Sunday, 21 May 2017 00:00

የመኢአድ እና ሰማያዊ አመራሮች፤ ታሳሪ አባሎቻችንን እንዳንጠይቅ ተከለከልን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

       የመኢአድ እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፤ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ አባሎቻችንን እንዳንጠይቅ ተከለከልን ሲሉ ያማረሩ ሲሆን ታሳሪዎች ከሚደርስባቸው እንግልት የተነሳ ለከፍተኛ የጤና ችግር እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ማክሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2009 ዓ.ም ለታራሚዎች አስፈላጊ ይሆናሉ ያሏቸውን ቁሳቁሶች ይዘው ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቢሄዱም፣”እቃውም አይገባም፤ እናንተም መጠየቅ አትችሉም” መባላቸውን አስረድተዋል፡፡
ክልከላውን በተመለከተ የጥበቃ አባላቱ የግል ውሳኔ ይሁን የኃላፊዎቹ ለማረጋገጥ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በደብዳቤ ቢጠይቁም እስከ ሐሙስ ማታ ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
አባሎቻቸው በከፍተኛ ህመምና ስቃይ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣እንዲጎበኟቸው ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሰረት ወደ ማረሚያ ቤቱ ቢሄዱም ምንም ዓይነት ማብራሪያና አሳማኝ ህጋዊ ምክንያት ሳይሰጣቸው እንዳይጠይቁ መከልከላቸውን አመራሮቹ ገልጸዋል፡፡
አባሎቻቸው የሚፈልጉትን የህግና ሞራል ድጋፍ፣ የህክምና እርዳታ እንዲሁም የአልባሳትና ልዩ ልዩ አላቂ የፅዳት መገልገያዎችን ለመስጠት አቅደው ወደ ስፍራው መጓዛቸውን የጠቆሙት የፓርቲዎቹ አመራሮች፤ “ክልከላው ታሳሪዎች ባይተዋርነት እንዲሰማቸውና ማንም እንደማያስታውሳቸው እንዲያስቡ የተቀነባበረ ሴራ ነው” ብለዋል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ያደረገባቸው ክልከላ ህገ ወጥ መሆኑንና በህገ መንግስቱ ላይ በህግ ጥበቃ ስር ያሉ ዜጎች አያያዝን በሚመለከት የተደነገገውን አንቀፅ የሚጥስ እንደሆነ ገልፀዋል - አመራሮቹ፡፡   

Read 2210 times