Sunday, 14 May 2017 00:00

50% እርግዝና ያልታቀደ ነው...

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች አገሮች ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ አልተለመደም። ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት የሚቆጠረው ደግሞ ቅድመ እርግዝና ምርመራ ሊደረግ ይገባዋል የሚለው እውቀት በብዙዎች ዘንድ አለመኖሩ ነው።
                ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ የ
                ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት
      ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና መምህር ለዚህ እትም እንግዳ ናቸው። እሳቸው እንዳሉትም ሴቶች እርግዝናን ሲያስቡ አስቀድመው ሊዘጋጁባቸው  ከሚገባቸው ነገሮች መካከል ዋናው የጤና ጉዳይ ነው። አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት ሙሉ የጤና ምርመራ ብታደርግ እጅግ በጣም ጥሩ እርምጃ ይሆናል። ነገር ግን ይህንን የሚያደርጉት እናቶች በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በአደጉት አገሮች ጭምር በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከዚህም ምክንያቶች አንዱ ከ50% በላይ እርግዝ ናዎች ሳይታቀዱ የሚከሰቱ መሆኑ ነው። ለእርግዝና እቅድ ሳይያዝለት የሚከሰት ሲሆን ደግሞ ምንም አይነት ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ መሆኑ እሙን ነው። በጤናው ፣በማህበ ራዊው ፣በኢኮኖሚው ጭምር ከእርግዝና ቀጥሎ ምን ሊደረግ ነው? የሚለው እርግዝና መኖሩ ከታወቀ በሁዋላ የሚደረግ ምክክር መሆኑ የተለመደ ነው። ነገር ግን ይህ በከፊል እናቶች በሰላም የእርግዝና ጊዜያቸውን ጨርሰው እንዲወልዱ ሲችሉ ብዙዎች ደግሞ የተለያዩ ችግሮች እንዲገጥማቸው ያደርጋል።
ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረገጽ እንደሚያመለክተው ከእርግዝና በፊት የጤና ምርመራ ማካሄድ ለሚወለደው ልጅ ከመወለዱ በፊትና ከተወለደ በኋላም ለሚኖረው ጤናማ የሆነ ሕይወት እጅግ ጠቃሚ ነው። እርግዝናው ከተፈጠረ በሁዋላ የተለያዩ የጤና ችግሮች መኖራቸው ቢታወቅ ከጽንሱ ጋር በተያያዘ የእናትየውንም ሕይወት ውስብስብ ችግር ላይ ይጥላል።
ጤናን በተመለከተ ለእናትየው የሚደረገው ቅድመ ምርመራ እና ለሴትየዋ ከሚደረግላት ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
ሴትየዋ እርግዝናውን ሙሉ በሙሉ ጤነኛ ሆና እስከመጨረሻው ድረስ በሰላም ትደርሳለች ወይ የሚለውን አስቀድሞ ለማወቅ ይረዳል።
እርግዝና ሲመጣ ቀድሞ የነበሩ የጤና ጉዳዮች ካሉ እነዚያን ሕመሞች ተቆጣጥሮና አስተካክሎ ለእናትየውም ሆነ ለጽንሱ ችግር እንዳይገጥማቸው ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ይረዳል።
ቅድመ እርግዝና ባሉ ሕመሞች ምክንያት የሚወሰዱ መድሀኒቶች ከእርግዝናው ጋር አብረው መቀጠል የማይችሉ ከሆነ እነዚያን መድሀኒቶች ለማስተካከል ይረዳል። ብለዋል ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ።
ብዙ ጊዜ እርግዝና ለምን ሳይታቀድ ይከሰታል የሚል ጥያቄ ሲነሳ በተለይም ባልና ሚስት ከሆኑ መቼም ይምጣ መቼ ...ትዳር የመሰረትነው ልጅ ለመውለድ ስለሆነ ስጋት የለብንም ሊሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ጋብቻ የፈጸሙ ሰዎች ሁሉ መውለድ አለባቸው ከሚል ድምዳሜ የሚደረስበት ሁኔታም ይታያል። አንዳንዶች በተለይም በኢትዮጵያ ማርገዝ ልቻል አልቻል ሳላውቅ ምርመራ ምን ያደርጋል የሚባልበት ሁኔታም ይስተዋላል። እንዲያውም አንዳንዶች እርግዝናው ገፍቶ እስኪታወቅ ድረስ ወደሐኪም ቤት መሔድ የማይፈልጉም አሉ። ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም እንደ ዶ/ር ድልአየሁ። ስለዚህ ሳያቅዱ መውለድ ባይለመድ እና ከእርግዝና በፊት ቅድመ እርግዝና ማድረግ ተገቢ መሆኑን ቢያውቁ ሁሉም ሴቶች ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ ሳያደርጉ ማርገዝን አይደግፉም።
