Sunday, 14 May 2017 00:00

“መርሃችን ቅድምያ ለሰራተኞች ነው”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ሆቴሉ ዛሬ ይመረቃል
     ዕድለኛ ብቻ ስለሆኑ አይደለም፤ “አትሙት ያላት ነፍስ” ስለያዙ ነው በወቅቱ ከተከሰተው ከፍተኛ አደጋ ከመቅፅበት አምልጠው ለዛሬ ደስታ የበቁት፡፡
የዛሬ 6 ዓመት የሆቴል ግንባታውን አሐዱ ብለው ሲጀምሩ ከባድ ችግር አጋጥሟቸው ነበር፡፡ የግንባታው ቦታ ሲቆፈር 8 ሜትር ያህል ወደ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በቴሌና በመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ ከባድ ዝናብ ጥሎ አካባቢውን ኃይለኛ ጎርፍ አጥለቅልቆት ነበር፡፡ የቴሌ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ከተመለከቱ በኋላ “ይኼ ጉድጓድ ተደርምሶ ቢሆን ኖሮ ከባድ ጉዳት ያስከትልብህ ነበር፤ ዕድለኛ ነህ” ብለው አፅናንተውት ሄዱ፡፡
እሳቸውና የጥበቃ ሰራተኛው፣ ጎርፍ፣ ወደተቆፈረው ጉድጓድ ገብቶ ውሃ እንዳይሞላውና እንዳይደረምሰው ድንጋይ እየደረደሩ፣ ላስቲክ እያነጠፉ፣ … ይከላከሉ ነበር፡፡ በሌላውም ጠርዝ ተመሳሳይ የመከላከል ተግባር ለማከናወን እግራቸውን ካነሱ ከሁለት ወይም ከሦስት ሴኮንዶች በኋላ ቆመውበት የነበረው ስፍራ አፈር ተንዶና ተደርምሶ ወደ ውስጥ ገባ፡፡
ታዲያ ይኼ “ትረፍ ያለው ነፍስ” ይዘው ነው አያሰኝም? ነው እንጂ! ለ6 ዓመት ከግንባታው ስፍራ ሳይለዩ፤ እያንዳንዱን ሥራ እየተከታተሉ፣ አንድም ሰው ጉዳት ሳይደርስበት፣ ሥራው ተጠናቅቆ ዛሬ “ሳፋሪ” አዲስ ሆቴል ሲመረቅ፣ በሆቴሉ ባለቤት ለአቶ ፍሥሐ አባይ ፊት ላይ የታየው የደስታ ስሜት የሚገርም ነው፡፡
አቶ ፍስሐ አባይ ከአክሱም ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ዞራት በተባለች ቀበሌ ነው የተወለዱት። እዚያው በተወለዱበት አካባቢ ከብቶች እያገዱና ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ ከቆዩ በኋላ 13 ዓመት ሲሆናቸው፣ አጎታቸውና የእናታቸው ወንድም ከሆኑት ከጣና ወርቅ ቤት ባለቤት ከአቶ ዓለማየሁ ኪ/ማርያም ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡
በወርቅ ቤቱ መስራት የጀመሩት ወዲያው ነበር። እዚያ እየሰሩ የወርቅ ጌጣጌጦችን አሰራርና ንግድ በሚገባ ተማሩ፡፡ በጣና ወርቅ ቤት ከ10 ዓመት በላይ ሰሩ፡፡ አሁን የወርቅ ጌጣጌጦች አሰራርና ንግዱን በሚገባ ለምደውታል፡፡ ስለዚህ የራሴን ወርቅ ቤት ከፍቼ ለምን አልሰራም? የሚል ሀሳብ መጣላቸው፡፡ ሐሳቡንም ለአጎታቸው ለአቶ ዓለማየሁ ኪ/ማርያም አማከሩ፡፡ አጎትዬውም፣ “እኔ ድሮውንም የምፈልገው የአንተን ሰው መሆን ነው፡፡ እኔም እደግፍሀለሁ፤ በሐሳብህ ቀጥልበት” ብለው አቶ ፍስሐ በነበራቸው 100 ሺህ ብር ላይ 500 ሺህ ብር ጨምረውበት አንበሳ ወርቅ ቤት በ 1984 ዓ.ም ተከፈተ፡፡
አቶ ፍስሐ በግላቸው 20፣ ከአጎታቸው ጋር 10 ዓመት በጠቅላላው 30 ዓመት በወርቅ ሥራ ሙያ ከቆዩና ሙያውንም በሚገባ ከተካኑ በኋላ የሥራ ዘርፍ ለውጥ አደረጉ፡፡ ያኔ እንደ አሁኑ በአገሪቷ ብዙ ሆቴሎች አልነበሩም፡፡ መንግሥትም በሆቴል ግንባታ ለሚሰማሩ ሰዎች ድጋፍ አደርጋለሁ እያለ ይገፋፋ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ፍስሐ “ሆቴል ብገነባ አትራፊ እሆናለሁ” በማለት የቀድሞ ስራቸውን ሳይተው፣ ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪው እንደገቡ ይናገራሉ፡፡
