Sunday, 14 May 2017 00:00

ኦልማርት የጥያቄና መልስ ውድድር አዘጋጀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ከ6 ዓመታት በፊት የተመሰረተውና በሱፐር ማርኬት ስራ ላይ የተሰማራው ኦልማርት፤ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ 20 የመሰናዶ ት/ቤቶች የ12 ክፍል ተማሪዎች የሚሳተፉበት የጥያቄና መልስ ውድድር አዘጋጀ፡፡ ኦልማርት ማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት ‹‹Excellence on Education›› በሚል ያዘጋጀው ይህ ውድድር፤ በተለይ በሂሳብና እንግሊዝኛ ትምህርቶች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡ ከ20 የመንግስት መሰናዶ ት/ቤቶች በድምሩ 6530 ተማሪዎች ባለፈው ሚያዚያ 26 ቀን 2009 ለፈተና መቀመጣቸውን የገለፀው ኦልማርት፤ ከነዚህ ውስጥ ከየት/ቤቱ ምርጥ 5 ተማሪዎች በድምሩ 100 ተማሪዎች ለመጨረሻው ውድድር እንደሚያልፉ አስታውቋል፡፡ ኦልማርት ከቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ውድድሩን ያዘጋጀ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው ጥያቄ በማውጣት፣ በመፈተንና ማርክ በመስራት ከፍተኛ ሙያዊ ተሳትፎ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
ኦልማርት ይህንን ውድድር በመንግስት መሰናዶ ት/ቤቶች መካከል ያደረገበትን ምክንያት ሲገልፅ፤ በአብዛኛው በመንግስት ት/ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ህልማቸውንና ሀሳባቸውን የሚያንፀባርቁበት መድረክ ስለማያገኙ ያንን ክፍተት ለመሙላትና ወቅቱ የዋናው ፈተና ወቅት በመሆኑ ተማሪዎቹን ይበልጥ ለማዘጋጀት እንዲረዳቸው በማሰብ ነው ብሏል፡፡ ከ1-10 የሚወጡ ተማሪዎች ከ15 እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብና ለትምህርት የሚረዳቸው ቁሳቁስ እንደሚሸለሙም ታውቋል፡፡ ኦልማርት ሱፐር ማርኬት ከዚህ ቀደም የህፃናትን ልዩ ተሰጥኦ የሚያወጣ የህፃናትና ታዳጊዎች የሙዚቃ አይዶል አዘጋጅቶ አሸናፊዎችን መሸለሙ የሚታወስ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ውድድር በመጪው ክረምት እንደሚካሄድ ጠቁሞ፤ የጥያቄና መልስ ውድድሩም በቋሚነት በየአመቱ ይቀጥላል ብሏል፡፡

Read 867 times