Sunday, 14 May 2017 00:00

“የፍትህ ስርአቱን ችግር የሚያጠና ገለልተኛ ኮሚሽን በአስቸኳይ መቋቋም አለበት”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

· የህግ የበላይነት ከሌለ ዘመናዊ መንግሥት አይገነባም
            · የዳኝነት ተቋም ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት
            · ፍትህ ሊያገኝ ወደ ፍ/ቤት የመጣ ሰው ሊንገላታ አይገባም
               አቶ ሞላ ዘገየ (የህግ ባለሙያ)

       የህግ የበላይነት ሲባል ምን ማለት ነው? በኛ ሃገርስ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ወይም እየተረጋገጠ ነው ለማለት የሚያስችል ደረጃ ላይ ተደርሷል?
የህግ የበላይነት ማለት በኔ እምነት በአንድ ሃገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ከህግ በታች መሆናቸውንና በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመላክት ፅንሠ ሀሳብ ነው። ይሄን ስርአት መገንባት ዜጎች በሃይለኞች በተለይ ከምንም በላይ ሃይል ባለው መንግስት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሠጣል፡፡ ያለ ህግ የበላይነት  ዘመናዊ  የመንግስት ስርአት አይገነባም። የህግ የበላይነት ከሌለ ዘመናዊ መንግስት የለም፡፡ በየትኛውም ሃገር መንግስት በህግ ካልተገደበ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ የፈላጭ ቆራጭ ምንጩም ይሄው ነው። ስለዚህ የህግ የበላይነት ማለት ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡
የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ደግሞ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አንዱ ፍ/ቤት ነው፣ ከፍ/ቤት ጋር ደግሞ አቃቤቢ ህግ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ ጠበቆች እንዲሁም ሚዲያ መኖር አለባቸው፡፡ ፍ/ቤት በህገ መንግስቱ የተደነገገ ነፃነት አለው፡፡ አሁን ጥያቄው በእርግጥስ በተግባር ነፃነቱ ተከብሯል ወይ የሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ህገ መንግስቱ መሬት ላይ ወርዷል ወይ? በኔ እምነት ይሄ አልተተገበረም፡፡
ይሄን በምሳሌዎች ሊያብራሩት ይችላሉ?
በሚገባ! ለምሣሌ እስከ ዛሬ ዳኞች እንዴት ነው የሚመለመሉት? የዳኞች አመላመልና አሿሿም ግልፅነት ይጎድለዋል፡፡ ሊሆን ይገባዋል ብዬ የማምነው አንድ ዳኛ የሚሆን ሰው መመልመል ያለበት በግል ነው፡፡ ለዳኝነት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች በግልፅ ወጥተው እነዚህ መለኪያዎች በአደባባይ በሚዲያ ጭምር ማስታወቂያ ወጥቶ፣ እነዚህን መለኪያዎች አሟላለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ አመልክቶ፣ በየደረጃው ተጣርቶ፣ መመዘኛውን የሚያሟሉ ጥቂቶች ብቻ ተመርጠው፣ አግባብ ባለው አካል አማካኝነት ለፓርላማ ቀርበው መሾም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡
ለምሳሌ አንድ እጩ በተማረበት ት/ቤት፣ በሚኖርበት ሰፈር በግልፅ ፎቶግራፉ ተለጥፎ፣ ዜጎች በሰውየው ላይ አስተያየት መስጠት አለባቸው፡፡ ዜጎች በግልፅ በሰውየው ላይ ባህሪውን፣ አስተዳደጉን፣ ስነምግባሩን በተመለከተ አስተያየታቸውን ሊሠጡ ይችላሉ፡፡
በዚህ መንገድ መመልመሉ ሰውየው ላይ ህዝብ እምነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ሌላው የእድሜ ጉዳይ ነው፡፡ ዳኝነት ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡ በከፍተኛ ፍ/ቤት የሚሾም ሰው ከማንም የፖለቲካ ስልጣን የተለየ ከባድ ሃላፊነት ነው ያለበት፡፡ ከማንኛውም ባለስልጣን በተለየ የመጨረሻውን ፍርድ የሚሠጥ ዳኛ፣ የሞት ፍርድና ንብረትን የሚያሳጣ ፍርድ የሚወስን ዳኛን እንዲህ በቀላሉ መመደብ አይገባም። ባህሪ፣ እድሜ፣ የስራ ልምድ ተደማምረው ነው ዳኛ መሾም ያለበት፡፡ አሁን ባለው አሠራር ይሄን ልምድ አላይም፡፡ ግልፅ አይደለም፡፡
የእድሜ ጉዳይ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው?
