Sunday, 14 May 2017 00:00

የዘንድሮው የአዳማ የቴአትር ፌስቲቫል ተቋረጠ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዳማ ከተማ የተካሄደው የቴአትር ፌስቲቫል ዘንድሮ በተመልካች እጦት መቋረጡን የተስፋ ቴአትር ኢንተርፕራይዝ ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ወርቁ ገለፁ። ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ሁለት ፌስቲቫሎች ከ25 በላይ ትልልቅ ቴአትሮችን በድምቀት ማሳየታቸውን የገለፁት አቶ ተፈራ፤ ዘንድሮ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ፕሮሞሽንና ዝግጅት ፌስቲቫሉ ባለፈው ረቡዕ ቢጀመርም በመክፈቻው ለእይታ የቀረበው ‹‹ፍቅርን የተራበ›› ቴአትር 92 ተመልካች ብቻ ማግኘቱና ‹‹የዳዊት እንዚራ›› የተሰኘውን ቴአትር ለመመልከት 110 ሰው ብቻ መግባቱ ተስፋ ስላስቆረጣቸው ፌስቲቫሉን አቋርጠው በነጋታው ሐሙስ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ገልፀዋል፡፡ በመክፈቻው ቀን በእያንዳንዱ ቴአትር ከ700 በላይ ተመልካች፣ በሁለተኛውና በሶስተኛው ቀን ደግሞ እንደሌላው ጊዜ ለእያንዳንዱ ቴአትር ከ1500-2000 ተመልካች ይገባል ብለው መጠበቃቸውን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የተመልካቹ ትያትር ለማየት ያለው መነሳሳት በእጅጉ መቀነሱ ከፍተኛ ውይይት እንደሚያስፈልገው መገንዘባቸውን የገለፁት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ቴአትር ለማየት ትኬት ገዝተው የነበሩ ሰዎች እንኳን የተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ትኩረታቸውን አድርገው እንደነበር መታዘባቸውን አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ “ፍቅር የተራበ”፣ “የዳዊት እንዚራ”፣ “አብሮ አደግ”፣ “እንግዳ”፣ “ባቢሎን በሳሎን” እና “እድል” የተሰኙ ቴአትሮችን በፌስቲቫሉ ለማሳየት አስፈላጊውን ቅድመ ክፍያ ለቴአትር ቤቶቹ ከፍለው መውሰዳቸውን የገለፁት አቶ ተፈራ፤ በወጪ በኩል ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ቢገቡም ከገንዘቡ በላይ የወደፊት የቴአትር እጣ ፋንታ እንዳስደነገጣቸው ጠቁመው በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላትና የዘርፉ ባለሙያዎች ጋር  ውይይት ለማዘጋጀት ማሰባቸውንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 1602 times