Saturday, 13 May 2017 12:31

ከቡሽ እስከ ትራምፕ - የአነጋጋሪው ኮሚ አነጋጋሪ መጨረሻ…

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 ባለፈው ማክሰኞ…
ከወደ ዋይት ሃውስ አንድ አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ዜና ወጣ…
አነጋጋሪው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ባወጡት መግለጫ፣ ከጆርጅ ደብሊው ቡሽ እስከ ክሊንተን፣ ከኦባማ እስከ ትራምፕ የአገዛዝ ዘመናት በአነጋጋሪነት የዘለቁትን ታዋቂውን የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚን ከስራ ገበታቸው ማባረራቸውን አስታወቁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2013 በያኔው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ተመልምለው ኤፍቢአይን ለአስር አመታት በዳይሬክተርነት ሊመሩ የተመረጡት የ56 አመቱ ሪፐብሊካን ጄምስ ኮሚ፣ ገና ሶስት አመት ከመንፈቅ ብቻ እንደሰሩ፣ ባለፈው ማክሰኞ ባልተጠበቀው የትራምፕ ውሳኔ ታላቁን ተቋም ከመምራት ታገዱ፡፡
የትራምፕ አስተዳደር የኤፍቢአይ ዳይሬክተሩን ጄምስ ኮሚ ከስራ ለማባረር የወሰነው፣ በሄላሪ ክሊንተን የኢሜይል ቅሌት ዙሪያ ኤፍቢአይ ያከናወነውን ምርመራ በፊታውራሪነት የመሩት ሰውዬው፣ ምርመራውን በሚያከናውኑበት ወቅት በርካታ ስህተቶች መፈጸማቸውንና ብቁ አለመሆናቸውን በማረጋገጡ እንደሆነ አስታውቋል። ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ድንገት ብቅ ብለው ባወጡትና በወቅቱ ከተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር እልህ አስጨራሽ የፍጻሜ ፍልሚያ ላይ የነበሩትን ሄላሪ ክሊንተንን የማሸነፍ ዕድል የከፋ አደጋ ላይ የጣለ በተባለው የዳግም የኢሜይል የቅሌት ምርመራ ውሳኔ ብዙዎችን አስደንግጠው ነበር - አነጋጋሪው ኮሚ፡፡
ሄላሪን አደጋ ላይ የጣለውን ይህን አደገኛ ውሳኔ ለመላው አለም ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ፣ ጠላቴን ድባቅ መታልኝ ያሏቸውን ጄምስ ኮሚን፣ ለፍትህ የቆመ ጀግና ሲሉ በአደባባይ አሞካሽተዋቸው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ከወራት በኋላ ታዲያ፣ እነሆ ባለፈው ማክሰኞ ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሆነው ብቅ አሉና፣ ያሞካሹትን ሰው መልሰው ለማዋረድና ለመወረፍ ደፈሩ- “ታላቁን ተቋም በቅጡ የመምራት ብቃት የሌለው ሰው ነው!... በአፋጣኝ ስራውን ይለቅ ዘንድ ፈርደንበታል!” በማለት፡፡
ጄምስ ኮሚ ከዳይሬክተርነታቸው መነሳታቸው በይፋ መነገሩን ተከትሎ፣ ዶናልድ ትራምፕ አስደንጋጩን ውሳኔ ለማሳለፍ ያነሳሳቸውን ሰበብና የውሳኔውን ስረ መሰረት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችና ትንተናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎች ውሳኔውን የሚያያይዙት ደግሞ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ወቅት ሩስያ ጣልቃ በመግባት ትራምፕን አግዛለች የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ኤፍቢአይ የጀመረውን ምርመራ የሚመሩት ጄምስ ኮሚ ከመሆናቸው ጋር ነው፡፡