ለምሳሌ በ20ዎቹ ውስጥ ያለን ሰው በዳኝነት አስቀምጦ፣ የትዳር ጉዳይ እንዲዳኝ ቢቀርብለት እንዴት ነው የሚዳኘው? ምን ልምድ አለው? አላገባም! አያውቀውም፤ እንዴት ነው ነገሮችን የሚገነዘበውና የሚያመዛዝነው? ይሄን ስል ስለ ትዳር ለመወሠን ሁሉም ዳኛ ማግባት አለበት ማለቴ አይደለም፡፡ እድሜ ለማመዛዘን ወሣኝነት አለው፡፡ እድሜ የልምድ ጥርቅም ነው፡፡
ሌላው አንድ አዲስ ወጣት ዳኛ፤ መጀመሪያ በረዳት ዳኝነት መስራት አለበት፡፡ ይሄን ስል አንዳንድ ከእድሜያቸው በላይ የበሠሉ ወጣት ዳኞች የሉም ማለቴ አይደለም፡፡ በኔ እምነት አንድ ሠው በዳኝነት መንበር ላይ ተቀምጦ ውሣኔ ለመስጠት፣ እድሜው ከ30 አመት በታች መሆን የለበትም ባይ ነኝ፡፡ 30 ዓመት የኖረ ሰው የህይወት ልምድ ይኖረዋል። በ30 ዓመቱ በረዳት ዳኝነት ተሹሞ በትንሹ ለ3 እና 4 ዓመት ቢሠራና በ35 አመቱ የዳኝነት ሃላፊነት ቢወስድ፣ የቀረበለትን ጉዳይ አመዛዝኖ መርምሮ መወሰን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እድሜን ሣነሳ ለእኔ የሚያሳስበኝ የማገናዘብ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በጥብቅና ስራ 28 አመቴ ነው እና ብዙ የምታዘባቸው ነገሮች ስላሉ ነው ይሄን የምለው፡፡
በሌላ በኩል ዳኞች በግልጽ መስፈርት ይለዩ የምልበት ምክንያት ደግሞ ይሄ አሁን ገለልተኛ አይደሉም የሚለውን ሃሜት ያስቀረዋል፤ እስካሁንም በግልፅ ቢሠራ የፍትህ አካሉ ለዚህ ሃሜት አይዳረግም ነበር፡፡
የዳኝነት ተቋሙ አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ነው ብለው ያስባሉ?
ይሄ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የዳኝነት ተቋም ነፃነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይሄን ማረጋገጡ የሚታየው ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ነው፡፡ እኛ ሀገር ዳኝነቱ ነፃነት የለውም የሚለው ሃሜት የበረከተው በሚታዩ ነገሮች መነሻነት ነው፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች ዳኞች ነፃነታቸውን የሚያስጠብቅ የሙያ ማህበር አላቸው፡፡ እኛ ሀገር የለም፡፡ ይሄ ማህበር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ማህበሩ ከምን ይጠብቃቸዋል ከተባለ አንደኛ በህሊናቸው ተመርተው ህግን መሰረት አድርገው በሰጡት ውሳኔ የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ለመከላከል ያስችላቸዋል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጥቅማጥቅማቸውን ለማስከበር ይረዳቸዋል፡፡
ዳኞች የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ከተፈለገ ይህ የሙያ ማህበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዳኛ ህግን መሰረት አድርጎ ውሳኔ ለመስጠት ከውሳኔው በኋላ በስራዬ፣ በህይወቴ፣ በቤተሰቤ ምንም ነገር አይደርስብኝም የሚል መተማመን ሊኖረው ይገባል፡፡ ይሄ በራስ መተማመን ሊፈጠር የሚችለው በማህበር ተደራጅቶ፣ ራሱን መከላከል ሲችል ነው፡፡ ይሄ አሁን ባለው ሁኔታ እኛ ሀገር የለም። የህግ የበላይነትን ለማምጣት ከሆነ ጥረቱ አሁንም አንድ ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን በአስቸኳይ ተቋቁሞ የእስከ ዛሬውን የዳኞችን አሰራር የሚገመግምና አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ችግሮች የፈተሸ ሪፖርት ማቅረብ አለበት፡፡ ነፃ የሆነ የማንኛውም የፖለቲካ ተፅዕኖ የሌለበት፣ ይህ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ ዳኝነቱ ነፃ የሚወጣበትን መፍትሄ የሚያፈላልግ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት አቅርቦ በፖለቲካ ተፅዕኖ ስር የወደቀው የዳኝነት ስርአቱ ነፃ የሚወጣበት መፍትሄ መበጀት አለበት፡፡ የዳኝነት ተቋሙ በህገ መንግስቱ መሰረት በነፃነት ስራውን ሰርቷል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል ወይ የሚለው  የሁልጊዜ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ የሚችለው ይህ ገለልተኛ ተቋም የሚያቀርበውን የምርመራ ሪፖርት መነሻ አድርጎ ሊወሰዱ በሚችሉ እርምጃዎች ብቻ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ችግሩን ከእነ መፍትሄው ማቅረብ አለበት። አሁን ሁሉም ሰው ያሉትን ችግሮች በራሱ እይታ ነው የሚተረጉመው፡፡ ሊቋቋም ይገባዋል ብዬ የማምነው ገለልተኛ ኮሚሽን፤ የዳኞች አሿሿምን፣ የፖሊስ አሠራርን፣ የአቃቤ ህግ አሰራርን፣ የጠበቆች አሠራርን፣ የማረሚያ ቤት አሰራርን፣ በጥልቀት የሚፈትሽና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠቃላይ የፍትህ ስርአቱን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ የሚያወጣ መሆን አለበት፡፡ ይሄ በአስቸኳይ ካልተፈፀመ ስለ ህግ የበላይነት የሚነሡ ጥያቄዎች ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡
ብዙዎቹ የሃገሪቱ ችግሮች የሚመነጩት’ኮ በሃገራችን የህግ የበላይነት ባለመኖሩ ብቻ ነው፡፡ የህግ የበላይነት የለም ማለት ደግሞ ፍትህ የለም ማለት ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ይህቺን ሃገር ያስተዳደሩና የገዙ መንግስታት አንዱ ትልቁ ችግራቸውና ድክመታቸው እንዲሁም ሊወቀሡበት የሚገባቸው ከፓርቲና ከመንግስት ተፅዕኖ ነፃ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን አለመፍጠራቸው ነው፡፡ አሁንም እነዚህ የሉም። ምናልባት ሙከራዎች ሊደረጉ ይችላሉ እንጂ ነፃ ተቋማት የሉም፡፡
ከዚህ በመነሣት ነው የሃገራችን ችግር የህግ የበላይነት አለመኖር ነው የምለው፡፡ የህግ የበላይነት የሌለው ደግሞ የፍትህ ተቋማት ከፖለቲካ ነፃ ሆነው መስራት ባለመቻላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ በዚህ በሚቋቋመው ኮሚሽን አማካኝነት መጣራት አለበት። ደህንነቱን ከፖለቲካ ጫና ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ የፍትህ አካሉ ለምንድን ነው ተደጋግሞ የሚወቀሠው የሚለው በአፋጣኝ የመጨረሻ ምላሽ ማግኘት አለበት።
