኦህዴድ ለሀገሪቱ ዕቅድ ስኬት ጥሪ አቀረበ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፤ የኦሮሞ ህዝብ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ስኬታማነት ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ” ይላል፡፡ (እሱስ ምን ሊሰራ?)

ልብ በሉ! ይሄ ጥሪ የቀረበው ድንገት አይደለም! ከተመሰረተ 22 ዓመት የሞላው ኦህዴድ፤ ሰሞኑን የልደት በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው፡፡ የድርጅቱን የምስረታ በዓል አስታኮ የተዘገበው ዜና ሲቀጥልም፣ የኦህዴድ ምክትል ሊ/መንበር አቶ ሙክታር ከድር ያስተላለፉት መልዕክት ሰፍሯል፡- “የኦሮሞ ህዝብ ከድህነት ለመላቀቅ እያደረገ ያለውን ርብርብ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ እቅድ ስኬታማነት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” (ምክር ነው ትእዛዝ?)

እኔ የምለው ግን… የኦሮሞ ህዝብ በኦህዴድ ሹመኞች እየተመዘበረ እንዴት ብሎ ነው ለትራንስፎርሜሽን እቅዱ የሚረባረበው? እርግጥ ነው… ህዝቡ ኦህዴድ ሳይፈጠርም በፊት ከድህነት ለመላቀቅ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ ችግሩ ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥረቱ በሙሰኞች እየተደነቃቀፈበት ነው፡፡ የሙስና ተዋናዮቹ ደግሞ ከየትም የመጡ ሳይሆኑ ራሱ ኦህዴድ መልምሎ የሾማቸው አባላቱ ናቸው፡፡ (ካልሆነ ይካድ!)

ነገርዬው ሃሜት እንዳይመስልብን መረጃ እናጣቅሳለን፡- “የቡራዩ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ 19 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ” በሚል ርዕስ  በቀረበው ዘገባ፤ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩት የቡራዩ ከተማ ከንቲባና ሌሎች 18 የከተማዋ የሥራ ሃላፊዎች፤ እንዲሁም መሃንዲሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጋዜጣው የኦሮምያ ሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በሻሸመኔ ከተማም ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

የሚገርማችሁ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል የሚበዙት  መሃንዲሶች ናቸው ተብሏል፡፡ (መሃንዲስና ሙስና ኮከባቸው ገጥሟል ልበል!)

እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ ኦህዴድን የመቅጣት የአባትነት (የወላጅነት) ሃላፊነትና ግዴታ የለበትም እንዴ? (ሙሉ ስሙ ኦህዴድ/ኢህአዴግ መስሎኝ!)

እኔ እንደውም አንድ ሃሳብ መጥቶልኛል … ምን መሰላችሁ? ልክ በከተሞች የድህነት ሁኔታ ላይ ጥናት ተደርጐ የድህነት ቅነሳ ደረጃቸው ይፋ እንደተደረገ ሁሉ የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች ውስጥ ያለው የሙስና “ጥልቀት” እና “ምጥቀት” በቅጡ ተጠንቶ ደረጃቸው ለህዝቡ እንዲነገረው እንጠይቃለን (የህዝቡን ገንዘብ ዘረፉት እኮ!)

በአሁኑ ጊዜ ሙስና በጣም የተንሰራፋው የት ነው? በህወሃት ወይስ በብአዴን? በደህዴግ ወይስ በኦህዴድ? ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይሄን አስጠንቶ (ራሱም ቢሆን አጥንቶ) ደረጃ ማውጣት ያቅተዋል ብዬ አላስብም፡፡ ካስፈለገም የዓለም ባንክ ስፖንሰርሺፕን መጠየቅ ይቻላል፡፡

አንድ ወዳጄ ምክንያቱን አልነገረኝም እንጂ የዓለም ባንክ፣ የኢህአዴግ ዓለማቀፍ ሊግ ሆኗል ብሎ ሲፎትት ነበር (የሚያውቀው ነገር ቢኖር ነው!)

እናላችሁ… ያለዚያ እኮ የሙስና ነገር አስፈሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሙሰኞች እየተፈለፈሉ የሚያድሩ እኮ ነው የሚመስለው፡፡

አዲስ ዘመን እንደዘገበው፤ ባለፉት ስምንት ወራት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ መንግስት ገቢ ተመላሽ ተደርጓል (በሙስና ተዘርፎ የነበረ ማለት ነው)፣ በሰበታ 6ሺ 400 ካ.ሜ መሬት ታግዷል፡፡ በአዳማ ከተማ ከ11ሚ.ብር በላይ የሆነ በጫት ቀረጥ ማጭበርበር የተገነባ ባለ 3 ፎቅ ህንፃ ተመልሷል፡፡ (ገና ያልተመለሰውንና ሳይመለስ የሚቀረውን ፈጣሪ ይወቀው!)

 

 

Read 3217 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 10:01