Sunday, 14 May 2017 00:00

‹‹አሪፍ ዘፈን››፤ የኢንተርኔት አልበም ሽያጭ በቴዲ አፍሮ ዘፈን ጀመረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 መሰረቱን በአሜሪካ አገር ካሊፎርኒያ ከተማ ውስጥ ያደረገና በአራት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተቋቋመው ‹‹አሪፍ ዘፈን›› የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ የኢንተርኔት አልበም ሽያጭ በቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው የማርኬቲንግና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሪት ምዕራፍ ክፍሌ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸችው፤ ኩባንያቸው  በአይነቱ አዲስ የሆነውን ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት፣ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በማሰብ ወደ ሥራው ገብተናል ብላለች፡፡ ኩባንያው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባደረገው የሥራ ስምምነት መሰረት፣ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ደንበኞች ከስልካቸው ሂሳብ ላይ ተቆራጭ በማድረግ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መጀመሩን ወ/ሪት ምዕራፍ ተናግራለች፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፤ ከገቢው 40 በመቶ የሚሆነው ለኢትዮ ቴሌኮም የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ ሲሆን ከቀሪው 60 በመቶ ላይ ቫትና የሾርት ኮድ ክፍያ ተቀናሽ ሆኖ ቀሪው ለባለመብቱ አርቲስት ተከፋይ ይሆናል፡፡ የአልበሙን ሽያጭ አርቲስቱ እራሱ በኢንተርኔት የሚከታተል ሲሆን የተሸጠውን ዘፈን መጠን፣ የተሸጠበትን ጊዜና ሰዓት ሁሉ በቀጥታ መከታተል የሚያስችል መሆኑ አሰራሩን ተመራጭ ያደርገዋል ብላለች፡፡  የአሰራር ሲስተሙ ደንበኛው በግዥ ያገኘውን ዘፈን ለሌላ 3ኛ ወገን ለማስተላለፍ እንዳይችል በሚያግድ መልኩ የተበጀ ሲሆን ይህም የቅጂ መብትን በማስከበሩ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብላለች፡፡ ለተጠቃሚውም ከአንድ አልበም ላይ የሚፈልገውን ሙዚቃ ብቻ መርጦ ለመግዛት የሚያስችል ከመሆኑ ባሻገር የሚፈልጋቸው ዘፈኖች በአንድ ቦታ ላይ (ጥቅል ውስጥ) ተሰባስበው መቀመጣቸው ለአጠቃቀም ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር ተመራጭ ያደርገዋል ስትል አስረድታለች፡፡  
በአዲሱ የቴዲ አፍሮ አልበም ወደ ሥራ የገባው አዲሱ “አሪፍ ዘፈን” አፕሊኬሽን፤ የቅጅ መብትን በማስጠበቅና አድማጭም ጥራት ያለውን ትክክለኛ ክፍያ የተፈፀመበትን የሙዚቃ ሥራ መጠቀም እንዲችል የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለሙዚቃ ኢንዱስትሪ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑን ወ/ሪት ምዕራፍ ገልፃለች፡፡ በቀጣይም ከሌሎች ድምፃውያን ጋር ስምምነቶችን በመፈፀም ዘፈኖቻቸውን በኢንተርኔት ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ሃላፊዋ አስታውቃለች፡፡

Read 2465 times