Print this page
Sunday, 14 May 2017 00:00

“ሰው ከሠራና ከጣረ የፈለገበት እንደሚደርስ እኔ ማስረጃ ነኝ”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

እርሻቸውን ውሃ የሚያጠጡት ከወንዝ በሞተር ውሃ እየሳቡ በመስኖ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የሚሳበው ውሃ ቢሠሩት ቢያደርጉት እየሰረገ በመስኖው ውስጥ አልገባ (አላልፍ) አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ባለቤትየው የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ግራ ገባቸው፡፡ በመጨረሻ አንድ ዘዴ ብልጭ አለላቸው፣ በመላ ሰውነታቸው መስኖው ቦይ ውስጥ ተጋድመውና አፈር ለብሰው ውሃውን በላያቸው ላይ ማሳለፍ፡፡
እንዳሰቡት አድርገው ውሃው በላያቸው ላይ እያለፈ ሲሄድ፣ ቀስ ብለው አፈሩን አራግፈው ተነሱ። በዚህ ዓይነት ከፍተኛ ጥረት በእርሻ ውጤታማ የሆኑት ገበሬ፤ በአዳማ (ናዝሬት) ከተማ ደንበል ቪው ኢንተርናሽናል የተባለ ባለ 3 ኮከብ ሆቴል ገንብተው፣ የዛሬ ሳምንት አስመርቀዋል፡፡
አቶ ዳዲ ጃራ ኩምቢ፤ በምሥራቅ ሸዋ ዞን በዱግዳ ወረዳ፣ ሾኒ ቀበሌ ማህበር በ1964 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ያደጉት መቂ ከተማ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 10ኛ ክፍልም የተማሩት እዚያው ባደጉበት ከተማ ካቶሊክ ት/ቤት ነው፡፡ 11ኛ እና 12ኛ ክፍልን ወደ አሰላ ተጉዘው፣ ጭላሎ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሩ፡፡
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤታቸው ጥሩ አልነበረም፡፡ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያስገባቸው አልነበረም፡፡ ስለዚህ ሾፌርነት ጀመሩ፡፡ ሹፍርናውን እየሰሩ ጎን ለጎን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እርሻ ጀመሩ፡፡ እርሻ የጀመሩት 5 ሺህ ብር በማይሞላ አነስተኛ ገንዘብ፣ ሰኔ 1 ቀን 1988 ዓ.ም  ነበር። መጀመሪያ የተከሉት ፓፓያ ነበር፡፡ ከዚያም ቲማቲምና ሽንኩርት ማምረት ቀጠሉ፡፡ የእርሻው ስራ ጥሩ እየሆነ ውጤት ማሳየት ሲጀምር፣ ትራክተር ገዝተው በመስኖ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ይኼው ዛሬም ድረስ ለ20 ዓመት ያህል ገበሬ ናቸው፡፡ ለሆቴሉ የፓፓያ ጭማቂ የሚሰራው ከእርሻው በሚመጣው ፓፓያ ነው፡፡ አንድ ሄክታር የነበረው እርሻ፣ መሬት በኮንትራት ከሰዎች እየወሰዱ፣ ከ25 እስከ 40 ሄክታር እንደሚያርሱ አቶ ዳዲ ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳዲ ‹‹ሆቴል እሠራለሁ›› የሚል ሐሳብ እንኳን በእውናቸው በሕልማቸውም አልነበረም። የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት፣ ወደ ሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚገባ ሰው ከቀረጥ ነፃ ዕድል እንደሚሰጥና ሌሎች ድጋፎችም ይደረግላቸዋል በማለት ይቀሰቅሱ ነበር፡፡ ቅስቀሳው ብቻ አልነበረም። በእርሻ ሥራ ውጤታማ ስለነበሩ ገንዘቡም ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ‹‹እስቲ ይኼን ነገር ልሞክረው›› ብለው ገቡበት፡፡