የተለያዩ ሕመሞች እርግዝናን ከዳር አድርሶ ልጅ ለመቀበል ሳያበቁ ወይ ጽንሱ እንዲቋረጥ አለዚያም በእናትየው ሕይወት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህም ቅድመ እርግዝና የህክምና ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው የህመም አይነቶች የሚከተሉት የተወሰኑት ናቸው።
የስኩዋር ሕመም፡-
አንዲት እናት ከማርገዝዋ በፊት የስኩዋር ሕመም ካለባት እና ስኩዋሩ በጥሩ ቁጥጥር ላይ ባለበት ሁኔታ ካላረገዘች የሚያመጣው ተጽእኖ አስከፊ ነው። ከስኩዋሩ ጋር በተገናኛ ጽንሱ ላይ ሊከሰት የሚችለው የአፈጣጠር ጉዳቶች ሁሉ አስቀድሞውኑ ቁጥጥርና ክትትል ከተደረገ ይቀንሳል።
ደም ግፊት፡-
አንዲት እናት የደም ግፊትዋ ጥሩ ቁጥጥር ላይ እያለ ካረገዘች ጽንሱም ላይ ሆነ እራስዋ ላይ ችግር የመፈጠሩ አጋጣሚ በጣም ይቀንሳል። አንዳንድ የደም ግፊት መድሀኒቶች በእርግዝና ጊዜ የማይመከሩ ሲሆን እነዚህ መድሀኒቶች በተለይም የመጀመሪያዎች የእርግዝና ሳምንታት ላይ ጽንሱ ላይ ችግር ያመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ ቀድማ ለምርመራ ከቀረበች ግን ሁኔታዎች ሊስተካከሉ ይችላሉ።
የደም መርጋት፡-
የደም መርጋት ችግር ያለባቸው እናቶች ከሚወስዱዋቸው መድሀኒቶች ውስጥ የተወሰኑት በተለይም የመጀመሪዎች የእርግዝና ወራት ላይ ባይወሰዱ ይመከራል። ይህንን በአስፈላጊ መድሀኒት ለመለወጥ መወሰን የሚቻለው ግን እናትየው ቅድመ እርግዝና ምርመራ ለማድረግ ወደሆስፒታል ከሄደች ነው።
ቅድመ እርግዝና ምርመራ ማድረግ ተገቢ የሚሆንባቸው ሌሎችም ብዙ ሕመሞችና የሚወሰዱ መድሀኒቶች አሉ። ለምሳሌም እንደልብ ሕመም ያሉት የእናትየውንም ሕይወት አስጊ ሁኔታ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም የታወቁ እና ከፍተኛ የህክምና ክትትል የሚደረግባቸው ሕመሞች ያሉአት ሴት እነዚህ ሕመሞች ያሉበት ደረጃ ስለመስተካከላቸው የሐኪም የይሁንታ መልስ እስኪያገኙ ድረስ እርግዝናው እንዳይከሰት ለማድረግ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት ሁኔታም ይኖራል።
ዌብ ሜድ የተሰኘው ድረገጽ እንደሚገልጸው ቅድመ እርግዝና የጤና ምርመራ በሚደረግበት ወቅት እናቶች ለሐኪማቸው ሊመልሱት የሚገባ የተለያየ ጥያቄ ይነሳል።
ከስነተዋልዶ ጤና ጋር የተያያዘ ጥያቄ፡-
የመጀመሪያው ከወር አበባ ጋር የተያያዘ ነው። ለመሆኑ የወር አበባ መቼ እንደሚመጣ የምታውቅበት ቀን መቁጠሪያ አዘጋጅታለች?
ስትጠቀም የነበረው የእርግዝና መከላከያ አይነት ምንድነው?
ከአሁን ቀደም በግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት የሚተላለፍ በሽታ ታማ ታውቃለች?ወይንስ? የሚሉትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት አለባቸው።
ከእርግዝና ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ፡-
ከዚህ በፊት የነበረው እርግዝና በምን ሁኔታ ተቋጨ? ተወልዶአል አልተወለደም? ውርጃ ነበረ? ...ወዘተ
ከዚህ በፊት ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና ጊዜ ፣ከወሊድ በሁዋላ ተፈጥሮ የነበረ የመንፈስ ጭንቀት አለ?ወይንስ?
ከዚህ በፊት የተወለደ ልጅ ካለ የጤናው ጉዳይ ምን ይመስላል? የጤና እክል አለ?ወይንስ?
የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። እነዚህ ችግሮች ትክክለኛውን መልስ ካገኙ በድጋሚ እንዳፈጠሩ ጥረት ይደረጋል።
የጤና ሁኔታ ጥያቄዎች፡-
በጤና ጉዳይ የሚነሱ ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። ነገር ግን ዋና ዋናዎቹ አስም ፣የደም ግፊት ፣ስኩዋር ፣የልብ ሕመም ፣የደም መርጋት የመሳሰሉት ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም የተደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ካሉ እና ከማደንዘዣ ጋር የተገናኘ አለመስማማት ከነበረ አስቀድሞ መታወቅ አለበት።
ሕክምና በሚደረግበት ወቅት ከሚሰጡ መድሀኒቶች አለመስማማት መኖር አለመኖሩም መረጋገጥ ይገባዋል። ከአሁን ቀደም ከምትወስዳቸው መድሀኒቶች ውስጥ የትኞቹ አለመስማማት ወይንም አለርጂክ እንደፈጠረባት ታውቆ ወደእርግዝናው ከመግባትዋ በፊት የሚስማማት መድሀኒት ካልተለወጠላት ወይንም መጠኑ ዝቅ ወይንም ከፍ ማለት የሚገባውም ከሆነ አስቀድሞ ካልተስተካከለ ለጽንሱ አስጊ ሊሆን ይችላል።
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎች ጥያቄዎችን ከእርግዝና በፊት ለሐኪሙ ማስረዳት የእናትየውንም ሆነ የጽንሱን ሕይወትና ሙሉ ጤነኛነት ለማረጋገጥ ያስችላል።

Read 2412 times