Monday, 15 May 2017 00:00

በሜዲትራኒያን ባህር የጀልባ አደጋ 250 ስደተኞች ሞቱ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሆኑ ስደተኞችን አሳፍረው ከሊቢያ በመነሳት በሜዲትራኒያን ባህር ወደ አውሮፓ በመጓዝ ላይ በነበሩ ሁለት ጀልባዎች ላይ ሰሞኑን በደረሱ አደጋዎች በድምሩ 250 ያህል ስደተኞች መሞታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ጀልባዎቹ ከመጫን አቅማቸው በላይ በርካታ ስደተኞችን አሳፍረው በመጓዝ ላይ ሳሉ ባለፈው እሁድና ሰኞ ከሊቢያ አቅራቢያ በሚገኙ የሜዲትራኒያን ባህር አካባቢዎች የመስጠም አደጋ እንዳጋጠማቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው እሁድ ከሊቢያ አቅራቢያ አደጋ በደረሰባት ጀልባ 163 ያህል ስደተኞች መሞታቸውን የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ገልጧል፡፡
የተወሰኑ ስደተኞች ከአደጋዎቹ ተርፈው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት አፍሪካውያን ስደተኞች መካከል ህጻናት እንደሚገኙበትና የሴት ስደተኞች ቁጥርም በርካታ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ1 ሺህ 300 በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ከሊቢያ በመነሳት ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት በአስቸጋሪ የጀልባ ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ6 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደተለያዩ የአውሮፓ አገራት መጓዛቸውን አስረድቷል፡፡
ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ወደ አውሮፓ የተጓዙ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር ከ43 ሺህ በላይ መድረሱንም የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

Read 2321 times