ብዙዎች እንደሚሉት፤ ትራምፕ በኮሚ ላይ ውሳኔውን ያሳለፉት፣ በምርመራው ሂደት እኔን ሊጎዱ የሚችሉ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ ይችላሉ ከሚል ስጋት በመነጨ ነው፡፡
ጄምስ ኮሚ ኤፍቢአይን በዳይሬክተርነት በመሩባቸው አመታት፣ የተሸናፊዋን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የሄላሪ ክሊንተንን የኢሜይል ቅሌት ጨምሮ ቁልፍ የተባሉ የምርመራ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን፣ ሰውዬው በሚይዟቸው አቋሞችና በሚያስተላልፏቸው አወዛጋቢ ውሳኔዎች በአንዳንዶች ብቁ መሪ በሚል ቢሞገሱም፣ ብልጣብልጥ በሚል የሚተቿቸውም አያሌ ናቸው፡፡
የሰውዬውን አወዛጋቢነት ከፍ ካደረጉት ሁነቶች መካከል አንዱ፣ ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ወሳኝ ምዕራፍ ሰሞን የሰሩት አነጋጋሪና አደገኛ የተባለ ያልተጠበቀ ድርጊት ነው። ሄላሪ ከትራምፕ ጋር በእልህ አስጨራሽ የምርጫ ፉክክር ውስጥ አልፈው ወደመጨረሻው ምዕራፍ በተሸጋገሩበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ነበር፣ ጄምስ ኮሚ ድንገት ብቅ ብለው አነጋጋሪውን ውሳኔ ይፋ ያደረጉት፡፡
ኤፍቢአይ በሄላሪ ክሊንተን የኢሜይል አጠቃቀም ዙሪያ የጀመረውን ምርመራ ማስረጃ ስላልቀረበበት መዝጋቱን በሃምሌ ወር በይፋ ያስታወቁት ኮሚ፣ ሄላሪ ከትራምፕ ጋር ትንቅንቅ ላይ በነበሩበትና አንደኛቸው የሌላኛቸውን የቆየ ስህተትና የከረመ ድብቅ ጉድ እየፈለፈሉ በአደባባይ በማሳጣትና ደጋፊ በማሳጣት በተጠመዱበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ብቅ ብለው፣ በሄላሪ የኢሜል ቅሌት ዙሪያ ጀምረን ትተነው የነበረውን ምርመራ እንደገና ከፍተነዋል አሉ፡፡
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክሩ በተጧጧፈበትና ቀጣዩ የአሜሪካ መሪ ማን ይሆን የሚለው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ የ11 ቀናት ዕድሜ ብቻ በቀረበት በዚያ ወሳኝ ወቅት ይፋ የተደረገው ድንገተኛው የኮሚ መግለጫ፣ ሄላሪንና ደጋፊዎቿን በድንጋጤ ክው ሲያደርግ፣ ትራምፕንና ደጋፊዎቹን አስፈነጠዘ። ጄምስ ኮሚ በወሳኝ ወቅት ላይ አጉል ሴራ ይዘው ከተፍ ያሉ መሰሪ ተብለው በሄላሪ ሰዎች ሲብጠለጠሉ፣ በትራምፕ ሰዎች ደግሞ ለእውነት ተሟጋች ድንቅ ባለሙያ ተብለው ተወደሱ፡፡
የኮሚ አነጋጋሪነት የሚጀምረው የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን በነበሩበት በጆርጅ ደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን ነው፡፡ በወቅቱ ከኤሌክትሮኒክ ቁጥጥር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ የሚያራምዱት አቋምና የሚያስተላልፉት ውሳኔ ብዙዎችን ያስገርም እንደነበር ይነገራል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንና በሞኒካ ሊዊንስኪ ቅሌት ውስጥም የጄምስ ኮሚ ስም አብሮ ሲነሳ የሚኖር የአገሪቱ አነጋጋሪ የቅሌት ታሪክ አካል ነው፡፡
ጄምስ ኮሚ ባለፈው ረቡዕ ለኤፍቢአይ በጻፉት የስንብት ደብዳቤ፣ ትራምፕ ለምን ይህን ውሳኔ አስተላለፉብኝ የሚለውን ጉዳይ በማጣራት የማጠፋው ጊዜ አይኖረኝም ብለዋል፡፡

Read 1454 times