Sunday, 14 May 2017 00:00

በኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የሚሰራ የግል ዘርፍ የለም ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ከደርባ ሲሚንቶ በስተቀር ከግሉ ዘርፍ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድር ወስዶ የሚሰራ ድርጅት እንደሌለ የተገለፀ ሲሆን፣ ባንኩ ከግል ኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ም/ፕሬዚዳንት፤ የግል፣ የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ ሚ/ር ፒየር ጉስሌይን፣ በኢትዮጵያ ለ3 ቀን ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ባለፈው ማክሰኞ በራዲሰን ብሉ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ከኢንዱስትሪና ከንግድ ሚኒስትሮች ጋር፣ እንዲሁም የግል ዘርፉን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሚ/ር ጉስሌይን፤ ድርጅታቸው በ2001 ዓ.ም ለደርባ ሲሚንቶ 55 ሚሊዮን ዶላር ያበደረ ብቸኛው የግል ባንክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደርባን ሲሚንቶን ሲጎበኙ፣ ጥራት ባለው እንቅስቃሴውና ለአህጉሩ የኢኮኖሚ ዕድገት በሲሚንቶ አቅርቦት እያደረገ ባለው አስተዋጽኦ መርካታቸውን ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የግል ኢንቨስተሮች ከባንኩ ጋር የማይሰሩትና የማይበደሩት፣ ባንኩ፣ ለግሉ ዘርፍ እንደሚያበድር ግንዛቤው ስለሌላቸው እንደሆነ ጠቅሰው፣ “በተለይ በኤክስፖርት ዘርፍ ከተሰማሩ የግል ኢንቨስተሮች ጋር ለመስራት ገንዘብ አዘጋጅተን እየተጠባበቅን ነው፤ ኑ አብረን እንሥራ!” በማለት ጋብዘዋል፡፡
ም/ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ስላደረጉት ጉብኝት በሰጡት መግለጫ፣ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ዓለም አቀፍ የምርት ፍላጎት መቀነስና የሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ቢያጋጥማትም፣ ኢትዮጵያ ጠንካራና እውነተኛ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት ስላሳየች፣ የትራንስፎርሜሽን እቅዷን ታሳካ ዘንድ ባንኩ፣ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
“ባንኩ፣ ለአፍሪካ ያለው አመለካከት፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው አምስት ስትራቴጂዎች ይጠቃለላል” ያሉት ሚ/ር ጉስሌይን፣ “እነሱም፣ አፍሪካን የመብራትና የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ፣ አፍሪካን መመገብ፣ አፍሪካን በኢንዱስትሪ ማበልጸግ፣ አፍሪካን አንድ ማድረግና የአፍሪካን ህዝብ ኑሮ ጥራት ማሻሻል ነው” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስራት የጀመረው ከ42 ዓመት በፊት በ1975 ሲሆን እስከ አሁን ወጪያቸው በአጠቃላይ 4.6 ቢሊዮን ዶላር የሆነ 130 ፕሮጀክቶች (በመሰረተ ልማት፣ በኃይል፣ በውሃና ሳኒቴሽን) በማህበራዊ፣ በእርሻና በግሉ ዘርፍ ተከናውነዋል፡፡ ባንኩ፣ በአሁኑ ወቅት በ2 ቢሊዮን ዶላር 26 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
ባንኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ተሳትፎ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ም/ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያና ጅቡቲን ለሚያገናኘው ስትራቴጂያዊ የኃይል አቅርቦት፣ ኢትዮጵያ - ኬንያን ለሚያገናኘው የመንገድ ፕሮጀክት፣ ለገጠር የኤሌክትሪክ አቅርቦትና መቀሌን ከዳሎል ለሚያገናኘው የኃይል ማሰራጫ መስመር፣ ባንኩ፣ 900 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉን ተናግረዋል። እንዲሁም ባንኩ፣ የምስራቅ አፍሪካን የኃይል ፕሮጀክት እየደገፈ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት፣ የገጠርና የከተማ ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የማዕድን ማዕከላት ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማስቻል፣ አፍሪካን ብርሃናማ ማድረግና ለአፍሪካ ኃይል (ፓወር አፍሪካ) ቅድሚያ መስጠት ይሆናል ተብሏል፡፡
አፍሪካን አንድ ማድረግ ወይም ማስተሳሰር በሚለው የባንኩ ስትራቴጂ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ አገራዊና አኅጉራዉ ትስስርን ለመፍጠር ለምሳሌ የኢትዮ - ኬንያ ትራንስፖርት ኮሪደር ፕሮጀክት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦሌን አለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ ደረጃ ለማሳደግ፣ ለበርካታ መንገዶች መገንቢያና ማደሻ፣ ባንኩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉ ታውቋል፡፡
የእርሻውን ዘርፍ ለመደገፍና ለማዘመን፣ 7, 000 ሄክታር የሚሸፍነውንና 77 ሚሊዮን ኪዩቢክ የመያዝ አቅም ያለውን የካጋ መስኖ ፕሮጀክት፣ በእርሻው ዘርፍ ዝናብ ላይ የሚታየውን ጥገኝነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ባንኩ ለኢትዮጵያ 630 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል። እንዲሁም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ አቅም ለማጎልበት በተለይም በሲሚንቶ ምርትና በማዕድን ዘርፍ 160 ሚሊዮን ዶላር በብድር ተሰጥቷል፡፡ እንዲሁም ባንኩ፣ ለውሃ አቅርቦትና ለሳኒቴሽን 340 ሚሊዮን ዶላር፣ ለበጀት ድጎማ፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት፣ ለትምህርት፣ ጤናና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻልና ለመደገፍ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጉ ተገልጿል፡፡ 

Read 1866 times