Tuesday, 16 May 2017 00:00

“ሙጋቤ አይናቸው ገርበብ ይላል እንጂ፣ ስብሰባ ላይ አይተኙም!”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በተለያዩ ብሄራዊ፣ አህጉራዊና አለማቀፍ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲያንቀላፉ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚያሰራጩና በታላቁ መሪያችን ላይ የሚያላግጡ ሰዎች ተሳስተዋል፣ ሙጋቤ በስብሰባዎች ላይ አይናቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ በጭራሽ አይተኙም ሲሉ የፕሬዝዳንቱ ቃል አቀባይ አስተባብለዋል፡፡
“ታላቁ መሪያችን አይኖቻቸው የብርሃን ጨረሮችን የመቋቋም አቅም ስለሌላቸው በተደጋጋሚ አይኖቻቸውን ገርበብ ስለሚያደርጉና ጎንበስ ስለሚሉ ያንቀላፉ ይመስላሉ እንጂ፣ ብዙዎች በማህበራዊ ድረገጾች እንደሚያብጠለጥሏቸው ስብሰባቸውን አቋርጠው አያንቀላፉም” ሲሉ የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ፣ ሄራልድ ለተባለው የአገሪቱ መንግስት ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡ እርጅና ተጫጭኗቸው አቅም ቢከዳቸውም በቀጣዩ አመት በሚካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ታጥቀው መነሳታቸውንና ስልጣናቸውን እንደዋዛ ለማንም እንማያስረክቡ ያስታወቁት የ93 አመቱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፤ ሰሞኑን ለአይን ህክምና ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሙጋቤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ እና የአረብ-አፍሪካ ጉባኤን ጨምሮ በበርካታ አህጉራዊና አለማቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ እንቅልፍ ወስዷቸው የሚያሳዩ አስቂኝ ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ምስሎች በተለያዩ ድረገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡

Read 1981 times