ሆቴሉ እጅግ ዘመናዊ መሆኑን የገለጹት የሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ም/ፕሬዚዳንት፣ የሆቴሉ ልዩ አማካሪና አደራጅ አቶ ዜናዊ መስፍን፣ የሆቴሉ ደረጃ ባለ 5 ኮከብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የምንጠብቀውን ደረጃ ባያሟላ እንኳ፣ ቀደም ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ ሆቴሎች ደረጃ ከሰጡ መዳቢዎች ጋር ስለሰራሁ፣ ለእያንዳንዱ ኮከብ የሚጠየቀውን መስፈርት አውቀዋለሁ፡፡ ስለዚህ መስፈርቱን አሟልተን፣ ሆቴላችንን ባለ 5 ኮከብ እንደምናደርገው እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡
ዘመናዊ ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ የእንግዶች ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት ነው። በክፍሎቹ ውስጥ ወይም በኮሪደሮች ላይ ጭስ ቢከሰት ጠቋሚ መሳሪያ ተገጥሞላቸዋል፡፡ እንግዶች እንደተኙ ክፍል ውስጥ የእሳት አደጋ ቢከሰት፣ ምንጣፍና በሮቹ እሳቱን እስከ 4 ሰዓት የመቋቋም አቅም አላቸውና፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ እንግዳው ነቅቶ ከእሳቱ ሊያመልጥ ይችላል፡፡
ሌላው ሆቴሉን ከሌሎች የተለየ የሚያደርገው ነገር ለሰራተኞቻቸው የሚሰጡት ክብር ነው፡፡ “Happy employee makes happy customers” የሚል ፍልስፍና ነው የሚከተሉት፡፡ ለዚህም መርሐቸው ቅድሚያ ለእንግዳ (ካስተመር ፈርስት) ሳይሆን፣ ቅድሚያ ለሰራተኞች (ኢምፕሎይ ፈርስት) የሚል ነው፡፡ የዚህ መርሕ ማጠንጠኛ በራሱ ደስተኛ ያልሆነ ሰራተኛ እንግዶችን በጥሩ ፈገግታ አያስተናግድም የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ለሰራተኞቻቸው ጥሩ ደሞዝ ይከፍላሉ፣ የደረጃ ዕድገት ይሰጣሉ፤ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲያገኙ ይደረጋል፤ የሥራ ላይና ከውጭ አገር የሆቴል ባለሙያ እየመጣ ሥልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፤ ልዩ አማካሪው፡፡ ሠራተኛው በሚደረግለት እንክብካቤ መርካት ያለመርካቱን፣ ምን እንደሚያስፈልገው፣ የጎደለውን ነገር … ስሙን ሳይጽፍ አስተያየቱን እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡
የሆቴሉ የምግብ አብሳይ (ሼፍ) የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የምግቡ አቀራረብ ፍላፒ የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ ይህም ማለት፣ የሚሠራው ምግብ ትኩስና የሚፈልገው መሆኑን ለእንግዳው አሳይተህ እያየው እፊቱ የሚዘጋጅ ነው፡፡
ሌላው ልዩ የሚያደርገን ነገር የሜዲቴራኒያን አካባቢ (ሜዲቴራኒያን ፉድ) የምናዘጋጅ መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ምግብ የሚዘጋጀው እኛ ጋ ብቻ ስለሆነ የሜዲቴራኒያ አካባቢ ምግቦች የሚፈልግ ሰው እኛ ጋ መጥቶ ይስተናገዳል ማለት ነው። ባህላዊና የውጭ አገር ምግቦችም እናዘጋጃለን በማለት አቶ ዜናዊ አብራርተዋል፡፡