ሰሞኑን 7ኛው የፍትህ ሣምንት መሪ ቃል፤ ‹‹የህግ የበላይነት ለዘላቂ ሠላምና ለህዝቦች አንድነት›› ይላል፤ ይሄ አስገራሚ ነው፡፡ ይሄንን ማረጋገጥ ያለበት ገለልተኛ ኮሚሽን ነው፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው ዳኛ የተከበሩ ሲባል ከርሞ፣ አንድ ቀን ደግሞ ጠበቃ የሚሆነው። ይሄ ስህተት ነው፡፡ አንድ ጊዜ በዳኝነት ወንበር ላይ የተቀመጠ ሰው የሚሞተው እዚያው በዳኝነቱ ወንበር ላይ ነው እንጂ ዳኛ ሆኖ ወደ ጠበቃ መምጣት ለፍትህ አሠጣጡም ተገቢ አይሆንም፡፡ ፍትህ ይዛባል። አላማቸው ጠበቃ መሆን ስለሆነ ፍትህ ይዛባል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳኝነት ኑሮ መሻሻል አለበት። ዳኛ ስለሚበላውና ቤተሠቡን ስለሚመግበው መጨነቅ የለበት፡፡ ሁሉም ሊሟላለት ይገባል፡፡ ሃሳቡ በሙሉ ዳኝነቱ ላይ መሆን አለበት፡፡ እኛ ሃገር ግን የምንታዘበው፤ የሞት ፍርድ የፈረደ ዳኛ፣ ከሰው ጋር ታክሲ ተጋፍቶ ሲሳፈርና በእግሩ ሲሄድ ነው፡፡ ይሄ መሆን የለበትም፡፡ የዳኞች ኑሮ በእጅጉ መሻሻል አለበት፡፡
እርስዎ እንደ ጠበቃ በዳኞች አካባቢ የሚታዩ ጉድለቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
በጣም ጠንቃቃና ችሎቱን ስነስርአት የሚያስይዙ ጎበዝ ዳኞች ያሉትን ያህል ዳኛ ይሁኑ ባለጉዳይ የማይለዩ፣ በአለባበሳቸውም ዳኛ የማይመስሉ ሰዎችም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ በፍ/ቤቶች የአለባበስ መመሪያ መኖር አለበት፡፡ እኔ ከምታዘበው ነገር ከኔ ጀምሮ ችሎት ስንቆም ከረባት አናስርም፡፡ ይሄ ስህተት ነው። የአለባበስ መመሪያ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ በፍ/ቤት ስንቆም “የተከበሩ … ጌታዬ” የምንለው እኮ ግለሰቡን አይደለም፤ ተቋሙን ነው፡፡ እዚያ ተቋም ውስጥ ያለ ሰው ደግሞ ይሄን ክብር የሚመጥን ሆኖ መቅረብ አለበት፡፡ ሌላው ሳልናገር የማላልፈው በፍ/ቤቶች ያለው የመፀዳጃ ቤት ችግር፣ የካፍቴሪያ ችግር ነው። ዳኞቻችን ወደድንም ጠላንም ክብር ይገባቸዋል፤ በፓርላማ የተሾሙ የተከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄንን ክብራቸውን የሚመጥን አገልግሎት ነው በስራ ቦታቸው ማግኘት ያለባቸው፡፡ የላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠው ልንመለከታቸው አይገባም። እኔ እንኳ ስለዚህ ነገር መናገር ከጀመርኩ ከዓመት በላይ ሆኖኛል፤ ግን ሰሚ የለም፡፡ ከፍ/ቤት በላይ ምን የሚከበር ተቋም ሊኖር ይችላል! የለም ስለዚህ ፍ/ቤቶች የሚገባቸውን ክብር የሚመጥን አደረጃጀትና አገልግሎት መስጫዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ሌላው የዳኞች ስነ ምግባር መታሰብ አለበት። አንዳንዶች ያመናጭቃሉ፣ ያልተገባ ንግግር ይጠቀማሉ፣ ሰዎችን ስሜታዊ ያደርጋሉ፤ እንዲህ ያሉ ዳኞች ሊታረሙ ይገባቸዋል፡፡
ሌላው በተደጋጋሚ የሚታየው ችግር የአሰራሮች አለመስተካከል፣ ደንበኞችን ማጉላላታቸው ነው። ከመቅረፀ ድምፅ ወደ ጽሑፍ ተገልብጦ ይቅረብ ይባልና የቀጠሮ ምልልስ ይፈጠራል፤ ይሄ ለፍትህ አሰጣጡ ተግዳሮት ነው፡፡ ሌላው የምታዘበው ነገር ባለጉዳይና ጠበቃ የሚመካከሩበት ቦታ የለም፡፡ ይሄ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ፍ/ቤት አካባቢ የመመካከሪያ ቦታ ሊኖር ይገባል። በአጠቃላይ የፍ/ቤት ግቢዎች ለፍትህ አሰጣጡ አመቺ የሆኑ ነገሮች ተሟልተው የሚገኙባቸው አይደሉም፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነው፡፡
ሌላው የፍ/ቤት ሰራተኞች ደንበኞች የማመናጨቅ፣ የመገፈታተርና የተለያዩ ችግሮች ይፈጥራሉ፤ ይሄ መታረም ያለበት ነው፡፡ ፍትህ ሊያገኝ ወደ ፍ/ቤት የመጣ ሰው ሊንገላታ አይገባውም፡፡

Read 5220 times