አዳማ መጥተው 1,132 ካሬ ሜትር ቦታ በ450 ሺህ ብር ገዙ፡፡ ሆቴሉ ያረፈው በ731 ካ.ሜ ላይ ነው፡፡ የደንበል ቪው ኢንተርናሽናል ሆቴል ግንባታ ፕሮጀክት የተጀመረው ከ10 ዓመት በፊት ነበር፡፡ ሆቴሉ 55 ዘመናዊ ክፍሎች አሉት፡፡ 7ቱ ክፍሎች፣ እንግዳው የራሱን ምግብ ማዘጋጀት ቢፈልግ የማዕድ ቤት (ኪችን) ዕቃዎች የተሟሉላቸው (ፈርኒሽድ ሱትስ) ናቸው፡፡ ሁለቱ ክፍሎች ደግሞ ባለ 2 አልጋ  የቤተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ 21ዱ  ክፍሎች ደሉክስ ስታንደርድ፣ 13 ሲንግል ስታንዳርድና 12 ሲንግል ናቸው፡፡ ክፍሎቹ፣ አንድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ባለ ኮከብ ሆቴል ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች የያዘ እንደሆነ፣ ሆቴሉን ለባለ 4 ኮከብ ደረጃ እያደራጀ ያለው አቶ ሲራክ ገልጿል፡፡
ሆቴሉ ከ30 እስከ 300 ሰዎች የመያዝ አቅም ያላቸው 4 አዳራሾች፣ አንድ ባርና አንድ ሬስቶራንት አሉት፡፡ በሆቴሉ ያደሩ እንግዶች ነፃ ቁርስና ነፃ ዋይፋይ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ክፍሎቹ፣ ቲቪ፣ ስልክ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ ፍሪጅ፣ ውድ ንብረቶቻቸውን በራሳቸው ኮድ የሚቆልፉባቸው ካዝና፣ መጸዳጃና ሻወር፣ ሻይና ቡና ማፍያ ጀበና፣ የሆቴሉ ስም የተጻፈበት ፎጣ፣ ሻምቦ፣ ኮንዲሽነር፣ ፀጉር ማድረቂያ፣ …አላቸው፡፡
የሆቴሉ ግንባታ እስከ አሁን ድረስ 65 ሚሊዮን ብር ፈጅቷል፡፡ አሁንም በግንባታ ሥራ ላይ ስለሆነ ወጪው እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ ሆቴሉ ለ72 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ባለሀብቱ ተናግረዋል። የሆቴሉ ስም ደንበል ቪው የተባለው ያደጉበትን አካባቢ ለማስታወስ ነው፡፡ ‹‹ደንበል›› ማለት ሞገድ ወይም ዌቭ ማለት እንደሆነ አባታቸው እንደነገሯቸው አቶ ዳዲ ገልፀውልኛል፡፡ ቪው ደግሞ በእንግሊዝኛ እይታ ሲሆን ‹‹የሞገድ እይታ›› እንደማለት ይሆናል፡፡
አቶ ዳዲ መልዕክት አላቸው፡- ‹‹አንድ ሰው ሲሠራ በርካታ ችግሮች ያጋጥሙታል፤ በአጭር ጊዜ ለምን ስኬት ላይ አልደረስኩም ብሎ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ ስኬት የከፍተኛ ጥረትና ድካም ውጤት ስለሆነ ወደ ኋላ ነው የሚመጣው። ሁልጊዜ ለሚገጥሙት መሰናክሎች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ቁርጠኝነትና ቆራጥነት ካለህ አንድ ቀን የተሳካላቸው ሰዎች ከደረሱት ደረጃ መድረስህ አይቀርም። እኔ እዚህ የደረስኩት ብዙ መሰናክሎችን አሳልፌ ነው። የሰው ልጅ ጠንክሮ ከሠራና ከጣረ፣ ችግሮችን በተስፋና በትዕግሥት ካሳለፈ፣ ከፈለገበት እንደሚደርስ እኔ ጥሩ ምሳሌ ነኝ›› ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ግንባታ 10 ዓመት የፈጀው፣ ቀደም ሲል የሆቴሉ ክፍሎች መብራት፣ መጸዳጃው፣ መታጠቢያው፣ የፍሳሽ መውረጃው፣… ባለ ኮከብ ደረጃ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ሊያሟላቸው የሚገቡትን መስፈርቶች ባለሟማላታቸው ነው። አሁን ያሉበትን ደረጃ ለመያዝ ክፍሎቹ ፈርሰው እንደገና ነው የተሠሩት፡፡ ክፍሎቹ 50 ከመቶ ፈርሰው ስለተሰሩ ነው ረዥም ጊዜ የወሰደሰው ይላል - ሆቴሉን ባለ 4 ኮከብ አድርጎ ለማስረከብ የተዋዋለው የውስጥ ውበት (ኢንቲርየር ዲዛይነር) ባለሙያ አቶ ሲራክ አምባው፡፡
‹‹አንድ የምንጠብቀው ማስፋፊያ አለ፤ እሱ ከተሳካ ባለ 4 ኮከብ ይሆናል፡፡ ካልተሳካ ደግሞ አሁን ባለበት ደረጃ ባለ 3 ኮከብ ሆኖ ይቀጥላል›› ብሏል - አቶ ሲራክ፤ ‹‹ሆቴል መገንባት የሚፈልጉ ሰዎች ስትራክቸራል አርክቴክትና ከፊኒሽንግ ኮንስትራክተር ዲዛይነር ጋር አንድ ላይ ተቀምጠው ባለ ስንት ኮከብ ሆቴል መገንባት እንደሚፈልጉ መነጋገር አለባቸው… ከዚያ በኋላ ግንባታው ሲሰራ፣ የኢንተርናሽናል ሆቴል ደረጃ እንዲኖረው ቁመቱ፣ የክፍል ስፋቱ፣ ቀለሙ…. በአጠቃላይ ስትራክቸራል ዲዛይኑ ይሠራል፡፡ ይህንን እንኳ ማድረግ ባይችሉ፣ ከባለሙያ ጋር ሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ሆቴሎችን ቢያዩ ጥሩ ነው፡፡›› በማለት የውበት ዲዛይነሩ አስረድቷል፡፡

Read 2504 times