የተለያዩ የማርኬቲንግ (የገበያ መሳቢያ) ስትራቴጂዎችም መቅረጻቸውን አቶ ዜናዊ ይናገራሉ። ይኸውም ሙያዎችን በሳምንት በሳምንቱ ከፍለዋል። ማለትም አንዱ ሳምንት በከተማዋ የሚገኙ ስፖርተኞች ተገኝተው እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፣ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚወያዩበት፣ ኔትዎርክ የሚፈጥሩበት ይሆናል፡፡ የሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ በሕክምና ተቋማት የሚሠሩ ሐኪሞች፣ ነርሶች፣ ላቦራቶሪ ቴክኒሻኖች፣ ጤና ረዳቶች … ተገኝተው በጋራ ችግሮቻቸው ላይ የሚነጋገሩበት፣ የመልካም ተሞክሮ ውጤቶችን የሚለዋወጡበት፣ የእርስ በርስ ትስስር የሚፈጥሩበት ይሆናል፡፡ የሕግ ባለሙያዎች፣ የነጋዴዎች፣ የመምህራን፣ … የዲፕሎማት … ሳምንት እያለ እንደሚቀጥል ልዩ አማካሪው አስረድተዋል፡፡
ሆቴሉ የሚመራበት የራሱ ፖሊሲ አለው። የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ማናጀሮች ማንም የማይገባበት የራሳቸው ቼክ ሊስት አላቸው፡፡ በዚያ መመሪያ ከጧት እስከ ማታ፣ ከምሽት እስከ ንጋት ምን መስራት እንዳለበት ይመራዋል፡፡ በዚያ ቼክ ሊስት ሰራተኛውንም ያርመዋል፣ ይቆጣጠረዋል። እያንዳንዱ ሲስተም በሦስት የተከፈለ ነው፡፡ 1ኛ የድርጅቱ አጠቃላይ መዋቅር (ኦርጋኒዜሽን ስትራክቸር) 2ኛ የሥራ ኃላፊነት (ጆብ ዲስክሪብሽን) 3ኛ ፖሊሲ አለው፡፡ እንዲህ የተደረገው ባለቤት ወይም ሰው ጣልቃ የሚገባበትን ዕድል ለማጥፋት በሲስተም እንዲመራ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የሆቴሉ ክፍሎች ሰፋፊ ከመሆናቸውም በላይ እያንዳንዳቸው በረንዳ (ባልኮኒ) አላቸው፡፡ 64 ክፍሎች ደሉክስ የሚባሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ክፍሎች ፍሪጅ፣ ሻይ ቡና ማፍያ፣ ውድ ዕቃዎች ማስቀመጫ ካዝና፣ ሚዛን፣ ቲቪ፣ ስልክ፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ መጻፊያ ጠረጴዛ፣ ሻወር፣ ጋዋን፣ ሻምፑ፣ ኮንዲሽነር፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ ፎጣ፣ የልብስ መተኮሻ ካውያ ከነጠረጴዛው፣ … ያላቸው ክፍሎች ዋጋ 70 ዶላር ነው፡፡ ፋሚሉ ሩም የሚባት ሁለት ክፍሎች ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መጥተው የሚስተናገዱባቸው ናቸው፡፡ ወላጆች አንዱ ክፍል ውስጥ ሲሆኑ፣ ሁለት አልጋዎች ባሉት ሌላው ክፍል ልጆች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች ቤተሰብ ባልመጣ ጊዜ መኻላቸው ተዘግቶ እንደ ሁለት ክፍል ያገለግላሉ፡፡፡ ሁለቱም ታዲያ የራሳቸው ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ ጠረጴዛና ወንበር …. አላቸው፡፡
ትልልቆቹ “ሱት ሩም” የሚባሉት 26 ክፍሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍሎች መኝታ ክፍልና የእንግዶች ማረፊያ ሳሎን አላቸው፡፡ ሰፋፊ ከመሆናቸውም በላይ ሳሎኑ 7 ሰዎች ማስቀመጥ የሚችል ሶፋ፣ ቲቪ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ፍሪጅ፣ አለው፡፡ መኝታ ቤቱም ቲቪ፣ ፍሪጅ፣ ካዝና፣ ሻይ ቡና ማፍያ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ መታጠቢያ ክፍሉ ውስጥ ጃኩዚ … አለው። በሌሎች ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ እዚህም አሉ፡፡ ዋጋው 90 ዶላር ነው፡፡      
ሆቴሉን ዘመናዊ ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ ላውንደሪው ነው፡፡ ይህ ላውንደሪ ትልቅ ከመሆኑም በላይ ራሱ አጥቦ ራሱ አድርቆ በራሱ የሚተኩስ ነው።

Read 789 times