Sunday, 21 May 2017 00:00

የአውሮፓ ፓርላማ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሣና ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲፈቱ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

‹‹የፓርላማው ውሣኔ ተቀባይነት የለውም›› - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሣና የተቃዋሚ ፖለቲከኛው ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲፈቱ የሚጠይቅ የውሣኔ ሃሣብ ያሣለፈ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ውሣኔው ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ፓርላማው ከትናንት በስቲያ ያሣለፈው የውሣኔ ሃሳብ በዋናነት ፖለቲከኛው ዶ/ር መረራ ጉዲና በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ ሲሆን የፀረ ሽብር አዋጁም የተቃውሞ ድምፆችን ለማፈኛነት ከማዋል እንዲታቀብ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሣና የህዝብ ሙሉ ነፃነት እንዲከበር የሚያሳስብ ነው፡፡
የውሣኔ ሃሣቡ  በኢትዮጵያ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለ8 ወራት በዘለቀው የህዝብ ተቃውሞና አመፅ ስለደረሰው ጉዳት በገለልተኛ የውጭ መርማሪ እንዲጣራ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈቅድ የህብረቱ ከፍተኛ ተወካዮች ግፊት ያደርጉ ዘንድ ጠይቋል፡፡
የህብረቱ ፓርላማ ያፀደቀው የውሣኔ ሃሳብ በአባላቱ ቀርቦ የነበረ ሲሆን በስብሰባው ከተሣተፉት 100 ያህል አባላት 90ዎቹ የውሣኔ ሃሳቡን እንዳፀደቁት ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል 14 የአሜሪካ ሴኔት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት ይፈፅማቸዋል ያሏቸውን የሠብአዊ መብት ጥሰትና የዜጎች መብት ገደቦችን አስመልክቶ ለሴነቱ የውሣኔ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን የአሜሪካ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት በድጋሚ እንዲመረምር ጠይቀዋል፡፡
የአውሮፓ ፓርላማ ስላሣለፈው የውሣኔ ሃሳብና የአሜሪካ ሴኔት አባላት ስላቀረቡት መከራከሪያ ጉዳይ ለአዲስ አድማስ የመንግስትን አቋም የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ ‹‹በመንግስት በኩል ሁለቱም ጉዳዮች ብዙም ትኩረት አይሠጣቸውም፤ በሃገሪቱ ላይም ምንም ተፅዕኖ አይኖራቸውም›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የስትራቴጂካዊ ግንኙነት ስምምነት መፈራረሟን የጠቀሱት አቶ መለስ፤ ፓርላማው ያሣለፈው ውሳኔ በዚህ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት በተለይም በፀረ ሽብር ትግል አቋም ላይ ተፅዕኖ የማይፈጥርና ትርጉም የሌለው ነው›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ሴኔት አባላት ያቀረቡትም ቢሆን ከዚህ በፊት ሲቀርቡ ከነበረው የተለዩ ባለመሆናቸው ተቀባይነት አይኖራቸውም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡


Read 4683 times